Site icon ETHIO12.COM

የውጭ ሀይሎች ጣልቃ ገብነትን በመቃወም ከመጪው አርብ ጀምሮ በይፋ ዘመቻ ይጀመራል፤ ኤምባሲዎች

የውጭ ሀይሎች በኢትዮጵያ የውስጥ ጉዳይ ጣልቃ ለመግባት የሚያደርጉትን እንቅስቃሴ በመቃወም የኢትዮጵያውያንን አቋም ለዓለም አቀፉ ማህበረሰብ ለማሳወቅ በታዋቂና ተጽዕኖ ፈጣሪ ኢትዮጵያውያን የተመራ እንቅስቃሴ የፊታችን አርብ እንደሚጀመር አስተባባሪዎቹ ገለጹ።

ዘመቻውን “ብሔራዊ ክብር በህብር” በሚል መሪ ቃል የሚያስተባብሩት ከሲቪክ ማህበራት፣ አርቲስቶች፣ ሀገር ወዳድ ግለሰቦች፣ የተለያዩ የማህበረሰብ አንቂዎች የተውጣጡ ታዋቂና ተጽዕኖ ፈጣሪ ግለሰቦች ናቸው። የዘመቻው አስተባባሪዎች በዛሬው ዕለት በጋራ በሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫ እንዳስታወቁት፣ በኢትዮጵያ ከለውጡ ጊዜ ወዲህ እየተባባሰ እና እየጨመረ የመጣ የውጪ ጣልቃ ገብነት እና ተጽዕኖ እየታየ ነው።

እነዚህም ተጽዕኖዎች ሶስት መሰረታዊ ክንውኖችን ማለትም የህዳሴ ግድብ ግንባታና የውሃ ሙሌት፣ በትግራይ ክልል የተካሄደውን የህግ ማስከበር ዘመቻ እና የዜጎች መብት የሆነውን የምርጫ ስርዓት በመታከክ በኢትዮጵያ ህዝብ ላይ የሚፈጸሙ ናቸው ብለዋል።

የዘመቻው የህዝብ ግንኙነት አስተባባሪ አቶ አብይ ታደለ እንደገለጹት፤ እስከ መጪው አርብ ባሉት ጊዜያት በተለያዩ የዓለማችን ክፍሎች የሚኖሩ ኢትዮጵያውያንና የኢትዮጵያ ወዳጆችን በማስተባበር በኢትዮጵያ የውስጥ ጉዳይ ጣልቃ ለመግባት የሚሞክሩ የውጭ ሀይሎች እጃቸውን እንዲያነሱ የሚጠይቅ ፊርማ ይሰበሰባል። እንዲሁም፣ መቀመጫቸውን አዲስ አበባ ላደረጉ የተለያዩ ሀገራት ኤምባሲዎች የወከሏቸውን ሀገራት በኢትዮጵያ ጉዳይ ጣልቃ ከመግባት እንዲቆጠቡ የሚጠይቅና የኢትዮጵያውያንን አቋም የሚገልጹ ደብዳቤዎች እንዲደርሳቸው ይደረጋል ብለዋል።

አቶ አብይ አክለውም፣ ከቀኑ 10 ሰዓት እስከ 11 ሰዓት ባለው ጊዜ “ከኢትዮጵያ ላይ እጃችሁን አንሱ” የሚል መፈክር በመላው ሀገሪቱ እንዲሁም በተለያዩ የዓለማችን ክፍሎች እንዲስተጋባ ይደረጋል። በመጨረሻም ከምሽቱ 12 ሰዓት የዕለቱ መርሃ ግብር ማጠቃለያ እና የአጠቃላይ ዘመቻው መክፈቻ የሆነውን የኪነ-ጥበብ ዝግጅት ይካሄዳል ብለዋል። ህብረተሰቡ የኮሮና ቫይረስ መመሪያዎችን በጥንቃቄ በመተግበር የዘመቻው ተሳታፊ እንዲሆኑም አስተባባሪዎቹ ጥሪያቸውን አቅርበዋል።

ህዝቡ ህግና ስርዓትን በተከተለ መልኩ በየኤምባሲዎች አቅራቢያ በመገኘት ድምጹን ማሰማት ይችላልም ተብሏል።በአስተባባሪ ኮሚቴው ውስጥ አቶ አንዳርጋቸው ጽጌ፣ ዑስታዝ አቡበክር አህመድ፣ አርቲስት ዘለቀ ገሰሰን ጨምሮ ሌሎችም ታዋቂ ኢትዮጵያውያን ይገኙበታል። EPA


Exit mobile version