Site icon ETHIO12.COM

ከመጪው አርብ ጀምሮ ሃገር አቀፍ የጸሎትና ምህላ መርሃ ግብር ሊጀመር ነው


ከመጪው አርብ ጀምሮ ሃገር አቀፍ የጸሎትና ምህላ መርሃ ግብር ሊጀመር መሆኑን የኢትዮጵያ የሃይማኖት ተቋማት ጉባኤ ገለጸ፡፡

ጉባኤው ዛሬ ለጋዜጠኞች በሰጠው መግለጫ እንደገለጸው ወቅታዊ ሀገራዊ ጉዳይን፣ የኮቪድ 19 ወረርሽኝ መስፋፋትን፣ መጪው ሀገራዊ ምርጫንና ሌሎች ሀገራዊ ጉዳዮችን ምክንያት በማድረግ ሃገር አቀፍ የጸሎትና ምህላ መርሃ ግብሩ አስፈልጓል፡፡

መግለጫውን የሰጡት የጉባኤው ጠቅላይ ፀሀፊ ሊቀ ትጉሀን ቀሲስ ታጋይ ታደለ እንደገለጹት ፀሎትና ምህላ የሀይማኖተኞች ችግር መፍቻ ነው፤ ሀገራችንም ከመቼውም ጊዜ በላይ ወደ ፈጣሪ በመቅረበ በይቅርታና በንስሃ የሚመላለሱ ልጆች ያስፈልጓታል፡፡

የጸሎትና ምህላ መርሃ ግብሩ ሚያዝያ 7 ቀን 2013 ዓ.ም ከቀኑ 9 ሰዓት በኢትዮጵያ የሃይማኖት ተቋማት ጉባኤ የበላይ ጠባቂ የሚታወጅ ሲሆን፤ ጸሎትና ምህላው ከሚያዚያ 8 ቀን ጀምሮም ለተከታታይ ሰባት ቀናት ይቆያል፡፡ ሚያዝያ 15 ላይም የመዝጊያ መርሀ ግብር እንደሚኖር ጠቅላይ ፀሀፊው አስታውቀዋል፡፡

በመርሀ ግብሩ የመንግስት አመራሮች፣ ተፎካካሪ የፖለቲካ ፓርቲዎች፣ የሀገር ሽማግሌዎች እንዲሁም ታዋቂ ግለሰቦች ይሳተፋሉ ተብሎ ይጠበቃል ሲሉ ቀሲስ ታጋይ ገልፃዋል፡፡

በዳግማዊት ግርማ. (ኢ ፕ ድ)

Exit mobile version