የትግራይ ህዝብ የሰላሙ፣ የህልውናው እና ደህንነቱ ዘብ እራሱ ህዝቡ ነው ሲሉ የትግራይ ጊዜያዊ አስተዳደር ዋና ስራ አስፈጻሚ ዶ/ር አብርሃም በላይ ገለፁ::

የትግራይ ጊዜያዊ አስተዳደር ዋና ስራ አስፈጻሚ ዶ/ር አብርሃም በላይ የባለፉት ሳምንታት የክልሉ የስራ ክንውኖች እና ቀጣይ አቅጣዎች ዙሪያ ማብራሪያ ሰጥተዋል::

በዚህም ባለፉት ሁለት ሳምንታት በትግራይ ህዝብ ተስፋ ሰጪና የሚያድግ ድጋፍ ተጨምሮበት በቀዳሚነት የጠቅላላ ሁኔታዎች ሰፊ ቅኝትና አስቸኳይ ጉዳዮችን የመለየትና መፍትሔ የመስጠት ስራዎችን በማስቀደም ወደ ተግባራዊ እንቅስቃሴ ተገብቷል ነው ያሉት።

ዋና ስራ አስፈፃሚው በዚህ የስራ አፈፃፀም ሒደትም አንገብጋቢ የሚባሉ ህይወት አድን የድጋፍ ስራዎች ተከናውነዋል ብለዋል፡፡

ከፌደራል መንግስት ጋር በመነጋገርም የህግና የአስተዳደራዊ ጉዳዮችን የተመለከቱ አሰራሮችን ማሻሻል፤ እንዲሁም በትግራይ ፈጣን ሰላምና ፀጥታን ማስፈን በሚያስችሉ ጉልህ እርምጃዎች ላይ ከሚመለከታቸው አካላት ጋር መነጋገርን ጨምሮ፣ ከመጪው የክረምት ግዜ መጀመር አስቀድሞ ዜጎች በአስቸኳይ እንዲቋቋሙና ወደ እርሻ ስራ እንዲመለሱና ትኩረት ሰጥቶ በመስራት ላይ ይገኛል።

በዚህ አግባብ በጊዜያዊ አስተዳደሩ ከተወሰዱ ጉልህ የህግና ፀጥታ ነክ ጉዳዮች መሐከል አንዱና ዋንኛው፣ በትግራይ ታውጆ የቆየውና ለስድስት ወራት በስራ ላይ ፀንቶ የቆየውን የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅና የተቋቋመውን የኮማንድ ፖስት ለተጨማሪ ግዜ ማራዘም ሳያስፈልግ እንዲቆም፣ ህዝቡ በራሱ ሰላምና ፀጥታ ማስከበር ሒደት ጉዳይ የላቀ ተሳትፎ እንዲኖረው የሚያስችሉ እድሎችን ማመቻቸት ነው።

በትግራይ የተለያዮ ቦታዎች የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁን ተከትሎ የተላለፈው የሰአት እላፊ ገደብም ደረጃ በደረጃ እየታየ የሚሻሻልና ሙሉ በሙሉም የማንሳት ዝግጅቶችም በጊዜያዊ አስተዳድሩ አየተደረጉ ነው፡፡

ስለሆነም ይህን ከወዲሁ ግምት ውስጥ በማስገባት ዜጎች በትእግስት ሁኔታዎችንና ተጨማሪ መግለጫዎችን እንዲከታተሉ ጊዜያዊ አስተዳድሩ በአክብሮት ያስታውቃል ነው ያሉት።

ይህ የፌደራል መንግስትና የትግራይ ጊዜያዊ አስተዳደር በጎ ጅምር፣ በተለይ በከተሞችና አንዳንድ ኦፐሬሽኖች ከሚከናወኑባቸው የተለዮ አካባቢዎች ውጪ፣ ህዝቡ ፀጥታና ሰላሙን በየአካባቢው ከሚገኙ የመከላከያ ማዘዢያ ጣብያዎች ጋር በመቀናጀት በራሱ ለማስከበር የሚችል መሆኑን በተግባር እያስመሰከረ ያለ መሆኑን ከግምት ውስጥ ያስገባ ነው፡፡

በሒደትም ክልሉን ወደ ተሻለ መረጋጋት ለመመለስ በሚደረግ ጥረት ውስጥ የህዝቡን የማይተካ ሚና ሙሉ እውቅና በመስጠት ነው።

የትግራይ ጊዜያዊ አስተዳደር ዋና አላማ፣ በትግራይ ቅቡልነት ያለው ለህገ-መንግስቱና ከዚያ መለስ ላሉ ህጋዊ ስርአቶችን ሳይሸራርፍ የመተግበር ግዴታውን የሚወጣ፣ ህጋዊ አስተዳደርን በህጋዊ መንገድ ለማምጣት አመቺ መደላደልን መፈጠሩን ማረጋገጥ መሆኑን ጠቁመዋል፡፡

በመሆኑም ይህንን በጎ አጋጣሚ በመጠቀም የጊዜያዊ አስተዳደሩን ስራ ህዝቡ በተለይም ወጣቱ በአንክሮ እንዲገነዘበውና ክልሉን በዘላቂነት ለማረጋጋት የሚደረገውን ጥረት በማገዝ ረገድም የበኩሉን ድርሻ ሊያበረክት እንደሚገባ መገንዘብ ያስፈልጋል።

በቀጣይም በክልሉ የሰብአዊ ድጋፍና የእርዳታ ስራዎችን በመላው ትግራይ ለማድረስ የሚያስችሉ ሰፊ ስራዎችን ለመስራት ከሚመለከታቸው አካላት ጋር በመተባበር አየተሰራ ነው፡፡

በመሆኑም፣ በከተማ ሆነ በገጠር ህዝቡ ወደተለመደው የእለት-ተእለት ተግባሩ ለመመለስ የሚያግዙ ጥረቶችም ተጠናክረው ቀጥለዋል፡፡

ከዚህ በተጨማሪም ጠቃሚ ጉልህ እርምጃዎች በመጪዎቹ ቀናት እንደሚከናወኑ ከወዲሁ እያሳወቅን፣ ህዝቡ በአጠቃላይ የሰላም የመረጋጋት የሰብአዊ እርዳታና የህይወት አድን ዘመቻ ስራዎችን እንዲሁም የመልሶ ግንባታ ሙከራዎችን በማሳካት ረገድ የበኩሉን ድርሻ እንዲወጣ አሳስበዋል።

በክልሉ በምርጫ የሚመሰረት ህጋዊ የክልል መንግስት እስኪቋቋም፣ በህዝባችን የሚደርሰውን ችግር ካለበት በላይ እንዳይቀጥል፤ እንዲሁም ህዝባችን ዓመታትን የሚሻገር ችግር: ቸነፈር እንዳያጋጥመውና ወደ ቀድሞ ሰላሙ በኣስቸኳይ እንዲመለስ ለማድረግ በሞያቸውና ልምዳቸው ህዝባቸውን ለማገልገል ዝግጁ የሆኑ በህዝብ የተመረጡ ወጣቶች የግዝያዊ ኣስተዳደሩ ኣካል ሆነው እያገለገሉ ነው ብለዋል::

ያም ሆኖ ግን፣ የጤና ኣቅርቦት እንዲያድግ ቁሳቁስ የሚያዳርሱ፣ ሰብኣዊ ድጋፍና የእርሻ ግብኣት ለህዝባችን ለማድረስ ሌት-ተቀን ደከመን የማይሉ፣ የመንግስት ኣገልግሎት ለማስጀመር ላይ ታች የሚዳክሩ፣ እርዳታና ድጋፎችን ተሸክመው ገጠር ከተማ ሳይለዩ ለማዳረስ የሚደክሙ ወጣቶች፣ ማዳበርያና ምርጥ ዘር ለገብሬ ለማዳረስ የማይሰለቹ ወጣቶች ሆን ተብሎ በታጣቂዎች ሲገደሉ ማየት/መስማት ከጀመርን ወራቶች ተቆጥሯል ብለዋል::

ዶክተር አብርሃም እነዚህ ወጣቶች፣ ታጥቀው የሚዋጉ ሳይሆን የሚራብ ወገን እንዳይኖር ደፋ ቀና ብለው የሚያጠግቡ፣ ነፍሰ-ጡር እናቶችና እህቶች በህክምና እጥረት እንዳይሞቱ የጤና ኣቅርቦት እንዲኖር የሚጥሩ፣ ሆስፒታሎችና ጤና ኬላዎች ወደ ስራ እንዲመለሱ ሌት-ተቀን የሚሰሩ፣ ህዝብ ተገቢ የሆነ የመንግስት ግልጋሎት እንዲያገኝ የሚሰሩ፣ የክልላችን ገበሬ የእርሻ ስራውን ሳይከውን የክረምት ወቅት እንዳይደርስበት ግብኣት የሚያዳርሱ ናቸው::

እንግዲህ እነዚህ የየትኛውም የፖለቲካ ፖርቲ ውግንና የሌላቸው የህዝብ ልጆች፣ እውቀታቸውን እና ልምዳቸውን ይዘው በቁርጥ ቀን ህዝባቸውን ለማገልገል ከህዝባቸው ጎን የቆሙ ናቸው::

ስለሆነም፣ እነዚህ በቂ የፀጥታ ሃይል ባልተደራጀበትና በመጥፎ ጊዜ የህዝባቸውን ችግር ለመፍታትና ለማገልገል በህዝብ የተመረጡ ምሁራን ተጋሩ መሆናቸውን በመረዳት ደህንንታቸውን በማረጋገጥ ረገድ የሁሉም ትግራዋይ ሃላፊነት መሆኑ ሊታወቅ እንደሚገባ ገልፀዋል ::

በትግራይ ክልል ሁሉን ያሳተፈ፣ ሰላማዊ አስተዳደር ለማረጋገጥ በቅርቡ ላቀረቡት ጥሪ፣ ከትግራይ ህዝብና ከመላው የሃገራችን ህዝቦች፣ እንዲሁም አንዳንድ የአለም አቀፍ ድርጅቶችና የማህበረሰብ አባላት ለተደረገው ድጋፍ ምስጋና አቅርበዋል። via – ENA

Leave a Reply