Site icon ETHIO12.COM

ምርጫ ቦርድ፤ በእስር ላይ ያሉ የባልደራስ አመራሮች በዕጩነት መመዝገብ፤ በፍርድ ሂደታቸው ላይ ተጽእኖ ያሳድራል አለ

በቅድስት ሙላቱ 

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ፤ ባልደራስ ለእውነተኛ ዴሞክራሲ ፓርቲ (ባልደራስ) በከፍተኛ ፍርድ ቤት ላቀረበው ክስ ዛሬ ሰኞ መጋቢት 20 በችሎት ፊት ምላሽ ሰጠ። ቦርዱ ዛሬ ላስቻለው አንደኛ የምርጫ ጉዳዮች ችሎት በሰጠው ምላሽ በህግ ከለላ ስር ያሉት የባልደራስ ዕጩዎች ለምርጫ መመዝገብ የማይችሉባቸውን ሁለት ምክንያቶች አስረድቷል። 

የባልደራስ አመራሮቹ ለምርጫ በዕጩነት ቢመዘገቡ በቀጥታ ያለመከሰስ መብት ስለሚኖራቸው፤ በሌላ ችሎት እየታየ ባለው የተከሳሾቹ የፍርድ ክርክር ሂደት ላይ ተጽዕኖ ይኖረዋል ሲል ቦርዱ በዛሬው ችሎት መግለጹን የባልደራስ ፓርቲ ጠበቃ አቶ ሄኖክ አክሊሉ ለ“ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” ተናግረዋል። ምርጫ ቦርድ አመራሮቹ ለምርጫ እንዳይመዘገቡ “የኢትዮጵያ የምርጫ ህግ እና የምርጫ ቦርድ መመሪያ ይከለክላል” በሚል ተጨማሪ ምክንያት ማቅረቡንም አክለዋል። 

የባልደራስ ፓርቲ ሊቀመንበሩን እስክንድር ነጋን ጨምሮ በእስር ላይ የሚገኙ አራት አመራሮች ለመጪው ምርጫ በዕጩነት እንዲቀርቡ ያቀረበው ባለፈው የካቲት ወር ነበር። የአራቱ አመራሮች ዕጩነት በምርጫ ቦርድ ተቀባይነት ሳይገኝ መቅረቱን ተከትሎ፤ “ውሳኔው አግባብ አይደለም” በማለት ባልደራስ በያዝነው መጋቢት ወር ለከፍተኛ ፍርድ ቤት ይግባኝ ብሏል። ፓርቲው ይግባኙን የጠየቀው፤ “አመራሮቹ የመምረጥም ሆነ የመመረጥ መብታቸው በፍርድ ቤት ሳይከለከል፤ ምርጫ ቦርድ ራሱን እንደ ፍርድ ቤት በመቁጠር፤ በምርጫ ሂደቱ እንዳይሳተፉ ማድረጉ፤ ህጉን የሚቃረን ነው” በማለት ነበር። 

ምርጫ ቦርድ ይህ አይነቱ አሰራር “በከፍተኛ ወንጀል ተጠርጥረው ጉዳያቸው በፍርድ ቤት እየታየ ለሚገኙ እና በነፍስ ማጥፋት ጭምር ለተከሰሱ ሌሎች ተከሳሾችም በር ከፋች ነው” በሚል ጥያቄውን አለመቀበሉን በይፋ ማስታወቁ ይታወሳል። የቦርዱ ሰብሳቢ ብርቱካን ሚደቅሳ ባለፈው የካቲት ወር ከፖለቲካ ፓርቲዎች ጋር ባካሄዱት ስብሰባ ላይ እንደተናገሩት፤ በአንዳንድ ሀገራት በእስር ላይ ያሉ ግለሰቦች በምርጫ ለመወዳደር እንደሚፈቀድ ጠቅሰው፤ የኢትዮጵያ ህግ ግን ይህን እንደማያዝ አብራርተው ነበር።

በዛሬው ውሎው፤ የምርጫ ቦርድን ምላሽ ያደመጠው አንደኛ የምርጫ ጉዳዮች ችሎት፤ የባልደራስ ፓርቲ በጉዳዩ ላይ የመልስ መልስ እንዲሰጥ ለመጪው ረቡዕ መጋቢት 22 ቀጠሮ ሰጥቷል።

Source (ኢትዮጵያ ኢንሳይደር)

Exit mobile version