Site icon ETHIO12.COM

በመዲናዋ ከ314 የግል አሰሪና ሰራተኛ ኤጀንሲዎች ባስመዘገቡት አድራሻ የተገኙት 150 ብቻ ናቸው- ጥናት

በአዲስ አበባ ውስጥ መቀመጫቸውን ባደረጉ 314 የግል አሰሪና ሰራተኛ ኤጀንሲዎች ላይ ሲደረግ የነበረው ጥናት ይፋ ሆነ፡፡

ጥናቱ የሰራተኛና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስትር ዶክተር ኤርጎጌ ተስፋዬ፣የኢትዮጵያ ሰራተኛና ማህበራዊ ኮንፌዴሬሽን ፕሬዚዳንት ካሳሁን ፎሎ እና የኢትዮጵያ አሰሪ ኮንፌዴሬሽን ፕሬዚዳንት ታደለ ይመር በጋራ በሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫ ነው ይፋ የሆነው፡፡

ጥናቱ ከሚመለከተው አካል ፍቃድን ሳያገኙ እየተበራከቱ የመጡና በዘርፉም ከጊዜ ወደ ጊዜ እየተወሳሰቡ የመጡ የህግ ጥሰቶችንና ወንጀሎችን መነሻ በመድረግ የተካሄደ መሆኑ የተገለፁ ሲሆን በአዲስ አበባ መቀመጫቸውን ባደረጉ 314 የግል አሰሪና ሰራተኛ ኤጀንሲዎች ላይ ትኩረት አድርጎ መካሄዱ ተነግሯል ።

በጥናቱ ወቅት ባስመዘገቡት አድራሻ የተገኙት 150 ኤጀንሲዎች ብቻ ሲሆኑ 71 የጥናት ቡድኑ ካስመዘገቡት አድራሻ ውጪ አፈላልጎ ያገኛቸው 28 የተዘጉ፣20 አድራሻ የቀየሩ፣ ዘጠኝ ምንም አይነት ቢሮ የሌላቸውና ቀሪዎቹ ቢሮ ለማሳየትም ፈቃደኛ ያልሆኑ ናቸው።

የጥናት ቡድኑ ባደረገው ምልከታም ከፌደራል ፖሊስ ብቻ የሙያ ፈቃድ ያላቸው 114 ከሰራተኛና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴር ብቻ የስራ ፈቃድ ያላቸው 122 ከንግድና ኢንዱስትሪ ሚኒስቴር የንግድ ፈቃድ ብቻ ያላቸው 151 ኤጀንሲዎች ሲሆኑ በአሰራሩ መሰረት ከሶስቱም ተቋማት ህጋዊ የሆነ የሙያ የስራ እና የንግድ ፈቃድ ኖሯቸዉ የሚሰሩ ኤጀንሲዎች ግን 88 ብቻ መሆናቸው በጥናቱ መረጋገጡ ተገልጿል ።

ከቢሮ አደረጃጀት አንፃርም 4 በመቶ ብቻ ተገቢው የቢሮ አደረጃጀት ኖሮት የሚሰራ ሲሆን 34በመቶ መካከለኛ 62በመቶ በዝቅተኛ ደረጃ ላይ ያሉ መሆኑን አረጋግጧል ።

የሰራተኛ ምልመላ፣የሰራተኛ ጥቅማ ጥቅም ማስከበር፣ የሰራተኛ ጉልበት ብዝበዛ ፣የክፍያ አፈፃፀም እና የመሳሰሉ አሰራሮችም በጥናቱ በዝርዝር ትኩረት የተደረገባቸው ሲሆን መሟላት ያለባቸውን በአግባቡ አሟልተው እየሰሩ ያሉት ግን በጣም ጥቂቶቹ መሆኑ ተነግሯል ።

ይህንን ጥናት መነሻ በማድረግም ውሳኔዎች እንዲተላለፉ መደገሩ ተገልጿል፡፡

በዚህም 144 ኤጀንሲዎች ፈቃዳቸውን መልሰው ከዘርፉ እንድወጡ፣ 71ኤጀንሲዎች ከእንግዲህ በዘርፉ ተሰማርቶ ለመስራት የሚፈልግ ከ3ቱ ተቋማት ፈቃድ ማግኘት እንደሚኖርበትና ሌሎች ውሳኔዎች የተላለፉ ሲሆን ይህም ተግባራዊ የሚደረገው ከአንድ ወር በኋላ መሆኑ ተገልጿል ።

በትዝታ ደሳለኝ via FBC

Exit mobile version