Site icon ETHIO12.COM

“ኢትዮጵያ ሐሳብን በነፃነት የመግለጽ እና ለፕሬስ ነፃነት መከበር የማይናወጥ አቋም አላት”

ኢትዮጵያ ሐሳብን በነፃነት የመግለጽ እና ለፕሬስ ነፃነት መከበር የማይናወጥ አቋም ያላት መሆኑን የኢትዮጵያ መገናኛ ብዙኃን ባለሥልጣን ዛሬ ባወጣው መግለጫ አስታወቀ።

ሐሳብን በነፃነት የመግለጽ እና የፕሬስ ነፃነት መብቶች በሕገ-መንግሥቱ የተረጋገጡ እሴቶች ናቸው ያለው ባለሥልጣኑ፣ የኢትዮጵያ መንግሥት እነዚህን እሴቶች ለመጠበቅ ቁርጠኛ መሆኑን በድርጊት ያረጋገጠ መሆኑን ጠቁሟል። አሁን በሥልጣን ላይ ያለው መንግሥት ወደ ሥልጣን እንደመጣ በቀዳሚነት የወሰደው እርምጃ ጋዜጠኞችን እና የፖለቲካ እስረኞችን መፍታት እንደነበርም በምሳሌነት አንስቷል።

የውጭም ሆነ የሀገር ውስጥ ጋዜጠኞች የመረጃ ተደራሽነትን እንዲያገኙ ለማስቻልም ለበርካታ ዓመታት ተጥለው የቆዩት ክልከላዎች እና እንቅፋቶች ሙሉ በሙሉ መነሳታቸውንም ጠቅሷል። በአሁኑ ሰዓትም በ129 ቋሚ ዘጋቢዎች የተወከሉ 35 የውጭ የዜና ድርጅቶች ሀገሪቱ ውስጥ እንዳሉም ባለሥልጣኑ ጠቁሟል። ከዚህ ባለፈም በትግራይ ክልል ሲካሄድ በነበረው የሕግ ማስከበር ዘመቻ ወቅትም ከተለያዩ ሀገራት ለተወጣጡ 82 የውጭ ጋዜጠኞች ጊዜያዊ ፈቃድ ተሰጥቶ ያለውን ሁኔታ መዘገብ የሚችሉበት ሁኔታ መመቻቸቱን አመላክቷል።

ሐሳብን በነፃነት የመግለጽ እና የፕሬስ ነፃነት መብቶች በሁሉም ወገኖች መከበር ይኖርባቸዋል ያለው የመገናኛ ብዙኃን ባለሥልጣን፣ ጋዜጠኞቹ የግጭት ዘገባዎችን በተመለከተ ሁኔታውን በሚገልጽ መልኩ ሙያዊ የሆኑ የአዘጋገብ ደንቦችን አክብረው ይዘግባሉ የሚል እምነት እንደነበረው አውስቷል። በየትኛውም ዓለም እንደሚደረገው ሁሉ ወታደራዊ ዘመቻ በሚካሄድበት አካባቢ ገደብ እንደሚጣል በመግለጽም፣ ፈቃድ የተሰጣቸው የውጭ ዘጋቢዎችም ይህንኑ እውነታ አክብረው እና ጠብቀው ይሠራሉ ተብሎ እንደሚጠበቅ ገልጿል።

ይህ ሳይሆን ቀርቶ የሕግ ጥሰት ሲያጋጥም በየትኛውም የዓለም ክፍል እንደሚደረገው ሁሉ ባለሥልጣኑ ሕግን የማስከበር ኃላፊነቱን የመወጣት ግዴታ እንዳለበት አስገንዝቧል። በዚሁ አግባብ ዓለም አቀፍ ተሞክሮን በመከተል በትብብር ለመሥራት እና ለዘጋቢዎች በተቻለ መጠን ሁኔታዎችን ለማመቻቸት ዝግጁ መሆኑን ባለሥልጣኑ አመልክቷል። አሁንም ቢሆን መንግሥት ሐሳብን በነፃነት የመግለጽ እና የፕሬስ ነፃነትን መከበር በተመለከተ የያዘው አቋም የማይናወጥ መሆኑን ገልጾ፣ “ሀገሪቱም ሆነች ባለሥልጣኑ በቅንነት ሥራቸውን የሚሠሩ ጋዜጠኞችን ለማስተናገድ ዝግጁ ናቸው” ሲል ገልጿል። ( ኢዜአ)


Exit mobile version