የህወሃት “ጁንታ” በትግራይ ክልል የኤሌክትሪክ መሰረተ ልማት ላይ ያደረሰው ጥፋትና ኪሳራ

በትግራይ ክልል የህወሃት ጁንታ የኤሌክትሪክ መሰረተ ልማት ላይ ባደረሰው ጥፋት ከ240 ሚሊዮን ብር በላይ ጉዳት ሲደርስ፤ በቢሊዮን የሚቆጠር ገቢ መታጣቱን የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል አስታወቀ።

ይህ በእንዲህ እንዳለ ለ116 ኪሎ ሜትር የኤሌክትሪክ መስመር ጥገና ተደርጎ ስራ መጀመሩን የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ አገልግሎት ገልጿል።

የህወሃት ጁንታ በትግራይ ክልል የኤሌክትሪክ መሰረተ ልማት ላይ ባደረሰው ጥፋት ከ240 ሚሊዮን ብር በላይ የሚገመት ጉዳት መድረሱን ነው የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል ለኢዜአ የገለጸው።

የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል የኮሙኒኬሽን ዳይሬክተር አቶ ሞገስ መኮንን እንደገለጹት ጁንታው በክልሉ የኤሌክትሪክ መሰረተ ልማት ላይ ያደረሰው ጥፋት ከፍተኛ ጉዳትና ኪሳራ አስከትሏል።

በዚህም በክልሉ ከባህርዳር አላማጣ፤ ከኮምቦልቻ አላማጣ እንዲሁም ከተከዜ አክሱምና ከአሸጎዳ መቀሌ በሁለት አቅጣጫዎች የሚገኙ የኃይል ማስተላለፊያ መስመሮች መጎዳታቸውን ተናግረዋል።

በሰሜን ሪጅን የሚገኙ ሶስት ባለ 66 ኪሎ ቮልት፣ አምስት ባለ 132 ኪሎ ቮልትና ሰባት ባለ 230 ኪሎ ቮልት የኃይል ማከፋፈያ ጣቢያዎች ጉዳት እንደደረሰባቸው አስረድተዋል።

በክልሉ የተለያየ አቅም ያላቸው 1 ሺህ 727 ኪሎ ሜትር ርዝመት ያላቸው የኃይል ማስተላለፊያ መስመሮች መበጣጠሳቸውንም እንዲሁ።

በተጨማሪም ግምቱ 15 ሚሊዮን ብር የሆነ የመለዋወጫ ዕቃ የጫኑ አምስት ተሽከርካሪዎች በጁንታው ተዘርፈው እስካሁን ያሉበት እንደማይታወቅ ገልጸው፤ ይህም በጥገና ስራው ላይ ተጽዕኖ አሳድሯል ብለዋል።

በወልቃይት በቢሮዎች፣ የሰራተኛ መኖሪያ ቤት የመለዋወጫ ዕቃዎች ማስቀመጫ ክፍሎች ላይ ጉዳት መድረሱንና የተዘረፈውን ጨምሮ ጉዳቱ በገንዘብ እንዳልተተመነ ተናግረዋል።

በማስተላለፊያ መሥመሮችና ሰባት የኃይል ተሸካሚ ማማዎች ላይ ጉዳት መድረሱንም ነው አቶ ሞገስ ያስታወቁት።

ኢትዮ ቴሌኮም የሚጠቀምበት ኦ ፒ ጂ ኤን የተባለ ፋይቨር ላይ የደረሰው ጉዳት ግምት እስካሁን እንዳልወጣም ተናግረዋል።

በጉዳቱ ከ245 ሚሊዮን ኪሎ ዋት በላይ ኃይል መባከኑን ያስረዱት አቶ ሞገስ፤ ኃይሉ ቢሸጥ ከ146 ቢሊዮን ብር በላይ ገቢ ይገኝበት ነበር ብለዋል።

በማስተላለፊያ መስመሮች ላይ የሚደረገው የፍተሻ ሥራ ከ80 በመቶ በላይ መድረሱን ጠቁመው የተከዜ የኤሌክትሪክ ኃይል ማመንጫ መስመርን ጠግኖ ከብሄራዊ የኃይል ቋት ጋር የማገናኘትና ወደ መቀሌ የሚሄደው የ230 ኪሎ ቮልት መስመር ጥገና እንደሚከናወንም ገልጸዋል።ENA

Leave a Reply