Site icon ETHIO12.COM

በትግራይ ክልል ያለውን የጸጥታ ሁኔታ ለማሻሻል ህብረተሰቡን ያሳተፈ ስራ እየተከናወነ መሆኑ ተገለፀ


በትግራይ ክልል ያለውን የፀጥታ ሁኔታ ለማሻሻል ህብረተሰቡን መሰረት ያደረጉ ስራዎች እየተሰሩ መሆናቸውን የክልሉ ጊዜያዊ አስተዳደር አስታወቀ።

ጊዜያዊ አስተዳደሩ በክልሉ ባለፉት ሶስት ወራት በክልሉ በተከናወኑት የፀጥታ ስራዎችን ዙሪያ ላለፉት ሁለት ቀናት ሲገመግም ቆይቷል።

የጊዚያዊ አስተዳደሩ ምክትል ስራ አስፈጻሚና የፀጥታ አስተዳደር ቢሮ ኃላፊ ኮሚሽነር ግርማይ ካህሳይ እንደገለጹት የፀጥታ ስራዎችን ለማሻሻል ህብረተሰቡን ባለቤት ማድረግ ያስፈልጋል።

“በክልሉ ያለው የፀጥታ ሁኔታ እየተሻሻለ ነው” ያሉት

ኮማንደሩ ባለፉት ሶስት ወራት በከተሞች ከነበረው የፖሊስ ሀይል 42 በመቶ እንዲሁም በማረሚያ ቤቶች ከነበሩት 58 በመቶ ወደ ስራ መግባታቸውን ተናግረዋል።

ፀጥታው በተረጋገጠባቸው አካባቢዎች የማህበረሰብ አቀፍ ፖሊሲ(ኮሚኒቲ ፖሊሲንግ) እንዲደራጁ እየተደረገ መሆኑን ኮማንደር ግርማይ ጠቅሰው ለአብነትም በመቀሌ፣ ማይጨው፣በአዲግራትና በአክሱም ከተሞች ወጣቶችን በማደራጀት አካባቢያቸውን እንዲጠብቁ እየተደረገ መሆኑን አስረድተዋል።

የደቡብ ምስራቅ ዞን ፖሊሲ አዛዥ ተወካይ ኮማንደር አፍቱ ገብረመስቀል እስካሁን በዞኑ ከነበሩት 500 የሚደርሱ የፖሊስ አባላት 227 ወደ ስራ እንዲመለሱ መደረጉንና በየቀበሌው ህብረተሰቡን በማሳተፍ አካባቢውን እንዲጠብቅ እየተደረገ መሆኑን ገልጸዋል።

እስከ አሁን በወረዳው የተፈፀሙ ወንጀሎችና የትራፊክ አደጋዎችን የማጣራት ስራ እየተካሄደ መሆኑን ኮማንደር ሃፍቱ ጠቅሰው በእንደርታ ወረዳና በአዲጉደም ከተማ ማህበረሰብ አቀፍ ፖሊስ በማደራጀት ስራ መጀመሩን አስረድተዋል ።

የምስራቃዊ ዞን ኮማንድ ፖስት አባል ኮማንደር ብርሃነ ቢሆን በበኩላቸው በዞኑ ውስጥ በሚገኙ 18 ወረዳዎች ከነበሩት 936 የፖሊስ አባላት 357 ወደ ስራ በመግባትና ከህብረተሰቡ ጋር በመተባበር የአካባቢውን ፀጥታ እየጠበቁ መሆናቸውን ተናግረዋል ።

እስከ አሁንም በአዲግራትና በጋንታ አፈሹም ወረዳ የተሻለ የፀጥታ ስራ መከናወኑን አስረድተዋል።

ለሁለት ቀናት በተካሄደው በዚሁ ግምገማ የደቡባዊ፣ የምስራቃዊ፣ ደቡባዊ ምስራቅና ማአከላዊ ዞንና የመቀሌ ከተማ የፀጥታ አካላት የተሳተፉ ሲሆን ለቀጣይ ሶስት ወራት የሚቆይ የጋራ እቅድ ማውጣታቸውን ኢዜአ ዘግቧል።

Exit mobile version