በትግራይ ክልል የሰብዓዊ ድጋፍን ለማፋጠን የፀጥታ ሃይሉ ከሚመለከታቸው አካላት ጋር በልዩ ትኩረት እየሰራ መሆኑን የጦር ሃይሎች ጠቅላይ ኢታማዦር ሹም ጀኔራል ብርሃኑ ጁላ ገለጹ።
የኢፌዴሪ ጦር ሃይሎች ጠቅላይ ኢታማዦር ሹም ጀኔራል ብርሃኑ ጁላ ከዓለም ምግብ ፕሮግራም ኃላፊዎች ጋር በጽህፈት ቤታቸው ተወያይተዋል።
ከዓለም የምግብ ፕሮግራም ዋና ዳይሬክተር ዴቪድ ቤስሊይ አማካሪ ጋአቪን ግርምስታት፣ በፕሮግራሙ የኢትዮጵያ ዳይሬከተር ስቴቨን ዌር ኦማሞ እና የፕሮግራሙ የአስቸኳይ ጊዜ ማስተባበሪያ አማካሪ ማርክ ጎርደን ከኢታማዦር ሹሙ ጋር ባደረጉት ቆይታ በትግራይ የሰብዓዊ ድጋፍ አሰጣጥን በተመለከተ ተወያይተዋል።
የኢታማዦር ሹሙ ጽህፈት ቤት ለኢዜአ እንዳስታወቀው ሰራዊቱ ለድጋፍ ስራ ምቹ ሁኔታ መፍጠር የሚያስችል ኦፕሬሽን በማጠናቀቁ ነባራዊ ሁኔታው ህዝቡ ድጋፍ ማግኘት የሚችልበት እንዲሆን አድርጓል ብለዋል። በአሁኑ ወቅትም የፀጥታ ሀይሉ በከፍተኛ ትጋት ህዝቡን እየደገፈ መሆኑን አብራርተዋል።
የዓለም የምግብ ፕሮግራም ኃላፊዎችም በትግራይ ክልል የሰብዓዊ ድጋፍን ለማቅረብ የሚያስችል ምቹ ሁኔታ መኖሩን ተረድተው ከሚመለከታቸው አካላት ጋር በጋራ እንዲሰሩም ጥሪ አቅርበዋል።
የጦር ሃይሎች ጠቅላይ ኢታማዦር ሹሙ ጀኔራል ብርሃኑ ጁላ፤ በጥቅምት 24 ቀን 2013 ዓ.ም በአገር መከላከያ ሠራዊት የሰሜን ዕዝ ላይ የህወሃት አሸባሪ ቡድን የፈጸመው የተቀናጀ ጥቃት ለችግሩ መከሰት ዋነኛው መሆኑንም በዚሁ ወቅት አብራርተዋል።
ይህም የሰብዓዊ ድጋፍ በተሟላ መልኩ ለማቅረብ ለፈለጉ አካላት መሰናክል ሲፈጥር እንደነበርና ሁኔታውን ለመሻገር ሰራዊቱ ከፍተኛ ድጋፍ ሲያደርግ እንደነበር አስታውሰዋል።
በአሁኑ ወቅት የፌዴራልና የክልል ጸጥታ ሃይሎች ልዩ ትኩረት ሰጥተው እየተንቀሳቀሱ መሆኑን አመልክተው፤ የሰብአዊ ድጋፍ አቅርቦት የማድረግ ስራዎች እየተከናወኑና ለማቅረብም ምቹ ሁኔታ መኖሩንም አረጋግጠዋል።
ከጸጥታ ሃይሉ፣ ከትግራይ ክልል ጊዜያዊ አስተዳደር፣ ከሰላም ሚኒስቴር፣ ከአገር ውስጥና ከውጭ የሰብዓዊ ድጋፍ ከሚሰጡ አካላት የተውጣጣ ኮሚቴ ተቋቁሞ ስራዎችን በልዩ ትኩረት እያከናወነ መሆኑን አብራርተዋል።
ህግ ማስከበሩ ከተጠናቀቀ በኋላ በትግራይ ክልል የሰብዓዊ ድጋፍ የማድረግና የመልሶ ግንባታ ስራዎች መጀመራቸው ይታወቃል።
መንግስት ለትግራይ ክልል ህዝብ ሰብዓዊ ዕርዳታ ማቀረብ፣ የተጎዳ መሰረተ ልማት መጠገን እንዲሁም የፈረሰውን መንግስታዊ የአገልግሎት ለማስጀመር የሲቪል ሰርቪስ አደረጃጀት በማዋቀር ጊዜያዊ አስተዳደር አቋቁሞ ስራዎችን እያከነወነ መሆኑ ይታወቃል። via Ena