Site icon ETHIO12.COM

በአማራ ክልል በአጣየ አካባቢ የተከሰተውን የጸጥታ ችግር መንግሥት በአስቸኳይ እንዲፈታ ነዋሪዎች ጠየቁ

በአማራ ክልል ሰሜን ሽዋ ዞን በኤፍራታና ግድም ወረዳ አጣየ ከተማ ነዋሪዎች በአጣየና አካባቢው ትናንት ከምሽቱ 3 ሰዓት አካባቢ ጀምሮ ተኩስ መከፈቱን ገልጸዋል፡፡

ነዋሪዎቹ እንደሚሉት ከዚህም በፊት በአካባቢው አልፎ አልፎ ተኩስ እንደነበር ገልጸው አሁን ላይ ግን በከባድ መሳሪያ ጭምር የታገዘ ጥቃት መፈፀሙን ተናግረዋል፡፡

ከባድ የሆነ የተኩስ ልውውጥ በአካባቢው በመኖሩ ከቤታቸው መውጣት እንዳልቻሉ የተናገሩት ነዋሪዎቹ የደረሰውን ጉዳት በውል ባያውቁትም በጎረቤታቸው የሰው ህይዎት መጥፋቱን አስክሬን ሲመጣ ማየታቸውን ነው የተናገሩት፡፡

አካባቢው ከዚህም በፊት ችግር እንደሚፈጠርበት የሚታወቅ በመሆኑ መንግሥት አስቀድሞ የጸጥታ ጥበቃ ሥራዎችን ሊሠራ ይገባ እንደነበር ነው የገለጹት፡፡

መንግሥት የአካባቢውን ማኅበረሰብ ከጉዳት እንዲታደግም ጠይቀዋል፡፡

ባንኮችንና የሰዎችን ንብረት የመዝረፍ ድርጊቶች ተፈጽመዋል ነው የሚሉት ነዋሪዎቹ፡፡

ነዋሪዎቹ ዘግይቶም ቢሆን የፌደራል ፖሊስ መግባቱን ተናግረው የተኩስ ልውውጡ ግን አለመቆሙን ነው የጠቆሙት፡፡

የሰሜን ሽዋ ዞን የሰላም እና የሕዝብ ደኅንነት መምሪያ ኀላፊ አቶ አበራ መኮንን መጋቢት 9/2013 ዓ.ም ጀምሮ በአማራ ክልል ሰሜን ሽዋ ዞን በኤፍራታና ግድም ወረዳ አጣየና አካባቢው እንዲሁም በኦሮሞ ብሔረሰብ አስተዳደር ዞን ጅሌ ጥሙጋ አካባቢዎች ተኩስ መከፈቱን ተናግረዋል፡፡

አጣየ አካባቢ አንድ ሰው በጥይት ተመቶ ህይወቱ አልፏል በሚል ግጭት መከሰቱን የተናገሩት ኀላፊው ጉዳዩን አመራሩ በማወያየት በሽምግልና የተፈታ ቢሆንም ድንገት ማታ ላይ ተኩስ መከፈቱን አብራርተዋል፡፡

ተኩሱ ከተጀመረ በኋላ የጸጥታ መዋቅሩን በማንቀሳቀስ የማረጋጋት ሥራ ሲሠራ ከቆየ በኋላ ወደ አካባቢው የፌደራል ፖሊስ እንዲገባ መደረጉን ነግረውናል፡፡

ችግሩ ከአቅም በላይ በመሆኑና ሊቆጣጠር የሚችል በቂ የጸጥታ ኀይል ባለመሠማራቱ ወደ ሌሎች አካባቢም ሰፍቶ ተኩሱ እስካሁን መቀጠሉን ተናግረዋል፡፡

ተኩሱ በከባድ መሳሪያ ጭምር የታገዘ እንደነበርም ነው የገለጹት፡፡ አሁን ላይ ተኩሱ በመጠኑም ቢሆን ጋብ በማለቱ የማረጋጋትና ሌሎች ሥራዎች እየተከናወነ እንደሆነም ነው ኀላፊው ያብራሩት፡፡

ጉዳዩን በቁጥጥር ስር ለማዋል የሚያስችል የጸጥታ ኃይል እንዲገባ እየተጠየቀ መሆኑን የነገሩን ኀላፊው አንዳንድ ቦታዎች ለእንቅስቃሴ የተዘጉ እና የተያዙ በመሆኑ ባለው ኃይልም ቢሆን ችግሩን በቁጥጥር ስር ለማዋል እንቅስቃሴ እየተደረገ መሆኑን ነው የነገሩን፡፡

ኀላፊው በሰው እና በንብረት ላይ የደረሰውን ጉዳት ወደፊት ተጣርቶ ለሕዝብ እንደሚገለጽ ተናግረዋል፡፡

ዘጋቢ፡- ምስጋናው ብርሃኔ (አብመድ)

Exit mobile version