Site icon ETHIO12.COM

እውነትን ዋጁ!ሰከን ብለን የጥፋት ኃይሎችን ብንመክት አይሻለንም?

(በንጉሴ መሸሻ (ዶ/ር))


መነጋገር/ክርክር በምክንያትና በእውነት ላይ ሲሆን ከህሊና ወቀሳ ያድነናል፤ እንደየአምልኮታችንም ደግሞ ፈጣሪ ደስ ይለዋል ብለን እናስባለን። ነገር ግን በቅጥፈት ሲሆን የህሊና ወቀሳ ውስጥ እንወድቃለን። በፈጣሪ ፍርድም ይፈርድብናል። ከዚህ አናመልጥም!

መከራከሪያችን በፍጹም እውነትና በንጽህና ሲሆን ህሊናን አይቆረቁረውም፤ ደስተኞችም እንሆናለን። እንደ አምልኮታችንም ፈጣሪ በኛ ደስ ይለዋል። ቅጥፈት ግን ለዘመናት ህሊናን ያሰቃየዋል፤ ለፈጣሪ ፍርድም ይዳርገናል!

ይሔን ሀሳብ እንድጽፍበት ያስገደደኝ ሰሞኑን በአጣዬ፣ በምዕራብ ወለጋና ቤንሻንጉል ጉምዝ የተከሰቱ ግጭቶችና የወገኖቻችን ሞትና የንብረት መውደም አሁንም ባዕዳን የኛኑ ወገን በመጠቀም የፍላጎታቸውን ለማሳከት፣ የዘመናት አኩይ ዓላማዎቻቸውን ለማርካት የሚዳክሩትንና የጥፋት ደም በማፍሰስ ሰይጣናዊ ህልማቸውን ለማሳካት ሲሉ ሃገራችንን ለመበተን የሚተጉ ኃይሎች ጽንፈኞችን ተጠቅመው እያባሉን እንደሆነ ስለተገነዘብኩ ነው። ይሔም አሁን እየሆነ ባለ እልቂትና ሀብት ማቃጠል እያሳዩን ስለሆነና በወገኖቻችን ዘንድ በማወቅም ይሁን ባለማወቅ እንዲሁም በቅጥረኛ ቋንቋዎቻችን በሚችሉ እኩያን የሚለጠፉ የፌስ ቡክ ጽሑፎችንና ቀረጸ ድምጽና ምስል በማየቴ ነው።

በአንድ በኩል ግጭቶቹን የብሔር ለማስመሰል ይጥራሉ። በሌላ መልኩ ደግሞ የሐይማኖት ሊያደርጉት ይፈልጋሉ። ለዚህ ማሳያ የሚሆኑት በቤንሻንጉል ጉምዝ ክልል የሚደረጉ ግጭቶች በአማራና በቤንሻንጉል መካካል የሚደረግ እንደሆነ የሚሰራ ሲሆን በወለጋ ደግሞ በኦሮሞና በአማራ መካከል በሚዘራ የጥላቻ ትርክት የተነሣ እርስ በእርስ ህዝባችን እንዳይተማመን የሚደረጉ ግድያዎች፤ ዘረፋዎች፣ ንብረት ማቃጠሎች፣ ወዘተ ከዚህ ጋር ቤተክርስቲያንን በማቃጠል የሚደረግ ነው። በሻሽመኔ ተሰቅሎ የተገደለው፣ እንዲሁም በቅርቡ በቻግኒ ተቀጥቅጦ የሞተው የጉምዝ ማህበረሰብ ተወላጅ ጉዳይ ልብ የሚሰብር ጉዳይ ሆኖ ሳለ እየተደረገ ያለው ግን የብሔር ጥላቻ ቀደሞ የተዘራውን ማቀጣጠል ነው። ይሄን ግን እንዴት እንረሣለን!?

የእስልምና ሐይማኖት ቤተ እምነት ሞጣ ላይ የተቃጠለውን እናስታውሰዋለን። የሐይማኖት ግጭትና አለመተማመኖች እንዲፈጠሩ የሚሸረበውን ሴራ አካል ነው! በአጣዬ የእስልምና ሐይማኖት ተከታይ ሰው ድምጽ ተቀረጾ የተለቀቀውም የሐይማኖት ጦርነት ለማስነሳት ነበር።

የእኛኑ ልዩነቶች በመጠቀም በኛ ውስጥ እንክርዳድ ዘርተው በማብቀል እንክርዳዱን ከንጹሁ ዘር መለየት እንዳንችል በሀሰተኛ ወሬዎችና አሉባልታዎች ተጠላልፈን እንድንወድቅ እየተጉ መሆናቸውን በምናስተውልበት ሁኔታ ውስጥ በመገኘታችን ነው።

ለወገናችን የሰላ ሀሳብ እንጂ የሰላ ጦር አያስፈልገውም። ጦር እንዲሰበቅብን እየሆነ ያለው ከጠላት (በአሁኑ ሰዓት በተለይ ከግብጽና ከምዕራቡ ዓለም) ሲሆን እነዚህ አካላት የቅርባችን ወዳጅ ሀገራት ሳይቀር በመጠቀም ቀን የጣለን ስለመሰላቸው ሊያጠፉን ቋምጠዋል።

ከዚህ በተጨማሪ በሦስተኛው ዓለም የያዙት የመንግስት ግልበጣ (regime change) እንደ ቶማስ ሣንካራ በቡርኪናፋሶ፣ አልተሳካላቸውም እንጂ በህዝባቸው በጣም ይወደዱ የነበሩትን በዚምባቡዌ ሮበርት ሙጋቤና የሞርጋን ሻንጋራይ የእሳቤ ልዩነቶች ከለላ አድርገው ከስልጣን በማስነሳት የነሱ ተላላኪ መንግስት ለማሰቀመጥ ያደረጉት እኩይ ተፅዕኖ፣ ጋዳፊን አምባገነን ነው በሚል ሰንካላ ምክንያት መሪያቸውን ህዝቡ እየወደደ ሀገሪቷን አውድመው ለተዳከመች ሊቢያ የዳረጓት እነማንና ከማን ጋር ተባብረው እንደሆነ የሚዘነጋ ነው?
በኢራቅስ ቢሆን የሰዳም ሁሴን ሞትና የኢራቅ መድቀቅ፣ የኢራንና የቱርክ ከምዕራቡ ዓለም ጋር የሚደረገው ግብግብ የምዕራቡን ኃያልነት ለማስቀጠል አይደል!? በኬንያ በእሁሩ ኬንያታና በስልጣን ተፎካካሪ በሆኑት ራዎል ኦዲንጋ መካካል በነበረ አለመግባባት የነሱ ይሁንታ ያለው መንግስት በቦታው ለማስቀመጥ ምዕራባዊያኑ ያደረጉት ክፉ ስራ፤ የውጭው ሚዲያ በሚነዛው የሀሰት ፕሮፖጋንዳ እንድንጠላቸው የተደረጉ የአፍሪካ መሪዎች እንዳሉ እሙን አይደል!? አምባገነን መሪዎች በማስባልና ስልጣን ላይ ብዙ ቆዩ በሚል ከስልጣናቸው እንዲወገዱ የተደረጉ የደሀው ዓለም መሪዎች ነገር ግን ሕዝባቸው የሚወዳቸው የነበሩ እልቁ መሳፍርት ናቸው። ለእነሱ ያልተመቹ ከሆኑና የማይመቹ ከመሰላቸው ደግሞ በመንግስት እንቀይራለን (regime change) በሚሉት መንግስታትና የእነሱ አስፈጻሚ በሚሆኑ መንግስታዊ ያልሆኑ አካላት በሚፈስ ገንዘብ ሲሆን ይሄም አኛኑ በእኛ በማባላት በሚሰሩና በዚህም እሳቤ የሚሰሩ የቀጥተኛ ያልሆነ ጦርነት/ኃይል (soft power) ተጠቃሚዎች የምዕራቡ ዓለም “የቀለም አብዮተኞች”፤ እንዲሁም የእጅ አዙር ጦርነት በመጠቀም እኛን ከኛ ጋር ያባላሉ፤ ከተቻለ ሊያጠፉን ያም ካልተቻለ ሊያዳክሙን በርትተው ይሰራሉ።

በሌላ መልኩ የውክልና ጦርነት(proxy war) እንዲፈጠር በማድረግ፤ አይዞህ ባይነታቸውን በመግለጽ (ትራምፕ ለግብጽ አለኝታነታቸውን እንደገለጹት)፦ በይፋ፤ አብዛኛውን ግዜ በህቡዕ በመስራት/በማድረግ ሀገርና መንግስት እንዲዳከም ይሰራሉ። ይሄም የጠቅላይ ሚኒስትራችንን በጎ ጅምር በአጭሩ ለማስቀረት ይደክማሉ። እነሱ ሿሚ እነሱ አንሺ በመሆን። ለዚህም በአሁኑ ግዜ ግብጽና ሱዳንን በመጠቀምና ሌሎች ጥቅማችን ተነካ የሚሉ የወስጥ አካላትን ጭምር በማሰለፍ የሚደረግ ነው።

አሁን ላይ በአባይ ግድብ ምክንያት የሁለቱን ሀገራት ማለትም ግብጽና ሱዳንን ነባራዊ ጥያቄ አስታኮ በመጠቀም ሀገር ማዳከምና ማፍረስ በእኛ ላይ እየተሰራብን ያለ ደባ መሆኑ እንዴት ይጠፋናል? የጁቡቲ መንግስት እንኳ በኛ ላይ እንዲነሳብን እየተሰራ መሆኑን የጁቡቲ መንግስት የቅርብ ግዜ ከኛው ሀገር ተነስቶ በእኛ ሀገር ውስጥ የሚቀረውን የአዋሽ ወንዝ የመጠቀም ጉዳይ ጋር የተነሣው ጥያቄ ምንጬ ከየት ነው!? የቅርብ ቀናት ትውስታ አይደለም ወይ!? ለዘመናት በወዳጅነት የኖርን ሕዝቦች ሆነን ሳለ ከኬንያ መንግስትና ሕዝብ ጋር እንድንጋጭ የተደረገብን የቅርብ ግዜ ሙከራስ እንዴት ተዘነጋን!?

ሱዳንን “ከአሸባሪነት ዝርዝር ውስጥ እናወጣሻለን” የሚሉ ቃለ ቡሪኬ በመስጠት ዘላቂ የሱዳን ሕዝብ የሚያረጋግጠውን የሕዳሴ ግድብ ከግብጽ ጋር በማበር እንድትቃወም የተደረገው ለሱዳን ተብሎ ነው? በሱዳን በኩል የነበረው የጦርነት መጎሰምና በአማራና በቤንሻንጉል ጉምዝ በኩል የሚደረጉ ትንኮሳዎች፣ የህዝቦች ዕልቂት አቀጣጣይና አይዞህ ባዮች ሩጫ፣ የአል ሲሲ ጁባ ደርሶ መመለስ፣ የአሜሪካና የእንግሊዝ ከፍተኛ ባለስልጣናት ጁባ፣ ካርቱም፣ ሞቋዲሾ፣ ጁቡቲና ናይሮቢ መሯሯጥ ለጽድቅ መስሎን ይሆን? ማነው የምስራቅ አፍሪካን አካባቢ፣ ቀይ ባህርንና ሕንድ ውቅያኖስን ለመቆጣጠር እየተሯሯጠ ያለው!?

ይሄ ሁሉ የኛ መፈራረስ ወይም መዳከም የሚያስደስታቸው ደግሞ በውስጥ ጉዳይዋ የተጠመደች ሀገር ስትሆን ወይም የተበታተነች ወይም የቁጭ ቀሉ መንግስት ያላት ኢትዮጵያ ስትኖር ብቻ ፍላጎታቸው ሊሳካላቸው እንደሚችል በብዙ እንደሚወጥኑልን ለኛ እንዴት ጠፋን!? ለኛ ቢጠፋን ግን ለነሱ የሚጠፋቸው ይመስላችኋል!?
ይህ በመሆኑም ቅጥረኛ የፌስቡክና የሌሎች ማህበራዊ ሚዲያ በመጠቀም እርስ በእርሳችን እንድንተላለቅ፣ እርስ በእርሳችን ጦር እንድንሰባበቅ የሚገፋፉ መልዕክቶችንና ምስሎችን በማህበራዊ ሚዲያ ሲለጥፉ (post ሲያደረጉ) ሌሎች ደግሞ የብሔርና የሐይማኖት ጽንፍ ይሰብካሉ።

በማንኛውም መልክ ቢሆን የሕዝባችን ሞት፣ ስቃይ፣ እንግልትና ንብረት መውደም እጅግ የሚያሳዝን ነው። በቅርቡና ሰሞኑን በአጣዬ፣ በቤንሻንጉል ጉምዝና በምዕራብ ወለጋ የተፈጠሩ ግጭቶችና ጥፋቶችና የዜግቻችን መሞት፣ ሀብትና ንብረት መቃጠል እጅግ የሚያሳዝነን ነው።

እውነታው ይሔ ሆኖ ሳለ አንዳንዶች ለሀገራቸው ክብር ሳይሆን ለክልፍልፍ ፍላጎታቸው ሲሉ የሀገርን ክብርና ህልውና አሳልፈው ይሳጣሉ። በዚህም “ውሻ” በቀደደው ጅብ ይገባል ሆኖብናል።

ሚዛን የማያነሱ ክርክሮችን ወይም መላምቶችን መስጠት የ’ቡና ጠጡ!’ ላይ የሚደረጉ ጫወታዎች፤ የስሜት መገለጫዎች፣ አሉባልታዎች፣ አልፎ ተርፎ ጎረቤታዊ ንትርኮችና ጥሎች ቡና ላይ የተለመዱ ናቸው። ግን ይሔ ለአደባባይ በማይመጥን ሁኔታ እንዴት ወደማህበራዊው ሚዲያ እናመጣዋለን!? ሰው ጤፉ መሆን አይሆንብንም!? ሌላው ቢቀርና የምዕራቡ ዕውቀት ቢቸግረን ወይ ባይገባን የእምነት አስተምህሮታችን የት ገባ!?

ቡናኮ እናቶቻቾን ሲጠጡ የቡናው ሰዓት አንኳ ለመዝናናትና ጠቃሚ ሀሳቦችን ለመለዋወጥ የመገናኛ ድልድይ (እንደ public sphere ) በመሆን የሚገለገሉበት ነው። ንትርክና ጥል እንኳን ቢፈጠር ምራቅ ዋጥ ያደረጉና በዕውቀት ይሁን በተሰሚነት የተሻሉትም ቢሆኑ በግሳጼ ጉዳዩን ያቃናሉ። አንዳንዴም ጉርብትናቸውን አስበው አውቀው በመተው በሌላም ግዜ አንተ/አንቺ “ተዉ/ተይ እንጂ” በሚሉ ድምጾች በመሸነፍም ይሁን በእፍረት የሚከሰቱ ችግሮችን በትዕግስትና በፍጹም አስተውሎት ያልፉታል። ይሄ ዕውቀትም ጽድቅም ነው እንጂ መሸነፍ ወይም መታበይ አይደለም። ይሄን ደግሞ ሁላችን ያለፍንበት ሕይወት ስለሆነ አይረሳንምና ነው። ታዲያ ማህበራዊ ሚዲያው የሕዝብ መገናኛ ድልድይ ከሆነ የአባቶቻችንና የእናቶቻችን ድንቅ ሕይወት እንዴት ጠፋን!?

በመሆኑም በማህበራዊ ሚዲያ ደረጃ ወጥተው የሚገለጹ ሀሳቦች ፍጹም ጥላቻ፣ ስድብ፣ መዘላለፍ እየሆኑ ስለሆነ የቡና ላይ የሚደረጉ ጨዎታዎች እንኳን የሚመጥኑ አይደሉም። ግን መሆን አይገባቸውም ነበር!

በእርግጥ የማህበራዊው ሚዲያ ዘመን ያፈራው ጥሩ የመገናኛ ቴክኖሎጂ ሆኖ ሳለና ብዙ ጠቀሜታዎች ቢኖሩትም በእኛ በኩል በዕኩይ መልኩ መጠቀሙ ሳይበረታብን አልቀረም። ይሄውም ጥላቻ በመሰበክ፣ ወገንተኛና ሰፈርተኛ በመሆን የሰፈራችንን ሰው ብቻ በጎ ሌላውን መጥፎ፣ የሰፈራችንን ሰው ብቻ ጎበዝ ሌላውን ማንኳሰስ፣ የኛ አለመረዳት መገለጫዎች መሆን የለበትም። ከአፍ የሚወጣ የጭንቅላት ሙሉነትና ባዶነት ይናገራልና!

በአንደንድ ሰዎች የሰሞኑ ጦርነቶችና ግጭቶችቱ በኛ መሪዎች እያታወቀ ነው እየተደረገ ያለው የሚሉ ሀሳቦች ይቀርባሉ። እነዚህ ደግሞ መሠረተቢስ የሚሆኑ መላምቶች ናቸው።

ቆይ እስቲ ሀገር የሚያስተዳድር አካል ምን ሆንኩ ብሎ በህዝብ እልቂት ላይ እጁ ይኖራል ብለን እናስባለን? ስልጣን አሸንፎ ለሚይዘው አካል ከሁለትና ሦስት ወራት ያልዘለለ ግዜ ብቻ ቀርቶ ባለበትና ገዢው ፓርቲ አሁን ያለሁበት የስልጣን ግዜ በህዝብ ድምፅ እንዳልቀጥል ከተደረኩና ከስልጣኔን ከተሸነፍኩ ስልጣኔን በሰላማዊ ሁኔታ አስረክባለሁ እያለ አሁን ያለው ግጭት ውስጥ ምን ሆኖ እጁ ይኖራል ተብሎ ይታሰባል?

ሁለት ወንድማማቾች በትንሽ ነገር ሲጣሉ/ እንዲጣሉ ምክንያት የሆነው አካል ለመጠቀም የፈለገውን ለማሳካት ብቸኛው መንገድ መቅጠፍ ነው። ግርግር መፍጠር ነው። ግርግር ለሌባ ይመቻልና። ይሔውም በሚፈጥረው ግጭት ሌባና ቀጣፊው በመሐል ይገባል። ታዲያ ይሄ እንዴት ይጠፋናል!?

በግብፅ እየታገዘ ሀገር የሚያፈርስ ሀይል እያለና ኢትዮጵያን ወደማያባራ ግጭት ውስጥ ገብታ የግብጽ አላማ እንዲሳካ የሚፈልግ ኃይል የጦር መሣሪያ አሳታጥቆ፣ ገንዘብ ረጭቶ በትህነግ ፊታውራሪነት አልሳካ ያለውን ሀገር የማፍረስ ሴራ በቤንሻንጉል ጉሙዝ ፣ በምዕራብ ወለጋ፣ በአጣዬና ሌሎች ቀድሞ ለግጭት ስስ የሆኑ ቦታዎችን በመለየት፣ ምቹ ሁኔታዎችን በመፍጠርና በማመቻቸት የቀሩ ርዝራዥ ጥቅመኞችን በመጠቀም እንደሚሰራ ለምን ለአፍታ እንኳ ይዘነጋናል!?

ሌላው አባይ ግድብ ተገንብቶ ቢያልቅ ኢትዮጵያ በአካባቢው ኃያል ሀገር ልትሆን ነው ብለው በስጋት የተዋጡ የሩቅ አገራትና ግብጽ የውሀ ሙሌቱን ለመስቆም የማያደርጉት ምን ነገርስ ይኖራል!? ለእነሱ እኩይ ሴራቸው ምቹ ይሆናል ብለው በሚገምቱት የሐይማኖት ግጭት በማስመሰል በብሔር ጉዳዮች፣ በዕርዳታ ጫና፣ ወደፊት የምናየው ሆኖ በማዕቀብ ጭምር ዝም እንድንል በማድረግ፣ ወገን ላይ የጥፋት እጃቸውን የሚሰነዝሩ ራዝራዥ የጥፋት ኃይሎች (የህወሓትና የኦነግ ሸኔ) በመጠቀም እንደሚሰሩ እንዴት ተዘነጋን!?

ሰሞኑን በማህበራዊ ሚዲያ የሚለቀቁ ግጭትን የማራገብ ስራዎች ሐይማኖታዊ ለማስመሰል በሙስሊም ጦረኛ የሚነገሩ ቀረጸ ድምጾች የተለቀቀበት ዓላማው በአካባቢው የሐይማኖት ጦርነት ለማስነሳት የሚደረግ ደባ መሆኑ ከኛ እንዴት የተደበቀ ሚስጢር ይሆንብናል!?

የህወሓትም ሆኑ የኦነግ በሀሳብ የተሸነፉ ኃይሎች “እኔ ከሞትኩ ሰርዶ አይብቀል” ቢሂል ገና መች አብቅቶ ነው!? ይሄን ዛሬ ላይ ግጭቶች ተፈጥረው የአንዱ ብሔር ወገን ሲጎዳ ህወሓት በቀደደልን የብሔር እይታ ብቻ ተሸብበን ትልቋን ሀገር ረስተን አንዳችን በአንዳችን ላይ እልቂት የምንጠራው እንዴት ቢጠፋን ነው!? ይሄስ ለማንስ ይበጃል!? “ሞኝ ሲጃጃል ዕቃ ይፈጃል!” አይሆንብንም!?

“ለህወሓት ያልሆነች ኢትዮጵያ” ትፈረስ ከሚሉ ኃይሎችና እነሱ መቀመቅ ይውደቁና “ኢትዮጲያ ትውደቅ ” Ethiopia down down!” የሚሉ መፈክሮችን በህወሓት በሚርጭላቸው የእናት ሀገር ከሀዲዎች ሀገራችንን እንድትዋረድ ሀገር ስትሰደብ የሰማነው አደጉ በተባሉት ሀገሮችም ውስጥም አይደል!? በእነዚሁ ሀገራትስ ቢሆን የአገራችንን ውድቀት ለማየት የሚፈልጉ የሉም የሚያሳብል ነገር ምን አለ!? መንግስታዊ ያልሆኑ ድርጅቶች ጭምር፤ በእርግጥ ይሄን ያደርጋሉ ባይባልም በስለላ ስራና መረጃ በማቀበል ስራስ የተጠመዱትስ ስንት ናቸው? የምዕራቡ ዓለም ፍላጎት ማሳኪያዎች ጭምር አይደሉም፤ ያመጡትን እርዳታ ወይም ገንዘብ በአብዛኛው መልሰው ለደሀው ሳይደርስ የአላማቸው ማሳኪያና የቡድኖች ማበልጸጊያና እኩይ ስራ ማስፈጸሚያስ አልሆኑም!? ወገን ምነው ይሔ ጠፋን!?

አልፎ ተርፎም የውስጥ ችግሮቻችንን በማራገብ ወደማያባራ ጦርነት ለመክተት እንደሚሰራ ከሶሪያ፣ ከየመን፣ ከሊቢያ፣ ከቀድሞዋ በርማ ከአሁኗ ማይናማር ልናውቅበት አይገባም!? የቀድሞው እንዳለ ሆኖ በፀጥታው ምክር ቤት በቅርቡ የተደረገብን ጫና የምንረሳው ነው? ሱዳን በሀገራችን ላያ ያደረገችውን የድንበር ወረራ ጦርነት ዝም ብሎ ሲያበቃ የሀገር ሉዓላዊነት ጉዳያችን ላይ ሲሆን ደግሞ ትህነግን ከሞት በመታደግ (ለምዕራቡ ጥቅም ሲባል) የጦርነት ቀጠና ሊያደርጉን የሚተጉት ለማን ብለው ነው? እርዳታ ለመስጠት መግቢያ መንገድ አጣን በሚል ከበሮ የደለቁ የምዕራቡ ዓለምና የእነሱ ፍላጎት አስፈጻሚ የሆኑት ከ36 የሚበልጡ የውጭ መንግስታዊ ያልሆኑ ድርጅቶች ለትግራይ ህዝብ ምን አደረጉለት!? እዚህ ግባ የሚባልም አይደለም፤ መንግስት ችግሩን በአብዛኛው እየተወጣው ሆነ እንጂ። ትርፉ ትዝብት ነው እንጂ! ይሄ ጬኸት ብቻ ነው ይሆነው። የተደረገብን በደል ግን የሚረሳ አይደለም!

እኛ ግን ለነሱ ጥቅም ለማስጠበቅ አንዳንድ የባዕዳን ሀገራት ኢትዮጵያውያን ለማዳከም አልፎ ተርፎም ለማጥፋት ቅጥረኞችን በመቅጠር እንደሚያዘጋጁ እንዴት ጠፍቶን ነው አሁን ሀገራችን የገጠሟት ችግሮችን የአማራና የኦሮሞ ህዝቦችና አመራርሮች ችግር ተደርጎ የሚወሰደው? የአመራሮች ችግር እንዳለ ሆኖና እንዲፈታ ፖለቲካዊ ትግል ማድረጉ እንደተጠበቀ ሆኖ።

ከባዕዳን ሀገራት በሚመጣ ላሴሩልን ጥፋት ማቀጣጠያና እነሱ በጫሩልን እሳትና ግብጽ በምትጎነጉንልን ሴራ፤ እንዲሁም ከግብፅ አልፎ በሚቀባበሉት ጠላትነት ህዝባችን ጭድ እንዳያደርጉን በዕውቀት መነሳትና መምከር እንዲሁም መመከት አለብን! እኛን ሊያዳክሙን ወይም ሊያዳክሙን አስበው የውስጥ ችግሮቻችን በቀጣይ ምርጫ ልንፈታው ስለምንችል ቀድመን ግድቡን መሙላት ላይ ብንረባረብ። ይህ ምዕራፍ ወሳኝ ምዕራፍ ስለሆነ። ከእንግዲህ የኛ ፖለቲከኞችም ለባዕዳን የሚነገሩ መልዕክቶችን በጥንቃቄና በፍጹም አስተውሎት ቢያደርጉት!

ባዕዳንም ወደኛ በቀጥታ(hard power) ስለማይመጡብን ግጭት የሚያቀጣጥሉትም በርቀት ስለሆነ (remote control) በመሆኑና የሚያቀጣጥሉትን ግጭት ከቦታው በተገኙ ተላላኪና ቅጥረኞች እንደሆነ በመረዳት፣ ይሄም ዛሬ ላይ ነውጥ በመጠራት ስለሆነ ማስተዋሉ አይከፋም። ጉዳዩ ስልጣን የያዘው ፓርቲ ጉዳይ አየድርጎ ማየቱ ደግም ፍጹም የዋህነት ሳይሆን ጅልነት ይሆንብናል። ሰሞኑን በማህበራዊ ሚዲያ የሚቀርቡ ስሜት ቀስቃሽ በመቅረጫ ምስልና ድምጽ እየተቀረጹ የሚቀርቡ ህብረተሰቡን ስጋት ላይ የሚጥሉና የሚያሸብሩ አላማቸው ለህዝብ በማሰብ ሳይሆን የቆሰቆሱትን ግጭት መጠቀሚያ ለማድረግ ነው። ይሄ ደግሞ የግብጽና የአንዳንድ ምዕራባዊያን ፍላጎት ማሳኪያ ይሆናል። ይህ የሚሳካውም በኛው ውስጥ ባሉ አልጠግብ ባይ ቡድኖችና ግለሰቦች ሲሆን ይሄን እኩይ ሀሳባቸውን ተግባራዊ ለማድረግ የሚፈልጉት በባዕዳን ጠላቶቻችን በሚረጨው የገንዘብ፣ የስልትና ስትራቴጂ ድጋፍ እንዲሁም የዘመኑን የጦር መሣሪያዎችን በማስታጠቅ ህዝባችንን እያሰፈጁ በእኛ ውስጥ ያሉ አብሮነት ለማፍረስና የሀገር ማፍረስ ስራ እየተሰራ እንደሆነ ሰከን ብሎ ማሰብ አይገባንም?

ይሄ ምናልባትም የቀለም አብዮት በሚደግፉ ሀገራትም ጭምር ታግዞ ሀገር የማዳከም ሴራና ኃያል ኢትዮጲያ ሀገር እንዳትሆን የሚሰራ ደባ እንደሆነ ማሰቡ እንዴት ይጠፋናል? የውጭ ተመራማሪዎች ነን በሚል ሽፋን፤ የእርዳታ ሰጪ አካል ነን በሚሉ አካላት፣ በዕርዳታ ሰበብ በሚመጡ ተቀጢላዎችና የሀገር አጥፊ ስራዎችንም ለአፍታ ሊረሳን አይገባም። በሌላውም ክፍለ አህጉራትና ሀገራትም እየተደረገ ያለው ይሄ ነውና!

ማንም የሀገሩን ክፉ አይመኝም፤ ለሆዱ ሲል ለባዕዳን የሚገዛ ካልሆነ በቀር! የተፈጠሩና በቀጣይነት ግን ለሚፈጠሩ የዕልቂት ልቃቂቶችን መተርተርና ሀገር የማስቀጠል ኃላፊነት በተከሻችን ላይ እንደወደቀ ለአፍታ እንኳ መዘንጋት የለብንም።

በመጨረሻም በሰሞኑ እየተለቀቁ ያሉ የግጭትና የጦርነት ስብከት/ ጥሪ የሚያሳዩ ከማህበራዊ ሚዲያ ምንጮች ያገኘኃቸውን ምስሎች አያይዤ የለጠፍኩ ሲሆን “ሟች እኛ ገዳይ እኛ” መሆናችንን ሳንዘነጋ በተቀደደልን ተንኮል ተጠልፈን ሳንወድቅ ሀገራችንን በዚህ ወሳኝ ግዜ ልንታደግ ይገባናል!

የባዕዳንም ሴራና የተላላኪዎች ባዶ ህልም በኢትዮጰያ የቁርጥ ቀን ልጆች ይፈርሳል!

ሀገር ውስጥ የሚፈጠሩ ችግሮችን ሁሉ ከመንግስት ላይ መለጠፍ/ ማላከክ የባዕዳኖችና ጥቅማቸው የተነካባቸው የውስጥ ኃይሎች አንዱ ስውር ሴራ አካል ሊሆን ስለሚችል ነገሮችን በውል ማጤን ይገባል። እንዲሁም ለሚከሰቱ ችግሮች ሁሉ ጠቅላያችን ላይ መለጠፍ አይገባም።

Via walta – “እውነትን ዋጁ!” ተብለናልና!

Exit mobile version