Site icon ETHIO12.COM

ከመጋረጃ ጀርባ የሚሰጥ ምስክርነት የህግ መሰረቱ እና ሀገ-መንግስታዊነቱ


  1. መግቢያ
    ምስክሮች በፍትህ ስርዓት ውስጥ ፍትሃዊ ውሳኔ ለመስጠት እና ፍትህ ለማስፈን የማይተካ ሚና አላቸው፡፡ምስክሮች በወንጀል ፍትህ ስርዓት ውስጥ የወንጀል ጥቆማ ከመስጠት ጀምሮ በምርመራ ሂደት መሳተፍ እና በችሎት ክርክር ምስክርነት በመስጠት የፍትህ ስርዓቱን ያግዛሉ፡፡ምስክሮች የሚሰጡት ምስክርነት በተቃራኒው በተከራካሪ ወገን ወይም በተከሳሽ ላይ ፍርድ የሚያከትል በመሆኑ ተከሳሾች በወንጀል ምርመራ እና በክስ ሂደት በምስክሮች ወይም በቤተሰቦቻቸው ላይ ጫና በማሳደር እና በማስፈራራት የፍትህ አስተዳደርን ለማደናቀፍ ጥረት ሊያደርጉ ይችላሉ፡፡ስለሆነም ለወንጀል ምስክሮች ጥበቃ በማድረግ ከጥቃት እና ከአደጋ ስጋት ነፃ የሆነ ምስክርነት እንዲሰጡ ማስቻል እስፈላጊ ነው፡፡በዚህ ምክንያት በአለም ላይ የተለያዩ ሀገራት የምስክሮች ጥበቃ ህግን በማውጣት በስራ ላይ ያዋሉ ሲሆን ህጎቹ በአብዝሀኛው ጥበቃ የሚያደርጉት ለከባባድ እና የቅጣት መጠናቸው ከፍተኛ ለሆኑ ወንጀሎች ነው፡፡ ኢትዮጵያም የወንጀል ምስክሮችና ጠቋሚዎች ጥበቃ አዋጅ ቁጥር 699/2003 በማውጣት በስራ ላይ አውላለች፡፡ በአዋጁ ለወንጀል ምስክሮች ከሚደረጉ የጥበቃ እርምጃዎች ውስጥ ምስክርነትን ከመጋረጃ ጀርባ መስጠት ይገኝበታል፡፡ ይህ ፅሁፍ ስለ ምስክሮች ጥበቃ አለም አቀፍ ተሞክሮዎችን በማካተት በኢትዮጵያ ከመጋረጃ ጀርባ ምስክርነት ስለሚሰጥበት ሁኔታና ከተከሳሻ መብትአንፃር የህግ መሰረቱን ይዳስሳል፡፡
  2. የምስክሮች ጥበቃ ህግ በአለም አቀፍ ተሞክሮ
    የምስክሮች ጥበቃ ለመጀመሪያ ጊዜ ከፍተኛ ትኩረት ያገኘው በ1970ዎቹ በአሜሪካን ሀገር ሲሆን ይህም የማፍያ ስታይል የወንጀል ቡድኖች ለማፈራረስ ጥቅም ላይ በማዋል ነው፡፡ በዚህ ወቅት የተደራጁ ወንጀሎች መቆጣጠሪያ አክት የአሜሪካ ጠቅላይ አቃቤ ህግ በምስክሮች ደህንነት ፕሮግራም ስር በተደራጁ ወንጀሎች እና በሌሎች ከባድ ወንጀሎች ላይ ምስክርነት ለመስጠት ፍቃደኛ የሆኑ እና ደህንነታቸው በአደጋ ስጋት ስር የሆኑ ምስክሮች የመኖሪያ ቦታቸውን ወደ ማይገለጥ አዲስ አካባቢ እንዲቀይሩ እና ማንነታቸውንም እንዲቀይሩ የሚያስችል ነበረ፡፡ በ1983 የአውስትራሊያ ሮያል ኮሚሽን በተለይ የተደራጁ ወንጀሎች ላይ መረጃ ሰጭዎችን በተሻለ ሁኔታ መጠቀምን ትኩረት በማድረግ እና ዝቅተኛ ተሳትፎ ያላቸው በዋና ወንጀል አደራጆች ላይ መረጃ እንዲሰጡ በማድረግ እስከ የመኖሪያ አካባቢ እና ማንነት መቀየር የሚደርሱ ህጎችን በማውጣት በስራ ላይ አውላለች፡፡

በጀርመን የምስክሮች ጥበቃ ለመጀመሪያ ጊዜ ስራ ላይ የዋለው በሀምበርበርግ ከሞተር ሳይክል ወንበዴዎች ወንጀል ጋር በተያያዘ በ1980ዋቹ ነው፡፡ በ1998 የምስክሮች ጥበቃ አክት (Witness Protection Act) ያወጣች ሲሆን በማንኛውም የፍትህ ሂደት የምስክሮች ግላዊ መረጃዎች በሚስጥር መያዛቸውን ማረጋገጥ፣ ለወንጀል ተጎጂዎች እና ምስክሮች የህግ ድጋፍ መስጠት ላይ ትኩረት ያደረገ ነው፡፡
በአብዛህኛው እነኝህ የአለም ሀገራት ለተደራጁ ወንጀሎች ምስክሮች በፍርድ ቤቶች በስራ ላይ የሚውሉ ስነ ስርዓታዊ የጥበቃ እርምጃዎች ምስክሮች ለህይወታቸው ከሚያሰጉ ሁኔታዎች ውጪ ሆነው ያለስጋት በነፃነት እንዲመሰክሩ የሚያስችሉ ዘዴዎችን የሚጠቀሙ ሲሆን ምስክርነት ከስክሪን ወይም ከመጋረጃ ጀርባ እንዲሰጥ ማድረግ አንዱ ዘዴ መሆኑን መረዳት ይቻላል፡፡

  1. የምስክሮች ጥበቃ ህግ በኢትዮጵያ
    በኢትዮጵያ የተሻሻለው የፀረ ሙስና ልዩ የሥነ ሥርዓትና ማስረጃ ህግ አዋጅ ቁጥር 434/1997፤ የሽብር ወንጀልን ለመከላከል እና ለመቆጣጠር የወጣው አዋጅ ቁጥር 1176/2012፤ በሰው የመነገድ እና ሰውን በህገ ወጥ መንገድ ድንበር የማሻገር ወንጀልን ለመከላከልና ለመቆጣጠር የወጣው አዋጅ ቁጥር 1178/2012፤ በ2003 የወጣው የኢ.ፌ.ድ.ሪ የወንጅል ፍትህ ፖሊሲ እና የወንጀል ምስክሮችና ጠቋሚዎች ጥበቃ አዋጅ ቁጥር 699/2003 ለምስክሮች ጥበቃ ስለማድረግ ሰፊ ሽፋን ሰጥተዋል፡፡ አዋጅ ቁጥር 699/2003 ተፈፃሚ የሚሆነው በሕግ የተደነገገው የፅኑ እስራት መነሻ ከግምት ሳይገባ አስር ዓመትና ከዚያ በላይ በሆነ ጽኑ እስራት ወይም በሞት ሊያስቀጣ በሚችል የወንጀል ድርጊት ተጠርጣሪ ላይ የሚሰጥ ምስክርነትን ወይም ጥቆማን ወይም የሚካሄድ ምርመራን በሚመለከት ሆኖ የወንጀል ድርጊቱ ያለምስክሩ ወይም ያለጠቋሚው ምስክርነት ወይም ጥቆማ በሌላ ማናቸውም መንገድ ሊረጋገጥ ወይም ሊደረስበት የማይችል ሲሆን፤ እና በምስክሩ፣ በጠቋሚው ወይም በቤተሰብ ህይወት፣ አካላዊ ደህንነት፣ ነጻነት ወይም ንብረት ላይ ከባድ አደጋ ይደርሳል ተብሎ ሲታመን ነው፡፡ በአዋጁ አንቀጽ 4 ስር የጥበቃ እርምጃ አይነቶች በዝርዝር የተቀመጡ ሲሆን እርምጃዎቹ በተናጠል ወይም በጣምራ ለጥበቃ ተጠቃሚ ተፈጻሚ ሊደረጉ ይችላሉ፡፡ በአዋጁ ከተዘረዘሩት የጥበቃ እርምጃዎች ውስጥ የአካልና ንብረት ደህንነት ጥበቃ፣የመኖሪያ ስፍራ መቀየርን ጨምሮ ደህንነቱ የተጠበቀ የመኖሪያ ቦታ መስጠት፣ ማንነትንና ባለንብረትነትን መደበቅ፣ማንነትን መቀየር፣ለራስ መጠበቂያ የነፍስ ወከፍ መሳሪያ መስጠት፣የፍርድ ሂደት ተጀምሮ ምስክርነት እስከሚሰጥ ድረስ የምስክር ማንነት እንዳይገለጽ ማድረግ፣ምስክርነት በዝግ ችሎት እንዲሰጥ ማድረግ፣ምስክርነት በአካል ሳይታይ ከመጋረጃ በስተጀርባ ሆኖ ወይም ማንነትን በመሸፈን እንዲሰጥ ማድረግ፣ ማስረጃ በኤሌክትሮኒክስ ወይም በሌላ የተለየ ዘዴ እንዲቀርብ ማድረግ ይገኙበታል፡፡
  2. ከመጋረጃ ጀርባ ምስክርነት ስለመስጠት የየህግ መሰረቱ እና ህገመንግሰታዊነቱ
    በወንጀል ምስክሮችና ጠቋሚዎች አዋጅ 699/2003 አንቀፅ 4/1/በ የተገለጸው የምስክሮች ከመጋረጃ ጀርባ ምስክርነት መስጠት የሚያስፈልገው ከተከሳሽ ጋር የዐይን ግንኙነት ስለማይኖራቸው ያለፍርሃት የሚያውቁትን ሐቅ ለማስረዳት ስለሚያስችላቸው እና ተከሳሽ የምስክሩን ማንነት መለየት ስለማይችል በምስክሮች ላይ ሊደርስ የሚችለውን ዛቻ እና ማስፈራራት እንዲሁም በህይወት እና በንብረት ላይ ሊደርስ የሚችል አደጋን ማስቀረት ስለሚያስችል ነው፡፡ ምስክሮች ከመጋረጃ ጀርባ ምስክርነት እንዲሰጡ ሲደረግ ሁለት ተቀናቃኝ ፍላጎቶች ይንፀባረቃሉ፡፡ እነዚህም በአንድ በኩል ፍትህ ለማገዝ ሲሉ ህይወታቸው እና ንብረታቸው በተከሳሻ ሊደርስ ከሚችል የአደጋ ስጋት ውስጥ ለገባ ምስክሮች መደረግ ስላለበት ጥበቃ ሲሆን በሌላ በኩል ደግሞ የተከሳሾች መብት ነው፡፡ በICCPR አንቀፅ 14 እንደተደነገገው የተከሰሱ ሰዎች የቀረበባቸውን ማስረጃ የመከላከል እና ምስክሮችን መስቀለኛ ጥያቄ የመጠየቅ መብት አላቸው፡፡ በተመሳሳይ በኢ.ፌ.ዲ.ሪ ህገ-መንግስት አንቀፅ 20(1)እና(4) ለእነዚህ የተከሳሽ መብቶች እውቅና ተሰጥቷቸው ይገኛሉ፡፡ ከዚህ አንጻር የምስክሮች ከመጋረጃ ጀርባ ምስክርነት መስጠት ህገመንግስታዊ አይደለም የሚሉ ሰዎች አሉ፡፡

ይሁን እንጂ ማንነት ሳይገለፅ ምስክርነት ከመስጠት ጋር በፌደራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት 19ኛ የወንጀል ችሎት ህገ መንግስታዊ ጥያቄ ተነስቶ የነበረ ሲሆን ጉባዔው ፍርድ ቤቱ የላከውን የትርጉም ጥያቄ በመ/ቁ 2356/2009 መመርመሩን በመጥቀስ የሕገ መንግሥቱ አንቀጽ 20(4) ድንጋጌን በሚመለከት ማብራሪያ የሰጠ ሲሆን በአንቀጽ 20(4) ምስክሮችን በሚመለከት የተደነገገው የተከሰሱ ሰዎች የቀረቡባቸውን ምስክሮች የመጠየቅ መብት ያላቸው መሆኑን የሚያረጋግጥ እንጂ፣ የምስክሮችን ስም ዝርዝርና አድራሻ እንዲደርሳቸው ግዴታ የሚጥል አለመሆኑን ገለጿል፡፡በሕገ መንግሥቱ በአንቀጽ 20(4) ላይ ለተከሳሾች መብት የሰጠበት ምክንያት፣ ፍትሐዊ የሙግት አካሄድ እንዲኖር መሆኑን አክሏል፡፡ ተከሳሽ የምስክሮችን ስምና አድራሻ ማወቁ ፍትሐዊ የሙግት አካሄድን ከማሳካት ይልቅ፣ምስክሮችን ለአደጋ የሚያጋልጡ ሁኔታዎች እንዳይፈጸሙ አስቻይ ሁኔታዎችን ለመፍጠርና በሕጎች አግባብ እንዲወሰን ለማድረግ መሆኑን ጉባዔው አስረድቷል፡፡ በመሆኑም ተከሳሾች በሕገ መንግሥቱ አንቀጽ 20(4) መሠረት የምስክሮችን ስም ዝርዝር እንዳይደርስ ማድረግ፣ ከተገለጸው መብት ጋር የማይጋጭና የሕገ መንግሥቱን መርህ የተከተለ መሆኑን በመግለጽ፣ የቀረበለትን የሕገ መንግሥት ትርጉም ጥያቄ ውድቅ አድርጓል፡፡

ይህ የህገ መንግስት ጉዳዮች አጣሪ ጉባዔ ውሳኔ የሚያወለክተው ለምስክሮች ጥበቃ ሲባል ምስክሮች ከመጋረጃ ጀርባ ምስክርነት እንዲሰጡ ወይም የምስክሮች ማንነት እንዳይገለፅ ማድረግ በህገ መንግስቱ ላይ ከተቀመጠው የተከሰሱ ሰዎች መብት ጋር የማይቃረን እና ህገ መንግስቱን የተከተለ ህግ መሆኑን ነው፡፡ ምስክሮች ማንነታቸው ሳይገለጹ ከመጋረጃ ጀርባ ሆነው ምስክርነት እንዲሰጡ ቢደረግም ተከሳሾች የቀረቡባቸውን ምስክሮች በችሎት መስቀለኛ ጥያቄ ከመጠየቅ የሚያግዳቸው ባለመሆኑ የተከሰሱ ሰዎች የመከላከል መብት ላይ የሚያስከትለው አሉታዊ ተፅዕኖ አለ ማለት አይቻልም፡፡ ስለሆነም ከመጋረጃ ጀርባ ምስክርነት እንዲሰጥ ማድረግ ፍትህ ለማገዝ ሲሉ ህይወታቸውን ለአደጋ መጋለጥ አሳልፈው ለሰጡ ምስክሮች ጥበቃ ሲባል መከናወን ያለበት የፍትህ ስነ ስርዓት ህገ መንግስታዊ ነው፡፡

በአጠቃላይ ፍትህ በማገዝ ሂደት ህይወታቸው የአደጋ ስጋት ውስጥ ለሚገኝ የወንጀል ምስክሮች የሚወሰዱ የጥበቃ እርምጃዎች ወንጀል ፈፃሚዎች ተገቢውን ቅጣት እንዲያገኙ እና የህብረተሰቡ ሰላማዊ ኑሮ እንዲረጋገጥ ተጠናክረው መቀጠል አለባቸው፡፡

Attorney general

Exit mobile version