Site icon ETHIO12.COM

ለግብጽና ሱዳን ሴራ – ሰርጎ ገቦችን መቆጣጠር የሚያስችል መረብ!

ውስጣዊ አለመረጋጋትና የሱዳን የድንበር ወረራ ከሕዳሴው ግድብ ሁለተኛ የውኃ ሙሊት ጋር ምን ያገናኛቸው ይኾን? የዓለም ሀገራትን በሚያስማማ የሕግ ማዕቀፍ የውኃ ሀብታቸውን መጠቀም ከሚፈልጉ ሀገራት መካከል ኢትዮጵያ አንዷ ናት፡፡ ግብጽ የዓባይ ውኃን የበላይነቷን ለማስጠበቅና ቀጣዩ ትውልድ በውኃ ሀብቱ የመልማት መብት እንዳይኖረው የሀገሪቱን የውኃ ባለቤትነት የሚነጥቅ አሳሪ ስምምነት እንዲፈረም ትፈልጋለች፡፡

ኢትዮጵያ ግን በሳይንስ፣ በሕግ፣ በፖለቲካም ሆነ በዲፕሎማሲ በቀላሉ የምትቀመስ ሀገር አልሆነችም፡፡ በወሎ ዩኒቨርሲቲ የሰላምና ልማት ትምህርት ክፍል መምህሩ አልዩ ውዱ (ዶክተር) ዓባይን ከምንጩ ለመቆጣጠር ተደጋጋሚ ሙከራ አድርጋ የከሸፈባት ግብጽ አሁንም የተለያዩ የሴራ አካሄዶችን እየተጠቀመች ትገኛለች ብለዋል፡፡ የድንበር ውዝግብ ማስነሳት፣ ውስጣዊ አለመረጋጋትን መደገፍና በኢትዮጵያ ላይ ዓለም አቀፍ ተጽዕኖ እንዲበረታ ማድረግ ግብጽ ከምትጠቀማቸው አካሄዶች መካከል ይጠቀሳሉ፡፡ ዓባይን ተጠቅማ ከማልማት አልፋ ወደ እስራኤልና መካከለኛው ምሥራቅ ማስተላለፏም የዓባይ ጉዳይን የመካከለኛው ምሥራቅና የአውሮፓ ሀገራት ጉዳይ ለማድረግ የታለመ መሆኑን አስገንዝበዋል፡፡

በዚሁ ዩኒቨርሲቲ የፖለቲካል ሳይንስ መምህር፣ በዓባይና አዋሽ ተፋሰስ ጥናት ተቋም የውኃ ፖለቲካ እና አስተዳደር አስተባባሪው ጀማል ሰዒድ እንዳሉት ለሱዳንና ግብጽ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ ዋና የመከራከሪያ ጉዳይ ሆኖ እያለ የድንበር ውዝግብ መፈጠሩ ድብቅ አጀንዳቸውን ለማስፈጸም ነው፤ ይህም በጥንቃቄ መታዬት አለበት ብለዋል፡፡ ምንም እኳን የሕዳሴ ግድቡ ተጽዕኖ እንደሌለው ራሳቸው ምስክርነት የሰጡበት ቢኾንም አካሄዱ ከሕዳሴው ግድብ ጋር ግንኙነት እንዳለው አመላካች አለው ብለዋል፡፡ለረጅም ዘመናት የተረጋጋ መንግሥት መመስረት የተሳናት ሱዳን በግብጽ ጣልቃ ገብነት ምክንያት ነጻ የውጪ ግንኙነት መመስረት ተስኗታል፡፡

ሱዳን ከኢትዮጵያ ጋር ቀጥታ ጦርነት ባትገጥምም ውስጣዊ ችግሯን እና የሚቀርብባትን ዓለም አቀፍ የሰብዓዊ መብት ጥሰት ጥያቄን ለማዳፈን የድንበር ውዝግቡን እንደ አማራጭ ተጠቅማለች፡፡ እንደ አቶ ጀማል ማብራሪያ የሁለቱ ሀገራት ዓላማ በድንበራቸው የማይደራደሩትን ኢትዮጵያውያን ወደ ጦርነት ማስገባት እና የብሔርና የሃይማኖት ግጭትን በመቀስቀስ ሀገሪቱን ማፍረስ ነው፡፡

አፍሪካ በኢኮኖሚ ኋላቀር እድትኾን የሚሹ የአውሮፓ ሀገራትም ኢትዮጵያ በተጽዕኖ ውስጥ ኾና ያልተገባ ውሳኔ እንድታሳልፍ እየጣሩ ይገኛሉ፡፡ ይህም ኢትዮጵያውያንን ጫና ውስጥ በመክተት እይታቸውን ከሕዳሴ ግድቡ እንዲያነሱ የታቀደ መኾኑን ተናግረዋል፡፡ እንደ ምሁራኑ ማብራሪያ ሱዳን ጎረቤት ሀገር እንደመኾኗ መጠን ኢትዮጵያ ታሪካዊ ስህተት ላለመሥራት ተጠንቅቃለች፡፡ ሉዓላዊ ድንበሯን የማስጠበቅ መብቷ የተከበረ ቢኾንም ለነገሮች ቅደም ተከተላዊ የእርምጃ ሂደትን መከተሏ የሚበረታታ ነው ብለዋል፡፡ ሱዳን የኢትዮጵያን ሉዓላዊ ድንበር ጥሳ በገባች ጊዜ የኢትዮጵያ መንግሥት ያሳየውን የተጠና አካሄድ ምሁራኑ አድንቀዋል፡፡

ግብጽና ሱዳን የኢትዮጵያን የውስጥ ድክመትና አለመረጋጋት እየተጠቀሙበት ነው፤ የጎሳ ፌዴራሊዝም በነገሰባት ሀገር ክልሎች ኮንፌዴራላዊ ሥርዓት የሚከተሉ እስኪመስል ድረስ የአትንኩኝ ባይነትና የእርስ በርስ ግንኙነት መሻከር ምቹ መደላድል እንደፈጠረላቸውም ምሁራኑ ተናግረዋል፡፡ በውስጣዊ የፖለቲካ ክፍፍል ውስጥ የገቡ ሀገራት ለውጪ ጠላቶች የመጋለጥ እድላቸው ሰፊ ኾኖ ታይተዋል ነው ያሉት፡፡ በአንጻሩ ውስጣዊ አንድነት፣ የፖለቲካ ቁርጠኝነትና ሕዝባዊ አንድነት ያላቸው ሀገራት ከጠላት የሚቃጣባቸውን ጥቃት በስኬት አክሽፈዋል፡፡

የሱዳንና የግብጽ የሴራ አካሄድ፣ የአረብና አንዳንድ የአውሮፓ ሀገራት እንዲሁም የአሜሪካ ጣልቃ ገብነት የኢትዮጵያን ሕዝብ በጠላትነት እንዲተያይ ከሚያደርገው የጎሳ ፌዴራሊዝም ጋር ተዳምሮ በሀገሪቱ ዕጣ ፈንታ ላይ አደጋ መደቀኑን አንስተዋል፡፡ የታላቁ ኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ የድርድር አጀንዳ ከውኃ ክፍፍል እንዲወጣ መታገል፤ ግብጽ ለዘመናት በዓባይ ወንዝ ላይ የተከተለችውን ትርክት የሚቀይር አዲስ ትርክት መፍጠር፤ በሀገሪቱ አስተማማኝ ሰላም እንዲሰፍን ማድረግና አዳዲስ የፖሊሲ አማራጮችን ማሳዬት ደግሞ ከልሂቃን እንደሚጠበቅ ምሁራኑ በመፍትሔነት ያስቀመጧቸው ሀሳቦች ናቸው፡፡

የአፍሪካ ሕብረት አጀንዳ በምዕራባውያን እንዳይጠመዘዝ፣ የአፍሪካ የልማት ፖሊሲ ሉዓላዊነትም አደጋ ላይ እንዳይወድቅ የፓንአፍሪካኒዝምን ስሜት መቀስቀስ ከኢትዮጵያ የሚጠበቅ ተግባር ነው ብለዋል፡፡ በመንግሥት መዋቅር ውስጥ ኾነው በጎሳ ሰዎችን ለማጋጨት የሚጥሩ አካላትን፤ የሀገር ኅልውናን የሚፈታተን የፖለቲካ እንቅስቃሴን እንዲሁም የሀገሪቱን ሕዝብ እና መንግሥት ኅልውና የሚፈታተን ታጣቂን አጥብቆ መፋለም ከመንግሥት የሚጠበቅ ተግባርና ግዴታ መኾኑንም አንስተዋል፡፡ በሀገራት መካከል መከባበር እንዲሰፍን የተመጣጠነ ወታደራዊ አቅም መፍጠር እንደሚያስፈልግም ምሁራኑ አስገንዝበዋል፡፡

እንደ ምሁራኑ ምክር ኢትዮጵያም አስፈላጊውን ወታደራዊ ዝግጅት ማድረግና ሠርጎ ገቦችን፣ መቆጣጠር የሚያስችል የደኅንነት መረብ መዘርጋት ይጠበቅባታል፡፡ በዲፕሎማሲው ረገድም የግብጽና የሱዳንን አካሄድ ሊቀለብስ የሚያስችል ስትራቴጂያዊ አጋርነት መመሥረትና ማጠናከር አለባት፡፡ የማኅበራዊ ሚዲያ አንቂዎችም ያላቸውን ተቀባይነት ተጠቅመው በዚህ ፈታኝ ጊዜ ለሀገርና ለሕዝብ ጥቅም እንዲሠሩ መክረዋል፡፡ ኀላፊነት በጎደለው መልኩ የሚንቀሳቀሱትን ግን መንግሥት አስፈላጊውን ርምጃ መውሰድ ይኖርበታል ብለዋል፡፡ (አሚኮ) ዘጋቢ፡- ደጀኔ በቀለ


Exit mobile version