Site icon ETHIO12.COM

ኬሪያ ኢብራሂም ውል አፍረሰው በድጋሚ በፍርድ ቤት ውሳኔ ታሰሩ፤ ዐቃቤ ህግ በቂ መረጃ ወስዷል

የቀድሞ የፌዴሬሽን ምክር ቤት አፈ ጉባኤ ወ/ሮ ኬሪያ ኢብራሂም የምስክርነት ጥበቃቸው ተነስቶ ዳግም ፍርድ ቤት መቅረባቸውን ጠቅላይ አቃቤ ሕግ ገለጸ። ዛሬ የፌደራል መጀመሪያ ደረጃ ፍርድ ቤት አራዳ ምድብ አንደኛ ጊዜ ቀጠሮ ችሎት ቀርበው በፖሊስ ቁጥጥር ስር እንዲውሉ ተወስኖባቸዋል። አቃቤ ህግ ቃል በቃል ባያስቀምጠውም ኬሪያ ዳግም እስር ቤት ሆነው ጉዳያቸውን እንዲከታተሉ የተፈረደው መረጃ ሰጥተው እንዲለቀቁ የተስማሙትን ውል አፍርሰው ነው።

ኬሪያ ኢብራሂም መቀሌ በትክክል ካልተገለጸ ቦታ በቁጥጥር ስር ከዋሉ በሁዋላ በርካታ መረጃ ሲሰጡ እንደነበር ይታወሳል። ለጉዳይ ቅርብ የነበሩ በወቅቱ እንዳሉት ኬሪያ ለህግ ማስከበሩ ግብአት የሆኑ መረጃዎችን ገና ከትግራይ ወደ አዲስ አበባ ሳያቀኑ አጋርተዋል። አዲስ አበባ ከመጡ በሁዋላ ለአቃቤ ህግ የሰጡት ምስክረነት በትህነግ ተጠርጣሪዎች ላይ ፍርድ ቤት ማስረጃ እንዲሆን ተስማምተው የምስክርነት ጥበቃ ህጉ በሚፈቅደው አግባብ እንዲደረግላቸው ተወስኖ ከእስር ተለቀው በጥበቃ ስር ነበሩ።

ዛሬ አቃቤ ህግ ራሱ እንዳለው ወ/ሮ ኬሪያ ቀደም ሲል የሰጡት መረጃ በሃይል ተገደው ወይም ፈርተው ያደረጉት በመሆኑ ማስረጃ ሆኖ እንዳይቀርብ በማለታቸው ሳቢያ ህጉ የሰጣቸውን ጥበቃ አንስቷል። ዜናውን የሰሙ እንዳሉት ወ/ሮ ኬሪያ ጫና ተደርጎባቸው ይህንን ማድረጋቸውን ገልጸዋል። በውሳኔያቸው የሚጎዱትም እሳቸው እንደሆኑ ገልጸዋል። ሲያስረዱም አቃቤ ህግ መረጃዎቹን በሙሉ በቀጥታ ሳይሆን በመስቀለኛ ጥያቄና በተለያዩ አግባቦች ምርመራውን ለማስፋት፣ ተቸማሪ ምስክሮች ለማግኘትና ክሱን ለማጠናከር፣ ከዚያም በላይ የክሱን አቅጣጫ የተከሳሾች ጠበቆች ሊመክቱ እንዳይችሉ በመቀያየር ለመገልገል ተጨባጭ ግብአት አግኝቷል። ይህንን ግብአት የሰጡት ወ/ሮ ኬሪያ መሆናቸውን ደግሞ ተከሳሾች ያውቃሉ። ይህን በመወሰናቸው ከሚደርስባቸው እንቅፋቶች ሊድኑ አይችሉም ብለዋል። አቃቤ ህግን ጠቅሶ ኢቢሲ ይህን ዘግቧል።

የፌዴራል ጠቅላይ አቃቤ ሕግ የፕሬስ ሴክሬቴሪያት ኃላፊ አቶ አወል ሱልጣን ለኢዜአ እንደገለጹት ወይዘሮ ኬሪያ ከተከሳሽነት ወደ ምስክርነት ተቀይረው ነበር። ተጠርጣሪዋ በጠቋሚዎችና ምስክሮች ጥበቃ አዋጅ ቁጥር 699/2003 በገቡት ሥምምነት መሠረት ዝርዝር የምስክርነት ቃላቸውን በፈቃዳቸው መስጠታቸውን አስታውሰዋል። በገዛ ፈቃዳቸው ምስክርነታቸውን ሰጥተው እንደነበር ያስታወሱት አቶ አወል በፍርድ ቤት ውሳኔ ከእስር እንደተለቀቁና ጎን ለጎንም ለግለሰቧ አስፈላጊውን የምስክርነት ጥበቃ ሲደረግላቸው መቆየቱን ተናግረዋል።

ይሁንና ወይዘሮ ኬሪያ ቆይተው ምስክር መሆን ፍላጎት እንደሌላቸው እንዲሁም ምስክርነት ሲሰጡ የቆዩት ተገደው እንደነበር በመግለጻቸው ምስክርነታቸው ማቋረጡን ገልጸዋል። በምስክሮችና ጠቋሚዎች አዋጅ ቁጥር 699/2003 አንቀጵ 11 መሰረት የጥበቃ ተጠቃሚው ሥምምነቱንና ግዴታውን የማያከብር ከሆነ የጥበቃ ስምምነት ውሉ ይቋረጣል። ይህንንም ተከትሎ አቃቤ ሕግ ለወይዘሮ ኬሪያ ምስክር በመሆናቸው ይሰጣቸው የነበረውን ጥበቃ ለማንሳት መገደዱን ነው አቶ አወል የተናገሩት።

ከዚህም በኋላ ወይዘሮ ኬሪያ ከዚህ ቀደም በተጠረጠሩበት ወንጀል የቅድመ ምርመራ ስራ እንዲጀመር አቃቤ ሕግ ዛሬ ለፍርድ ቤት ጥያቄ አቅርቧል ብለዋል። የተጠርጣሪዋ ጠበቆች በጉዳዩ ላይ ለመከራከር አልተዘጋጀንም በማለታቸው ፍርድ ቤቱ ወይዘሮ ኬሪያ በመጪው ሰኞ ዳግም ፍርድ ቤት እንዲቀርቡ አዟል። ወይዘሮ ኬሪያ እስከ መጪው ሰኞ በፖሊስ ቁጥጥር ስር እንዲቆዩም ፍርድ ቤቱ ወስኗል።


Exit mobile version