Site icon ETHIO12.COM

“በአዲስ አበባ የመኖሪያ ቤት በአንድ ጠባብ ቤት ውስጥ ከ6 እስከ 7 ሰው ይኖራል”

ግልጽ የሆነ የከተሞች ፖሊሲ አለመኖር ከከተሞች ዕድገት ጋር የሚመጡ ችግሮችን ለመፍታት አስቸጋሪ እንዳደረገው ተጠቆመ በአዲስ አበባ የመኖሪያ ቤት እጥረት ከፍተኛ በመሆኑ በአንድ ጠባብ ቤት ውስጥ ከ6 እስከ 7 ሰው ይኖራል።

በኢትዮጵያ ግልጽ የሆነ የከተሞች ፖሊሲ አለመኖሩ ከከተሞች ዕድገት ጋር ተያይዘው የሚመጡ ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ችግሮችን መፍታት አስቸጋሪ እንዳደረገው በመለስ ዜናዊ አመራር አካዳሚ የተጠናው ጥናት አመለከተ።

“የከተሜነትና የኢኮኖሚ ዕድገት” በሚል ርዕስ በአካዳሚው ሰሞኑን ጥናታዊ ጽሑፍ ያቀረቡት ዶክተር አወቀ አሸናፊ እንዳስታወቁት፤ ኢትዮጵያ ግልጽ የሆነ የከተሞች ፖሊሲ የሌላት በመሆኑ ከከተሞች ዕድገት ጋር ተያይዘው የሚመጡ ዘርፈ ብዙ ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ችግሮች ተጋላጭ ሆናለች። ከከተሞቿ የምታገኘው ጥቅምም ከሰሃራ በታች ከሚገኙ አገሮች ጋር ሲነጻጸር በጣም ዝቅተኛ ነው።

ዓለም ባንክ እ.ኤ.አ 2020 ባጠናዉ ጥናት በዓለም ደረጃ የከተማ ነዋሪ ሥራ አጥነት ቁጥር 15 በመቶ ነው ፤ በአዲስ አበባ ግን የሥራ አጥነት ቁጥር 23 ነጥብ 5 በመቶ ነው። በሥራ ዕድል ማጣት ምክንያት አብዛኞቹ ለመኖር ሲሉ ተገደው ወደ ጎዳና ተዳዳሪነት፣ ሴተኛ አዳሪነት እንዲሁም በተለያየ የወንጀል ድርጊቶች ይሳተፋሉ ብለዋል።

የጎዳና ተዳዳሪዎችና የሴተኛ አዳሪዎች ቁጥር መበራከት ከሥራ አጥነት ጋር ቀጥተኛ ግንኙነት እንዳለው ያመለከቱት ዶክተር አወቀ ፣ ሌሎች ተያያዥ ጉዳዮች ቢኖሩም በከተሞች የወንጀል ድርጊት መበራከትም የሥራ አጥነት ውጤት እንደሆነ አስታውቀዋል።

“የተጠቀሱት ችግሮች እንዳሉ ሆኖ ወደ ከተማው የሚደረገው ፍልሰት ከጊዜ ወደ ጊዜ እየጨረ ይገኛል። አሁን ባለው ነባራዊ ሁኔታ በከተሞች በተለይ በአዲስ አበባ የመኖሪያ ቤት እጥረት ከፍተኛ በመሆኑ በአንድ ጠባብ ቤት ውስጥ ከ6 እስከ 7 ሰው ይኖራል። አብዛኛው ሰው 70 እስከ 80 በመቶ የሚሆነው ደረጃቸውን ያለጠበቁ ከጭቃ በተሠራ ቤት ውስጥ ይኖራሉ። ይህ ደግሞ ይቅር በዓለም ከሰሐራ በታች ከሚገኙ አገሮች ጋር ሲተያይ ዝቅተኛ ነው”ብለዋል።. Via ENA

Exit mobile version