የአማራ ሕዝብ ከፖለቲካ ነጋዴዎች ራሱን አግልሎ በአንድነት ይቁም!! ሰሜን ሸዋ፣ ጭልጋ፣ ፍኖተ ሰላም አማራ እየተወጋ ነው

የክልሉ የሰላምና ሕዝብ ደኀንነት ጉዳዮች ቢሮ ኃላፊ ሲሳይ ዳምጤ ሲናገሩ እንደተሰማው በሰሜን ሸዋ ያለው ሁኔታ የከፋ ነው። አማራ አንድ ሆኖ መነሳት አለበት። የአካባቢውን አመራሮች የጠቀሱ የሌሎች ሚዲያዎች እንዳሉት ወራሪው ሃይል እጅግ ብዙ ነው። አሁን ስፍራው ላይ ያለው ሊቋቋመው አይችልም።

አቶ ሲሳይ ” አማራ በአንድ ይቁም” ሲሉ ጥሪ አቅርበዋል። ተጨማሪ ሃይል ተሰባስቦ መመከት ካልተቻለ ሕዝቡ ሊጎዳ እንደሚችል ግልጽ አስቀምጠዋል። ” ክልሉ ወዳልተፈለገ አቅጣጫ እየተወሰደ ነው” ካሉ በሁዋላ ጭልጋ ትህነግ ያስለጠናቸው በአካባቢው ችግር እየፈጠሩ ነው፣ ከቅማንት ጋር ተያይዞ አጀንዳ እየተሰጣቸው ከመከላከያና ከክልሉ ልዩ ሃይል ጋር ተታኩሰዋል። አጀንዳ የተሰጣቸው ፍኖተ ሰላም አካባቢ ግጭት ፈጥረዋል። ይህንን ካሉ በሁዋላ የፖለቲካ ነጋዴዎች እሳቱና የህዝብ ስቃይ ስር እየተሯሯጡ መሆኑንን አመለክተዋል።

ዛሬ ሌላው ላይ ጣት መጠቆም ብዙም ዋጋ የለውም፤ መጀመሪያ የውስጥ አንድነትን መጠበቅ፣ እውነት ላይ ያተኮረ ህብረት አድርጎ፣ የትም ይሁን የትም፣ ማንም ይሁን ማን የችግሩን ሰንኮፍ መንቀል ላይ ማተኮሩ ይበጃል። ሕዝብ ሁሌም ሕዝብን አይነካምና በየትኛው ሁኔታ ለፖለቲካ ገበያ ራሳችንን አናውል

ሃላፊው ያለማመንታት እንዳሉት ግዜው ለአማራ ክልል ከባድ ነው። ክልሉ ደግሞ ያለ አንድነት ይህንን ችግር ሊወጣው አይችልም። በአገሪቱ የተለያዩ ክፍሎች ሰርቶና አፈር ገፍቶ የሚኖረው ሕዝብ ትህነግ ፈርጆት ለአደጋ እንዲጋለጥ አድርጎት ኖሯል። ይህ የኖረ አበሳ እንዳይበቃው ዛሬ ከውጭ በተጨማሪ ከራሱ ውስጥ በተነሱ አስመሳዮች ጭምር ጉዳት እየደረሰበት ነው።

ማንም ይሁን ማን ደሃ በማስጨረሰ ምንም አያተርፍም። ማንም ይሁን ማን በደሃ ደም ነግዶ እስከወዲያኛው አትራፊ አይሆንም። ዛሬ የዩቲዩብ ገበያ የደራላቸው “ተንታኞች” ሁሉም አይደሉም፤ ለማየት የሚዘገንን ምስል እየለጠፉ ቂም ይራባሉ። ሕዝብ ያሸብራሉ። አርፎ የተቀመጠውን እየነደፉና እየነካኩ አውሬ ያደርጋሉ። ለአንድ ሳምንት የሚዘገንን ምስል ቢያጡ የድሮውን ይለጥፋሉ። አንዳንዴም የራሳቸውን ምስል እንደ ሆሊውድ አክተር እየለጠፉ ሩቅ ተቀምጠው አገር ያሸብራሉ። እርኩሶች ሕጻናትን ሳይቀር ይገላሉ። ” ተንታኞቹ” ደግሞ የሞቱትን ደም ይጠጣሉ። ከዚህ ከሚገኙት ገንዘብ ለልጆቻቸው ወተት ይገዛሉ። ኬክ ያዛሉ። መዝናኛ ቦታ ይወስዳሉ። ዘማንዊ ቤትና መኪና ሸምተው ይኖራሉ።

See also  በራማ በኩል የኤርትራ ልዩ ሃይል ወደፊት ማጥቃት ወደ አድዋ ጉዞ ጀምሯል

መረጃ መስጠት አግባብነት ያለው ተግባር ቢሆንም አንድም ቀን መርምረውና ፈልፍለው የተዋጣለት ስራ ሲሰሩ አይታዩም። ጠጅ ቤት ቁጭ ብሎ ” ሰዎች ምን አሉ” የሚል ወሬ ለቃሚ አሜሪካ ስለገባና የሃላፊዎችን ስም ስለሚያውቅ እንደ አዋቂ በመጋበዝ ትርምስ ይፈጥራሉ። አንዳንዶቹ በመንግስትነት ሂሳብ ሲጫወቱ ኖረው፣ ሰዎች ሲገደሉ አደባባይ ሲዛበቱ ከርመው፣ ዛሬ ከሃረት ይልቅ ይዛበቱብናል። አጀንዳ እያመረቱ ያዋጉናል። ያፈራርሱናል። አጫፋሪው የድግምት ትምህርቱን ይነፋል። ከሁሉም አቅጣጫ ክልሉ ላይ የሚዘነበውን የጥፋት ዝናብ ሃይ ብሎ ከማስቆም ይልቅ በደመ ነፍስ መደገፍ የተሻለ አማራጭ የሆነላቸው አሉ።

ሰበት ሰነበት ” እየሱስ ጌታ ነው” የሚሉ ሚዲያ ከፍተውና ጠላትን ስፖንሰር አድርገው አገር እየስደበደቡ ነው። የማሪያምን ስምና የፈረደባትን ኦርቶዶክስ ምሽግ አድረገው ” ነጭ ነጯን” እያሉ በመሃይም አንደበት ሕዝብ ላይ እየተፉ ከህሳናት ደም ይገበያሉ። ዛሬ አቶ ሲሳይ ” ሃይል ጨመረን ካለተቆጣጠርነው ሕዝባችን ይጎዳል” ሲሉ የማይደነግጡ ከነማን ወገን ናቸው?

አማራ ክልል እንደ ክልል ከላይ ትህነግን የሚያክል ጠላት የተቀመጠለት ህዝብ ነው። በቤኒሻንጉል በኩል እየሆነ ያለው ሁሉ ተራ የብሄር ግጭት አድርጎ መመለከት አግባብ አይሆንም። ሰሜን ሸዋ የሆነውን እያየን ነው። በየቦታው የሚፈናቀሉት ወገኖች ጉዳይ አሁን ባለው ሁኔታ መቆሚያ የሚበጅለት አይመስልም። መንግስት ተደደም ተጠላም ያለውን ሃይል በየስፋራው በትኖ እየሰራ ነው። አማራም እንዲሁ ሃይሉን በታትኗል። በስመ ተቀናቃኝ ፓርቲ ውስጥ ውስጡን የሚርመጠመጡ ምን ያደርጉ እንደነበር ነበሳቸውን ያማረውና አቶ ምግባሩ በጨዋ ደንብ ነግረውን ነበር። እነዛን ምርጦች ያስበሉ ዛሬም ለአማራ ሕዝብ ተከራካሪ መስለው የክልሉን ሃይል እያዛሉ ነው።

በየስፋርው እየተሸጡ ቀውስ የሚፈጥሩትን ለመታደግ የክልሉ ሃይል መበተኑ ለዛሬ ጥቃት እንደዳረገው ሊታወቅ ይገባል። ስለሆነም የክልሉ ህዝብ፣ ምሁራን፣ ትንሽ ትልቁ ቅድሚያ ክልሉ እንዲረጋጋና ሰላም እንዲሰፍን ከየአቅጣጫው የተነሳበትን ቀውስ በድል እንዲያጠናቅቅ ልዩነት የሚባል ጉዳይን ” አልሰማም” ማለት ይኖርባቸዋል። በህጻናት ደም፣ በአዛውንቶች አስከሬን የሚሰራዉን ድራማ በማቆም አንድ ሆኖ መርዙን መንቀል ላይ ብቻ ትኩረት እንዲደረግ ግፊት ሊደረግ ይገባል። ዛሬ ክልሉን የሚመራው ፓርቲም ሆነ ተቀናቃኝ ነን የሚሉት / ዲቃላዎቹን ጨምሮ/ የሃሳብ ልዩነታቸውን አስወግደው ሕዝቡን በእውነትና በፍትህ ሊደርሱለት ይገባል።

See also  "በስራ እንጂ በአሉባልታ ስም-ማጥፋት ያደገ ሀገር የለም!" ወ/ሮ አዳነች አቤቤ

አቶ ሲሳይ ዳምጤ የህን ብለዋል ያድምጡ ከስር ያለውን ያንብቡ

ትናንትና ከፍተኛ ጉዳት የደረሰባትን አጣዬ ከተማን የጸጥታ ኃይሉ መቆጣጠሩንም የአማራ ክልል የሰላምና የሕዝብ ደኀንነት ጉዳዮች ቢሮ ኃላፊ ሲሳይ ዳምጤ አስታውቀዋል።

በአማራ ክልል ሰሜን ሸዋ ዞን በደረሰ ጥቃት ንጹሐን ተገድለዋል፣ አካል ጎድሏል፣ ሀብትና ንብረት ወድሟል። ዜጎች ቀያቸውን ለቀው ራሳቸውን ለማዳን ሸሽተዋል። በአካባቢው ከአሁን በፊት የተከሰተው ችግር በመረጋጋት ላይ ባለበት ወቅት ነው ችግሩ በድጋሜ ነው የተነሳው። የአማራ ሚዲያ ኮርፖሬሽንም ጉዳዩን እየተከታተለ ሲዘገብ መቆዬቱ ይታዎሳል።

በአማራ ክልል ስለተፈጠረው የጸጥታ ችግር የክልሉ የሰላምና ሕዝብ ደኀንነት ጉዳዮች ቢሮ ኃላፊ ሲሳይ ዳምጤ ለአሚኮ ማብራሪያ ሰጥተዋል። በማብራሪያቸውም በሰሜን ሸዋ ዞንና በኦሮሞ ብሔረሰብ አስተዳደር አዋሳኝ አካባቢ መጠነ ሰፊ የሆነ ችግር ተፈጥሯል ብለዋል። በአካባቢው ከአሁን በፊት ሲከሰቱ የነበሩ ችግሮችን ከሕዝብ ጋር በመሆን ሲፈቱ እንደቆዬ ያመላከቱት ኃላፊው ችግሩ በድጋሜ ማገርሸቱን ነው የተናገሩት።

ትናንት በአጣዬና በአካባቢው የኦነግ ሸኔ ጽንፈኛ ቡድን ከፍተኛ ጉዳት ማድረሱንም አመላክተዋል። በደረሰው ጉዳትም ንጹሐን ሞተዋል፣ አካል ጎድሏል፣ የመንግሥትና የሕዝብ ሀብትና ንብረትም ወድሟል ነው ያሉት። በአጣዬ በማረሚያ ቤት የነበሩ ታራሚዎች ከእስር እንዲወጡ ተደርጓል።

ከአጣዬ ባለፈ በካራቆሬ፣ በማጀቴ፣ በአንፆኪያ፣ በመኮይና በሸዋሮቢት ሕዝቡ በውጥረት ውስጥ ነው ያለው ብለዋል። በሰሜን ሸዋ ዞን ያለው ችግር እየከፋ የመጣና ሕፃናት፣ እናቶችና አዛውንቶች ጭምር በግፍ የተገደሉበት መሆኑንም ተናግረዋል።

የኦነግ ሸኔ ቡድን በሸዋሮቢት የሚገኙ ታራሚዎችን ለማስለቀቅ እንቅስቃሴ እያደረገ መሆኑን ያመላከቱት ኃላፊው በአካባቢው አሁንም የተኩስ ልውውጥ መኖሩን ነው የተናገሩት። የአማራ ልዩ ኃይል፣ የአካባቢው የጸጥታ መዋቅርና የፌዴራል የጸጥታ መዋቅር ችግሩን ለመፍታት ጥረት እያደረገ መሆኑንም አመላክተዋል።

የአማራ ክልል የጸጥታ መዋቅር ከፌዴራል የጸጥታ መዋቅር ጋር በቅንጅት እየሠራ መሆኑንም ተናግረዋል። አካባቢውን ለማረጋጋት እና አጥፊውን ቡድን ለሕግ ለማቅረብ ተጨማሪ የጸጥታ ኃይል ወደ ስፍራው መግባቱንም ተናግረዋል። የአካባቢውን ሚሊሻ በማደራጀት ከሌላው የጸጥታ ኃይል ጋር እንዲገባ እያደርግን ነውም ብለዋል። ከፍተኛ ጉዳት የደረሰባትን አጣዬ ከተማን የጸጥታ ኃይሉ መቆጣጠሩን አስታውቀዋል። በሸዋሮቢት ያለውን ችግር ለመቅረፍ የመከላከያ ሠራዊት ጥረት እያደረገ ነው ብለዋል።

See also  «ታክቲካዊ ማፈገፈግ ነው ... ተከበናል ከበባውን መስበር አልቻልንም» ዶ/ር ደብረፅዮን

የኦነግ ሸኔ ጽንፈኛ ቡድን የአማራን ሕዝብና መንግሥት ወደ አልተፈለገ አቅጣጫ ለመውሰድ እየሠራ መሆኑንም አመላክተዋል። ችግሩን የፈጠሩ፣ ያደራጁና የመሩ ለሕግ መቅረብ አለባቸው፤ ጽንፈኛውን ቡድን ከሕዝብ እየነጠሉ ለሕግ ማቅረብ ይገባልም ብለዋል።

በሌላ በኩል በጭልጋ አካባቢም የታጠቁ ኃይሎች በመከላከያ ሠራዊትና በአማራ ልዩ ኃይል ላይ ጥቃት በመፈፀም ችግር መፍጠራቸውን የተናገሩት ኃላፊው የክልሉና የፌዴራል የፀጥታ መዋቅር ሰላምን ለማረጋገጥ እየሠራ መሆኑን አስታውቀዋል። የአማራ ክልል ሕዝብ የሚሰጡትን አጀንዳዎች በሰከነ መንገድ በማዬት ከመንግሥት ጎን በመቆም ችግሮችን በጋራ እንዲፈታም ጥሪ አቅርበዋል።

አሚኮ ዘጋቢ:- ታርቆ ክንዴ.

Leave a Reply