Site icon ETHIO12.COM

አስፈሪው ጊዜ በደጅ ነው – ለኮቪድ-19 ጽኑ ህሙማን የኦክስጂንና የቬንትሌተር እጥረት አጋጥሟል፤ ስብሰባ ቀጥሏል

ከሶስት ሳምንት በፊት አንድ ሃኪም በፋና ቴኤቪዥን ቀርባ ስትናገር ለሰሚው አስደንጋጭ ነበር። ሐኪሟ እንባ እየተናነቃት “ወገኖቻችን አየር እየሉ… መተንፈስ እያቃታቸው እጃችን ላይ እየሞቱ ነው” በማለት አስደንጋጩ ጊዜ ከፊት እየመጣ መሆኑንን አመላክታ ነበር። እንደሚያተውና እንደሚሰማው ጥንቃቄው ቆሟል። ስብሰባ በየቦታው ይካሄዳል። የምርጫ ቅስቀሳ እንጂ የኮቪድ ወረርሺኝ ስጋት የሆነ አይመስልም።

የዕለት ጉርሱን መሸፈን የማይችል ዜጋ በበረከተበት አገር ጥንቃቄውን ሙሉ በሙሉ ለመተግበር አስቸጋሪ ቢሆንም፣ ዛሬ ላይ እየወጡ ያሉት ሪፖርቶችና ዜናዎች የሚያስጨንቀው ጊዜ ስለመድረሱ አመለካች ነው።

ዛሬ ከመቶ ሰዎች 19 የሚሆኑት በኮቪድ መያዛቸው እየተሰማ ነው። ሰሞኑንን በሁለት ቀን ብቻ 57 ግለሰቦች በኮቪድ-19 ህይወታቸውን ያጡ ሲሆን በአጠቃላይ 2 ሺህ 540 ግለሰቦች በኮቪድ-19 ህይወታቸውን አጥተዋል። ቁጥሩ እንደሚያሳየው የሚያዙና የሚሞቱ ወገኖች እየበዙ ነው። ይህ በሌሎች ዓለማት እንደ ጣሊያን፣ ስፔንና ብራዚል የታየው አይነት ጅማሬ ነው።

እስካሁን ከፍተኛ የሞት ቁጥር ያስመዘገቡ ክልሎች :- አዲስ አበባ ቀዳሚውን ደረጃ ሲይዝ 1 ሺህ 852 ግለሰቦች ወይም 73 በመቶ፣ ኦሮሚያ ክልል 256 ግለሰቦች ወይም 10 በመቶ፣ በአማራ ክልል 105 ግለሰቦች ወይም 4 በመቶ፣ በሲዳማ ክልል 75 ግለሰቦች ወይም 3 በመቶ ግለሰቦች ህይወታቸውን አጥተዋል። በኮቪድ-19 በትላንትናው ዕለት ለ 7 ሺህ 654 ግለሰቦች ናሙና የሰጡ ሲሆን 1 ሺህ 483 ግለሰቦች የኮቪድ-19 ቫይረስ ተገኝቶባቸዋል ።

ቢቢሲ ኢንስቲትዩቱ የሰጠውን መረጃ አስመልክቶ ከታች ያለውን ዘግቧል።

በኢትዮጵያ በኮሮናቫይረስ የሚያዙና የጽኑ ህሙማን ህክምናና ክትትል የሚያስፈልጋቸው ሰዎች ቁጥር እየጨመረ በመምጣቱ የሰው ሰራሽ መተንፈሻ መሳሪያና የኦክስጂን እጥረት እያጋጠመ መሆኑ የሕብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት ገለጸ።

ተቋሙ በአሁኑ ጊዜ በአገሪቱ ውስጥ በኮቪድ-19 የሚያዙ ሰዎች ቁጥር ከዕለት ዕለት በከፍተኛ ደረጃ እየጨመረ በመምጣቱ የባለሙያ ድጋፍና እንክብካቤ የሚሹ ሰዎች ቁጥር “የህክምና ማዕከላት ማስተናገድ ከሚችሉት አቅም በላይ” እየሆነ መምጣቱን ጨምሮ ገልጿል።

በዚህም ሳቢያ በኮሮናቫይረስ በጽኑ ታምመው በህክምና ተቋማት ድጋፍ ለማግኘት ለሚመጡ ህሙማን አገልግሎት የሚውሉ “የሰው ሰራሽ የመተንፈሻ መሳሪያ (ቬንትሌተር) እና የኦክስጅን እጥረት እያጋጠመ ነው” ሲል ገልጿል።

በኢትዮጵያ እስከ ትናንት እሁድ ድረስ በተደረገ የላብራቶሪ ምርመራ 175,467 ሰዎች በኮሮናቫይረስ መያዛቸው ሲረጋገጥ፣ 2,550 ሰዎች ደግሞ ህይወታቸው አልፏል።

የኮሮናቫይረስ የመተንፈሻ አካላትን በተለይም ሳንባን የሚያጠቃ ሲሆን በበሽታው ክፉኛ ለተጠቁ ጽኑ ህሙማን ሰው ሰራሽ የመተንፈሻ መርጃ (ቬንትሌተር) እና ኦክስጂን ህይወታቸውን ለመታደግ ለሚደረገው ጥረት በእጅጉ አስፈላጊ ናቸው።

በኢትዮጵያ በኮሮናቫይረስ በጽኑ የታመሙ ሰዎችን ህይወት ለመታደግ በአሁኑ ወቅት በአገልግሎት ላይ የሚገኙት የሰው ሰራሽ የመተንፈሻ መርጃ ቬንትሌተሮች ቁጥር ከ500 ብዙም የበለጠ አይደለም።

ስለዚህም በበሽታው የሚያዙት ሰዎች ቁጥር በከፍተኛ ደረጃ መጨመሩ የህክምና ድጋፍ የሚፈልጉ ሰዎችን መጠን በመጨመር በህክምና ተቋማቱ ላይና በባለሙያዎች ላይ ጫናን በመፍጠር ከአቅም በላይ ሊሆን እንደሚችል ተሰግቷል።

በተለይም በወረርሽኙ በጽኑ ታምመው የቬንትሌተርና የኦክስጂን ድጋፍ የሚያስፈልጋቸው ህሙማን ቁጥር እየጨመረ በመሆኑ የነፍስ አድን አገልግሎቱን መስጠት ከማይቻልበት ደረጃ ላይ ከደረሰ የሚሞቱ ሰዎች ቁጥር በከፍተኛ ደረጃ ሊያሻቅብ ይችላል።

በአሁኑ ወቅት በመላው አገሪቱ በየዕለቱ የሚመዘገበው በኮሮናቫይረስ የተያዙ ሰዎች ቁጥር እየጨመረ መሆኑን የገለጸው ኢንስቲትዩቱ፤ ከዚሁ ጋር ተያይዞም በወረርሽኙ ሳቢያ የጽኑ ህሙማን የህክምና አገልግሎት የሚፈልጉ ህሙማንና ህይወታቸውን የሚያጡ ሰዎች ቁጥር “አስደንጋጭ በሆነ ሁኔታ እየጨመረ ይገኛል” ይገኛል ብሏል።

የኮሮናቫይረስ በኢትዮጵያ ውስጥ መገኘቱ ይፋ ከተደረገ ባለፈው ቅዳሜ አንድ ዓመት የሞላው ሲሆን፣ በዚህ ጊዜ እስካሁን ድረስ በወረርሽኙ ሳቢያ ህይወታቸውን ያጡ ሰዎች ቁጥር 2550 ደርሷል።

በኮቪድ-19 ለሞት ከተዳረጉት ሰዎች መካከል 74 በመቶ የሚሆኑት በህክምና ማዕከላት ውስጥ ሲሆን 24 በመቶዎቹ ደግሞ በአስክሬን ላይ ከተወሰደ ናሙና ላይ በተደረገ ምርመራ የተገኘ መሆኑ ተገልጿል።

ኢንስቲቲዩቱ እንደሚለው ባለፉት ጥቂት ቀናት እየተመዘገበ ያለው የሟቾች ቁጥር በከፍተኛ ደረጃ እየጨመረ ነው።

እስካሁን ድረስ በየዕለቱ ከተመዘገቡት ሞቶች ሁሉ ከፍተኛው በእነዚህ ቀናት ውስጥ ተመዝግቧል።

በወረርሽኙ ምክንያት የሞቱ ሰዎች ቁጥር በተለያዩ የአገሪቱ ከፍሎች የተመዘገቡ ሲሆን በዋና ከተማዋ አዲስ አበባ ውስጥ የተመዘገበው የሟቾች ቁጥር ከሌሎቹ ቦታዎች አንጻር በእጅጉ ከፍተኛ ነው።

በዚህም መሠረት በአዲስ አበባ 1,852 ሰዎች በኮቪድ-19 ሳቢያ ለህልፈት ሲዳረጉ ይህም ከአጠቃላዩ የሟቾች ቁጥር 73 በመቶውን ይይዛል።

በተከታይነት በኦሮሚያ ክልል 256 ሰዎች (10 በመቶ)፣ በአማራ ክልል 105 ሰዎች (4 በመቶ)፣ በሲዳማ ክልል 75 ሰዎች (3 በመቶ) የሚሆኑት በበሸውታው ህይወታቸው አልፏል። በየዕለቱ በሚደረገው ምርመራ ቫይረሱ የሚገኝባቸው ሰዎች ቁጥርም በፍጥነት እየጨመረ መሆኑ ተገልጿል።

Exit mobile version