Site icon ETHIO12.COM

የአሜሪካ መንግስት ውሳኔ ኢትዮጵያ አልሸባብን በመከላከል እያደረገች ባለው እና ሌሎች የጸጥታ ጥበቃ ስራዎች ላይ ተጽእኖ እንደሚያመጣ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር አስታወቀ!

በአሜሪካ የተጣለው የቪዛ እገዳ ኢትዮጵያ በቀጣናው በምታካሂደው አልሸባብን የመከላከል እና ሌሎች የጸጥታ ጥበቃ ስራዎች ላይ ተጽእኖ እንደሚያመጣ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር አስታወቀ።

የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ አምባሳደር ዲና ሙፍቲ ዛሬ በሰጡት ሳምንታዊ መግለጫ እንደተናገሩት፤ ውሳኔው በቀጣናው ሽብርተኞችን በመከላከል ረገድ ኢትዮጵያ እያከናወነች ያለው ስራ ላይ አሉታዊ ተጽእኖ ይኖረዋል።

በአሜሪካ መንግስት የተላለፈው ውሳኔ መልሶ አሜሪካኖቹን መጉዳቱ አይቀርም ሲሉ ነው አምባሳደር ዲና ያብራሩት።

የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ትናንት ባወጣው መግለጫም፤ የአሜሪካ መንግስት ውሳኔ በኢትዮጵያ የውስጥ ጉዳይ ላይ ለመግባት ያለመ ከሆነና ክፍለ ዘመን የተሻገረውን ወዳጅነት ከግምት ውስጥ ያላስገባ እስከሆነ ድረስ የኢትዮጵያ መንግስት ከአሜሪካ መንግስት ጋር ያለውን የሁለትዮሽ ግንኙነት መለስ ብሎ ለማጤን ይገደዳል ሲል አስታውቋል።

አምባሳደር ዲና በዛሬው መግለጫቸው፤ ሱዳንና ግብጽ የጋራ ጦር ልምምድ ማድረግ ይችላሉ፤ ኢትዮጵያውያን ግን ሉአላዊነታቸውን ለማስጠበቅ ሁሌም ዝግጁ ናቸው ብለዋል።

አምባሳደር ዲና እንደገለጹት፤ በአገሩ ሉኣላዊነት ጉዳይ የሚተኛ ህዝብም ሆነ መከላከያ ሰራዊት እንደሌለን ይታወቃል። ሱዳን እና ግብጽ በድንበር አካባቢ የጥምር ጦር ልምምድ ቢያደርጉም ሁልጊዜም እንደምንለው በኢትዮጵያ ላይ ኪሳራ የሚያመጣ መሆን የለበትም። ኪሳራ የሚያመጣ ከሆነ ግን የኢትዮጵያን ሉአላዊነት ለመጠበቅ የሚሰራው ኃይል ምላሹን ለመስጠት ሁሌም ዝግጁ ነው።

የኢትዮጵያ መንግስት በዚህ ደረጃ እምነት ይዞ እየተንቀሳቀሰ መሆኑ አምባሳደር ዲና አብራርተዋል። via FBC

Exit mobile version