Site icon ETHIO12.COM

በዘጠኝ ወራት ዉስጥ ከቀረቡ 34,117 የምርመራ መዛግብት ውስጥ 33,027ቱ መዛግብት የተለያዩ ዉሳኔዎች አግኝተዋል”

ጠቅላይ ዐቃቤ ህግ የኢ.ፌ.ዴ.ሪ ጠቅላይ ዐቃቤ ህግ የ2013 በጀት ዓመት የዘጠኝ ወራት የእቅድ አፈፃፀም ግምገማዉን የኢፌዴሪ ጠቅላይ ዐቃቤ ህግ ዶክተር ጌዲዬን ጢሞቲዎስን ጨምሮ ምክትል ጠቅላይ ዐቃቤ ህጎች፣ የተቋሙ መካከለኛ አመራሮች በተገኙበት በዛሬዉ እለት አካሂዷል። የእቅድ አፈፃፀም ሪፖርቱን በኢ.ፌ.ዴ.ሪ ጠቅላይ ዐቃቤ ህግ እቅድ ፣ ፕሮጀክትና በጀት ክትትልና ግምገማ ዳ/ት ዳይሬክተር አቶ ደሳለኝ መንግስቴ አቅርበዋል፡፡

በዘጠኝ ወራት ዉስጥ በአጠቃላይ 40,564 የክርክር መዛግብት የቀረቡ ሲሆን ከነዚህም ዉስጥ በፍርድ ቤት ዉሳኔ ያገኘት 10,957 መዛግብት ናቸው፡፡ ከእነኚህ ውሳኔ ካገኘ መዛግብት መካከል 10,476 መዛግብት ላይ ዐቃቤ ህግ ጥፋተኛ ያስባለ ሲሆን ይህም ከመዛግብት አንፃር የዐቃቤ ህግ የመርታት ምጣኔን በ95.6 % እንዲደርስ አስችሎታል፡፡

የምርመራ መዛግብት አፈጻጸም በተመለከተ በድምሩ 34,117 መዛግብት በሁሉም የወንጀል አይነቶች በፖሊስ ምርመራቸው ተጣርተው የቀረቡ ሲሆን ከእነኚህ መዛግብት ውስጥ በ 33,027 መዛግብት ላይ የተለያዩ ውሳኔዎች በዐቃብያነ ሕግ የተሰጠ ሲሆን የማጥራት ምጣኔ 96.8% ደርሷል፡፡በወንጀል ክርክር ሂደት ተከሳሾች ፍርድ ቤት እንዲቀርቡ በማድረግ ተከሳሾች ባለመቅረብ የሚቋረጡ መዛግብትን አፈፃፀም ከ10% እንዳይበልጥ ለማድረግ ታቅዶ ከአጠቃላዩ 40,564 የክርክር መዛግብት ዉስጥ 7,141 መዛግብት የተቋረጡ ሲሆን አፈፃፀሙንም ከታቀደው እቅድ አንፃር አናሳ አንዲሆን አድርጎታል።

በሌላ በኩል ምስክር ባለመቅረብ የሚቋረጡ መዛግብት አፈፃፀም ከ5% እንዳይበልጥ ለማድረግ ታቅዶ በተሰራዉ ስራ በዘጠኝ ወራት ዉስጥ የነበረዉ አፈፃፀም የተሻለ እንደሆነ በገለጻው ተነስቷል፡፡ልዩ ትኩረት ከሚደረግባቸው የወንጀል መዛግብት አንጻር በኦሮሚያ ክልል ዉስጥ ከተከናወኑት የህግ ማስከበር ስራዎች በተጨማሪ በደቡብ ብሔር፣ ብሔረሰቦች እና ህዝቦች ክልል ቤንች ሸኮ ዞን ጉራ ፈርዳ ወረዳ፣ እንዲሁም በትግራይ ክልል ማይካድራ በሚባል አካባቢ ማንነትን መሰረት ያደረጉ ጥቃቶችን አስመልክቶ ከፌዴራል ፖሊስ ጋር በመሆን በጋራ ምርመራ የሚያጣራ የዐቃቤ ሕግ የምርመራ ቡድን ተደራጅቶ በአካባቢው የወንጀል ምርመራ ስራን በማከናወን 34 ሰዎች በህግ ቁጥጥር ስር የዋሉ ሲሆን 59 ሰዎች ደግሞ በፍርድ ቤት መያዣ ትዕዛዝ ወጥቶባቸው ለመያዝ እየተፈለጉ ይገኛል፡፡

በወንጀል የተገኘን ሀብት የማስመለስ ተግባራትን በተመለከተ በዘጠኝ ወራት ዉስጥ በርካታ ሀብት በማስመለስ ወደ መንግስት ካዝና ገቢ ማድረግ የተቻለ ሲሆን በተያያዘ ጥሬ ገንዘብ – 4‚443‚176‚421ብር፣ 426ተሽከርካሪዎች፣ 15 ቤቶች፣ 15 ድርጅቶች፣ 450‚595‚572 አክሲዮን፤ 484 ማሽነሪዎች፣ 235‚491 ቦንድ፣.መሬት-335‚542 ካሬ በሁሉም ላይ እግድ እንዲወጣ ተደርጓል፡፡ህግ ማርቀቅ ስራን በተመለከተ በዘጠኝ ወር ዉስጥ 14 ህጎችን የማርቀቅ ስራ የተሰራ ሲሆን ከነዚህም ዉስጥ አምስት ያህሉ ህጎች ጸድቀዉ ስራ ላይ ዉለዋል፡፡

ከዚህ ውስጠ በዚሁ የበጀት አመት የንግድ ህጉ ጸድቆ ወደ ተግባር እንደገባ የሚታወቅ ነው፡፡በጥቅሉ ከሴቶችና ህፃናት፣ ከሰብአዊ መብት የድርጊት መርሀ ግብር፣ብሄራዊ የፍልሰት የትብብር ጥምረት ፅ/ቤት፣ከፌዴራል ህጎች ተፈፃሚነት፣ከአለም አቀፍ ፣ከፍትሐ ብሄር ፣ነፃ የህግ ድጋፍ፣ጥብቅና፣ የዜጎችን ንቃተ ህግ ከማሳደግ አንፃር ከፕሮጀክት አፈፃፀም፣ የተግባቦትና ሌሎች ዘርፎችን አስመልክቶ በዘጠኝ ወራት ዉስጥ ዘርፈ ብዙ ተግባራት ተከናዉነዋል፡፡

በዉይይቱ የተሳተፉ የስራ ሀላፊዎችም በቀረበዉ ሪፖርት ላይ ሀሳብ አስተየየታቸዉን እንዲሁም ጠያቄዎችን አንስተዋል፡፡በቀረቡ ጥያቄዎችንም የየዘርፉ ከፍተኛ አመራሮች ምላሽ ከሰጡ በኃላ ጠቅላይ ዐቃቤ ህግ ዶክተር ጌዲዮን ጢሞቲዎስ በቀጣይ የባለ ሙያን ብቃት በማሻሻልና በተከሳሽ እና በምስክር አለመቅረብ የሚቋረጡ መዛግብትን ለመቀነስ በሚያስችል መንገድ በትኩረት መሰራት እንደሚገባ ጠቁመዉና ሌሎች የቀጣይ ወራት የስራ አቅጣጯ ሰጥተዉ ዉይይቱ ተጠናቋል፡፡


Exit mobile version