Site icon ETHIO12.COM

ቀና ልቦና ከበቂ ጥበብ ጋር ስኬታማ ያደርጋልና ጉዟችን በቀና ልቦና እንደተሞላ ይቀጥላል

ከሁሉ በማስቀደም በአንድ የኢፍጣር ምሽት ሰበብ ትልቁን የሀገራችንን ሽንቁር አሳቻ ወቅት በመጠበቅ ቀድደው ለችግር ሊዳርጉን ከነበሩ ሁሉ በቀና ልቦና እና በአላህ እገዛ በመሻገራችን ለአላህ ምስጋናዬን አቀርባለሁ።

በተፈጠው ችግር በተወሰደው ኃላፊነት የጎደለው የሃይል አማራጭ ቀና ምኞታቸው አለመሳካቱ ሳይበቃ ፆማቸውን በጭስ እና በዱላ ለፈቱ ወገኖቼ የተሰማኝን ሀዘን እገልፃለሁ። ጉዳዩ ከአንድ ምምሽት ኢፍጣርነት የዜግነት መብትን የማስከበር ህልውና እንዲሆን በታየው ቅፅበታዊ ለውጥ ወደ ነውጥ ሳይገቡ ላሳዩት ልእለ ሰባዊ ጨዋነት የምንግዜም አድናቆቴን እገልፃለሁ።

ይህ ታላቅ ኢስላማዊ እና ሀገራዊ የኃላፊነት ስሜት አብሮን እንዲዘልቅም አደራ አደራ አደራ እላለሁ። በተለይም ትናንት በተለያዩ ሚዲያዎች እንደገለፅኩት የኢፍጣሩን ፕሮግራም ከማስደቀድ አንስቶ አቅርቦት ለማሟላት አድካሚ ሂደት ውስጥ እንደማለፌ ውጤቱ ውስጥ የሚሰብር ነበር። ይሁንና በቅን ልቦና የተጀመረ ስራ ስኬት እንደማይርቀው በማመን ስሜትን መቆጣጠርና ስለመፍትሄው መልፋት ግድ ነበርና በዚያው ላይ ውለን አምሽተናል።

ቀና ፍላጎት በህግ፣ በፖለቲካ እና በቢዝነስ በተለምዶ የሚታወቀው Good faith በርካታ ችግሮችን ለመፍታት የሚረዳ መርህ ነው። ቀና ፍላጎት ሲኖር ነገራትን የምናይበት መነፅር ከመስተካከል አልፎ አንዱ የሌላውን ችግር ለመረዳት ይጠቅማል። ከተስተጓጎለው የኢፍጣር ፕሮግራም መልስ መንግስትም ህዝቡም ወደቀልባችን ተመልሰን ስለነገ በቀና ልቦና ማሰባችን የተወጠረውን በማርገብ፣ የጠፋውን በመካስ መርህ ለመነጋገር በር ከፍቷል። ይህ ትልቅ ፀጋ እና እድል ነው።

በዘንድሮው ረመዳን በተለያዩ የሀገራችን አካባቢዎች የጎዳና ላይ ዒፍጣር ፕሮግራሞች ተካሂደዋል። የአዳራሽና የሆቴል ፕሮግራሞችም ከወትሮው በተለየ ጨምረዋል። የቤተመንግስት ፕሮግራሞችም በቁጥርና በአይነት በርክተዋል። ይህ ጥሩ ጅምርና ያልተጠቀምንበትን እሴታችንን ዞረን ማየት መጀመራችንን ያመላክት ነበር። በዚህ ደስተኛ ያልነበረ ካለ የመከፋቱ ሰበብ የራሱ የተለየ ፍላጎት ይኖረዋል። በየደረጃው ያሉ የመንግስት አመራሮች ግን ይህን በጎ ጅምር የማድነቅ፣ የመደገፍ፣ እሴትነቱን የማሳደግና ለስኬቱ ሁሉንም አይነት ድጋፍ ሲያደርጉ ቆይተዋል። ሰውን ያላመሰገነ አምላኩንም አያመሰግንምና የነበረውን ጥረት በድንገተኛ አሉታዊ ውጤቱ ለክቶ ምስጋና አለማቅረብ ንፉግነት ነውና በተለይም ለክቡር ዶክተር አብይ አህመድ እና ክብርት አዳነች አቤቤ ምስጋናዬን ለማቅረብ እወዳለሁ።

ዛሬ በነበረን ውሎ የከተማ አስተዳደሩ ትናንት ምሽት ካወጣው መግለጫ ተጨማሪ በክብርት ከንቲባዋ በኩል በይፋ ይቅርታ ጠይቀዋል። ወሩም ረመዳን፣ ክስተቱም በድንገት የተቀለበሰ እንደሆነ በመረዳትና ህዝቡም ከሱ የሚጠበቀውን እንደተወጣ ማመኑ ይቅርታውን በቀና ልቦና ተቀብሎ ሲያበቃ ተግባራዊ ምላሽ እንደሚፈልግ አቋሙን ሲያሳውቅ ውሏል። ይህንን መነሻ በማድረግና ከመንግስት የተለያዩ አካላት በቀረቡ ጥሪዎች መሰረት ተደጋጋሚ ውይይቶችን በማድረግ “ሁላችንም ለበጎ አስበን የለፋንበት ፕሮግራም አለመሳካቱ እንዳሳዘነን እና ማናችንም እንዳላተረፍን” በግልፅና በቀናነት ተወያይተናል። በደረስነውም ስምምነት መሰረት

በነገው እለት ማለትም ግንቦት ሶስት ከተማ አቀፍ የኢፍጣር ፕሮግራሙ ቀድሞ በተያዘለት እንደውም በተሻለ ድምቀት ለማካሄድ ተስማምተናል

መሰል ችግሮችን በዘላቂነት መፍታት የሚያስችሉ መዋቅራዊ ጉዳዮች ላይ በስፋት ተወያይተናል

ፕሮግራሙ የሁላችንም ፍላጎት በመሆኑ ሁላችንም የሚጠበቅብንን እንደምንወጣ ተስማምተናል

በዚህ አጋጣሚ በመንግስት እና በሃይማኖት ተቋማት ውስጥ የሚገኙና ከመንግስትና ህዝብ ጤናማ ግንኙነት ተቃራኒ የሚሰሩትን ህልም ለአሁኑ ማክሸፉ ላይ ሳንብቃቃ ሁሌም በንቃት ሀገራችንን ና ሰላማችንን በጋራ መጠበቅ እንደሚገባን ተወያይተናል

ኢፍጣሩ እንደታሰበው ለታዳሚው በረከትና አብሮነትን፣ ለነዳያን የለት ጉርስን፣ ለሌሎች እምነት ተከታዮች መልካም ጉርብትናን በሚያንፀባርቅ ሁላችንም ሰርተንበት ሁላችንም የምናተርፍበት ለማድረግ እንደምንሰራ ተስማምተናል።

ይህ የኢትዮጵያዊያን ሙስሊሞች እና ግልጽ የሆነ ጥያቄያቸውን ደግፈው ከጎናቸው የቆሙ የክርስትና እምነት ተከታይ ወገኖችም ሰላማዊ ትግል የጋራ ስኬት ነው፡፡ የሃይማኖት እኩልነት የተረጋገጠባት ኢትዮጵያ የዜጎችዋ ኩራት እንጂ እዳ አትሆንም፡፡
ኢትዮጵያዊያን ሙስሊሞች አገራችን ለአማኞቿም ሆነ እምነት ለሌላቸው የአብራኳ ክፋዮች የጋራ ቤታቸው እንድትሆን ታግለዋል፡፡ ብዙ አወንታዊ ለውጦችም ተመዝግበዋል፡፡ ግዙፍ የአማኝ ቁጥር ያሏቸው ክርስትናን እና እስልምናን ተቀብላ ቤተኛ ያደረገች ኢትዮጵያችን የአንድ ወይም የሌላ እምነት ብቸኛ ንብረት የመሆኗ ዘመን ላይመለስ ሄዷል፡፡ ሆኖም ልዩ ልዩ አጋጣሚዎች ይህ የታሪክ ግድፈት ውል እንዲሉብን የሚየደርጉ አካሄዶችን ማረም በቀና ልቦና ማረም ይጠበቅብናል።

በመሆኑም የከተማችን ሙስሊም ነዋሪዎች በኢፍጣሩ ላይ እንድትገኙ እየጋበዝኩ በመልካም ፈቃድ ለማገዝና ለመሳተፍ የምትሹ የሌላ እምነት ተከታዮችም አስቀድማችሁ አስተባባሪዎችን ብታናግሯቸው ለዝግጅት ይረዳናል።

በዚህ ታሪካዊ አጋጣሚ በሚኖረን የአብሮነት ቆይታ ፊቶቻችንን እና እጆቻችንን ወደ ፈጣሪያችን አዙረን ለሰላማችን፣ ለአብሮነታችን፣ እንዲሁም ወገኖቻችን ለተጋረጡባቸው ልዩልዩ ፈተናዎች ዱዓችንን እንድናደርግ ጥሪዬን እያቀረብኩ አላህ (ሱ.ወ.) አገራችንን ሰላም ህዝባችንን ሰላም ያድርግልን-አሚን፡፡

ኡስታዝ አቡበክር አህመድ

Exit mobile version