Site icon ETHIO12.COM

እስከ ቀራኒዮ? “ኢሳያስን አሳልፈህ ስጥ፣አማራን ከትግራይ ንቀልና ለትህነግ ድንበር ክፈት” የአሜሪካ ጫና

ዩ.ኤስ. አይ.ዲ ሰራተኛ ነው። ትግራይ ቆይቶ ወደ አዲስ አበባ ከተመልሰ በሁዋል ለአዲስ አበባ ተባባሪያችን እንዳለው ኢትዮጵያ ውስጥ ያለ ፈረንጅ ሁሉ ያለው ትግራይ ነው ማለት ይቻላል። እርዳታ በገፍ ይጎርፋል። የረህብ ስጋትና የህል እጥረት ዜናም ይጎርፋል። የእጥረት ዜናው ከምን የመነጨ እንደሆነ የሚናገር እንደሌለ ያስረዳል። ሰዎቹ ለወታደራዊ ጣልቃ ገብነት ያመቻቸው ዘንዳ “ ለኬሚካል ቦንብ ተጠቅማቹሃል” ዜናም እያስከተሉ ነው።

ለስራው አመቺ ባለመሆኑ ስሙ እንዳይገለጽ ጠይቆ መረጃ የሰጥን የዩ.ኤስ.አይ.ዲ ሰራተኛ በየጊዜው በሚወጡ መረጃዎች ግነት ብቻ ሳይሆን ሙሉ ስዕል የሚያሳዩ አመለሆናቸው ያበሳጨዋል። እንደ ምሳሌ ሲያስረዳ በአንዳንድ ወረዳዎች እርዳታ በቀጥታ ለትህነግ ሃይሎች እንደሚጫን እርዳታ ሰጪዎቹም፣ አድራሾቹም፣ተቀባዮቹም ያውቃሉ። ስለ እጥረትና ስለ ረሃብ ስጋት ሲያወሩ ይህን እውነት ይዘሉታል።

አንዳንድ ወረዳና ቀበሌዎች የተሳሳተ መረጃ እንደሚሰጡ፣ እርድታ የደረሳቸውን ክፍሎች መዝግበው በወጉ ሪፖርት እንደማያደርጉ፣ ከተመደቡበት ስራ ውጭ ጫካ ካለው ሃይል ጋር በመመካከር ለነጮቹ የተሳሳተና “ትግሉን” የሚደግፍ መረጃ እንደሚያቀርቡ በገሃድ ይታወቃል። ነጮቹም ይህን እያወቁ የተሳሳተውን መረጃውን በይፋ ሪፖርትነት ይጠቀሙበታል።

ይህ የአይን እማኝ እንደሚለው እርዳታ ሰጪዎቹ መንገድ ላይ እህል እንደሚዘረፍ፣ የሚዘርፉት የትህነግ ሃይሎች መሆናቸውን፣ እርዳታ ሰራተኞች እንደሚገደሉ፣ የሚገድሉት እነሱ እንደሆኑ፣ ጠንቅቀው እንደሚያውቁ በጎንዮሽ ይነግሩናል ግን በይፋ ትህነግ የህንን እንደሚፈጽም ሪፖርት ማድረግ አይፈልጉም።ጭራሹኑ አያስቡትም።

ይህ ብቻ አይደለም በቦታው ላይ ስለነበረ ማንነቱ እንዳይታወቅ ሲል ስም ባይጠቅስም የእዛ አካባቢ ነዋሪዎች የትህነግ ሰዎች የፈጸሙባቸውን በደል ጠቅሰው፣ መከላከያ በቦታው ምንም ጥፋት እንዳልሰራ ቢያስረዱም ነጮቹ ለሪፖርታቸው አልተጠቀሙበትም። እንደ ምስክሩ አባባል አብዛኞቹ ልዩ ፍላጎትና ተልዕኮ እንዳላቸው ግልጽ ነው። አሁን ላይ በሱዳንና በትግራይ መካከል የድንበር ግንኙነት እንዲፈጠር እየገፉ ነው። ለዚህም ሲሉ “የአማራ ልዩ ሃይል ከትግራይ ይውጣ” የሚለውን ገፍተውበታል።

“ አሁን ባለው ህገ መንግስት መሰረት በተካለለው ክልል ወልቃይት ትግራይ ውስጥ ነው። የአማራ ልዩ ሃይል ከትግራይ ይውጣ ሲባል ይህንንበመንተራስ ነው። የይገባናል ጥያቄ ካለ ወደፊት የሚታይ ነው” በሚል ነጮቹ ህግ ጠቅሰው እንደሚከራከሩ ይኸው ምስክር አስረድቷል። ይህ ተግባራዊ ሲሆን በረሃ ያለው ሃይል ከሱዳን የሚያገናኘው ኮሪዶር ያገኛል። መሳሪያ ይገባለታል። እንሱም ወደ ሱዳን እንዳሻቸው ይመላለሳሉ።

የመከላከያ ሰራዊት ላይ ያልታሰበ ጥቃት ተሰንዝሮ ጦርነቱ ሲጀመር በአየር፣ በምድርና በመድፍ ሁመራ ላይ የነበረው ሊደፈር የማይችል ምሽግ እንዲደመሰስ የተደረገው የትህነግ ሃይል ሎጅስቲክ እንዳያገኝና ሸሽቶ ወደ ሱዳን እንዳይወጣ ታስቦ መሆኑንን የኢትዮጵያ የጦር ባለሟሎች መናገራቸው የአይን እማኙን መረጃ የሚያተናክር ይሆናል።

ይህ ብቻ ሳይሆን ሱዳን ወረራዋን በማራዘም የኢትዮጵያ መከላከያ እንዲበተንና ሃይሉ እንዲሳሳ ትኩረት ሰጥታ መስራቷ፣ የኤርትራ ሰራዊት እንዲወጣ የሚደረገው ግፊት ለትህነግ ሃይል የድንበር ማስተንፈሻ ለመስጠትና በሱዳን እየሰለጠነ ያለው የትህነግ ሃይል መግቢያ እንዲያገኝ ታስቦ እንደሆነ በተደጋጋሚ መገለጹ ይታወሳል። ሙከራ ተደርጎም በመከላከያ ሰራዊት ሃይል መመታትቱ ይታወቃል።

ይህ እየሆነ ባለበት ሰዓት ነው የአውሮጳ ኅብረት ዓለም አቀፍ ትብብር ኮሚሽነር ዩታ ዑርፒላይነን በትግራይ ክልል ውስጥ ስላለው ወቅታዊ ኹኔታ ሲገልጹ «ይህን ቀውስ ለመቅረፍ በዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ የተቀናጀ አሰራር ያስፈልጋል» ያሉት። ሲትየዋ ይህን ያሉት አሜሪካ ኢትዮጵያና ኤርትራ ላይ የጉዞና የኢኮኖሚ ማዕቀብ ማድረጓን ተከትሎ ነው። አሜሪካ አጋሮች እንዲከተሉ ባሳሰበችው መሰረት ነው።

በኤርትራ 30ኛ ዓመት የንግስና በዓላቸውን ያከበሩት ፕሬዚዳንት ኢሳያስና ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ ወደ ግጭት ውስጥ እንዲገቡ አሜሪካ በዚህ ምክንያት ነው። በዛውም “ እጅ አልሰጥም” ያሉትን ኢሳያስን ከመንበራቸው ለማንሳት “ጊዜው አሁን ነው” የሚል አቋም በመያዙ እንደሆነ እየተደመጠ ነው።

ለዚሁ የአሜሪካ ሃሳብ እጅግ ዝግ የሚባል ድህንነት አላቸው የሚባሉት ኢሳያስን ዛሬ ለማንበርከከ መሳሪያ የሆነው ትህነግ ሆኗል። ትህነግ በመከላከያ ሰራዊት ላይ ድንገተኛ ጥቃት መሰንዘሩን ተከትሎ በተወሰደ እርምጃ ህልውናው ቢከስምም ጦርነቱ ያስከተለው መዘዝ ኢሳያስን ወደ ፊት ያመታቸውም በዚሁ የአሜሪካ የቆየ ፍላጎት ሳቢያ ነው።

ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ በተዛዋሪ ፣ ለጉዳዩ ቅርብ የሆኑ በግልጽ እንደሚሉት የኢትዮጵያ መንግስት ጫና መነሻና መድረሻ ፐሬዚዳንት ኢሳያስ ናቸው። አብይ አሕመድ “ በፍጹም” ሲሉ መልስ እንደሰጡበት የተሰማው ጉዳይ ኢሳያስ አፉወርቂን አሳልፈው እንዲሰጡ የቀረበላቸውን ጥያቄ ነው። ኢትዮጵያና ኤርትራ ግጭት ውስጥ ሁሉ እንዲገቡ አሜሪካ አስገድዳለች። አብይ የኤርትራን ሰራዊት በሃይል እንዲያስወጡ አሜሪካ ድጋፍ እንደምታደርግ ሁሉ ገልጻለች። ሁሉም ሆኖ ከአብይ ወገን የተሰጠው ምላሽ “ አይታሰብም” የሚል ነው። ብልጽግና ስብሰባውን ሲያጠናቅቅ የኤርትራና ኢትዮጵያ ወዳጅ መሆን በቀይ ባህር ላይ ለታሰበው ሃይልን የማጠናከር እቅድ ስማቸው ባልተጠቀሰ አገራት እንዳልተወደደ መግለጹ ከላይ የተባለውን ጉዳይ ያጎላዋል።

ለዚህ ነው እንግዲህ የኤርትራ ጦር ከትግራይ ክልል ሙሉ በሙሉ ለቆ እንዲወጣ፣ ሲወጣም ሌሎች ወገኖች እንደሚፈልጉት በኢትዮጵያና ኤርትራ መካከል የተፈጠረውን አዲስ የመረዳዳት መንፈስ በማይጎዳ መልኩ እንዲሆን አስበው እየሰሩ ያሉትን ወገኖች አሜሪካ ብዙም መስማት የማትፈልገው። ኢትዮ 12 አንድ አገር በቀል ድርጅት ይህን እያከናወነ መሆኑንን ሰምታለች።

አሜሪካ ዜናውን በገሃድ ባትቃወምም  የኤርትራ ሰራዊት በሰላማዊ ወይይት ከትግራይ ሲወጣ ፕሬዚዳንት ኢሳያስ እስካሉ ድረስ ኢትዮጵያና ኤርትራ አሁን በጀመሩት የመረዳዳት መንገድ እንዲቀጥሉ ስለማትፈልግ አካሄዱን አጥወልውሏታል።

ሂደቱን አመቻችቶ የኤርትራ ሰራዊት በመግባባት ከትግራይ እንዲወጣ እያደረገ ያለው አገር በቀል ድርጅት፣ ተግባሩን እያከናወን መሆኑንን አምኖ ለጊዜው ስሙ እንዳይጠቀስ ጠይቋል። ይህም የሚሆነው የተጀመረው ስራ እንዳይበለሽ ነው ሲል ለኢትዮ አስራ ሁለት ነግሯል።

አሜሪካ አሁን ላይ በፕሬዚዳንት ኢሳያስ ላይ የጠና አቋም መያዟ ትህነግን እንደ ምክንያት መጠቀሚያ ማድረጓን ይኸው ድርጅት አመልክቷል።

“(ትህነግ) በቅርብ ያለ ልምጭ ነው” ነው ሲሉ አስተያየት የሰጡ የድርጅቱን ሃሳብ ያጠናክራሉ። አሜሪካም ሆኑ አውሮፓውያን የቀይ ባህር ጉዳይ ላይ ፕሬዚዳንት ኢሳያስ ያሳዩት ዳተኛነት በዋናነት፣ በአገራቸው ላለፉት 30 ዓመታት የተከተሉት ዘመኑንን የማይመጥን አገዛዝ፣ ምርጫ፣ ሕገመንግስት፣ ነጻ ሚዲያ፣ የተቃዋሚ ፓርቲ አለመኖር፣ እስር፣ አፈና … የመሳሰሉትን ዋና ጉዳዮች አስመክቶ ለውጥ ለማካሄድ ቃል ገብተው በተግባር አለማዋላቸው ማነቆው እንዲጠብቅባቸው እንዳደረገ ይገልጽሉ። በዚ መመሻ ተንተርሰው የቆየ ቂማቸውን ለመወጣት አሁን በትግራይ የተፈጠረው ቀውስ ጥሩ ምክንያት ሆኖ ተገኝቷል። ይህን የኖረ ቂም ነው አብይ አህመድ እንዲተርጉ የተጠየቁት።

ከአሜሪካው ልዩ መልዕተኛ ፊልትስ ማን ጋር የ5 ሰዓታት ውይይት ያደረጉት ኢሳያስ ከትግራይ ለመውጣት ያስቀመጡት ቅድመ ሁኔታ የደህንነት ስጋት ነበር። ኢትዮ 12 እንደሰማችው ኢሳያስ በኢትዮጵያና በኤርትራ ድንበር መካከል ሰላም አስከባሪ እንዲመደብ ጠይቀው ነበር። ግን ተቀባይ አልሆነም። በተቃራኒው አሜሪካ በመላው ትግራይ የሰላም አስከባሪ ለማሰማራት አስባ ኢትዮጵያ አይሆንም ብላለች።

የተባበሩት መንግስታት የጸጥታው ምክር ቤት በመጨረሻ ውሳኔው የኢትዮጵያን ሉዓላዊ አገርነት፣ሉዓላዊ ክብርና ውሳኔ እንደሚያከብሩ ገልጸው መግለጫ ማሰራጨታቸው፣ አመሪካና እንግሊዝ ሰላም አስከባሪ ለማስገባት ያላቸውን ፍላጎት ውሃ ደፍቶበታል።

ሲንከባበል ቆይቶ የጉዞ ፣ የድህነትና የኢኮኖሚ ማዕቀብ ላይ የደረሰው የማስገደዱ ዘመቻ በፕሬዚዳንት ኢሳያስና ጠቅላይ ሚኒስቴር አብይ መካከል ጸብ እንዲያስነሳ ድግስ ስለመሆኑ ፍንጭ የነበሩ ጉዳዮች ዛሬ ወደ እውነትነት እየተቀየሩ ይመስላል።

አብይ አሕመድ “ በተከዳን ጊዜ” ሲሉ ትህነግ የአገር መከላከያ ላይ በድንገት ጥቃት ሲከፍት ከሞትና ከመታረድ የተረፈው ሰራዊት ሲበተንና እርቃቅኑን ወደ ኤርትራ ምድር ሲዘልቅ የተደረገለትን በማስታወስ “አንዳንዶች ኤርትራን እንድንሰድብ ይፈልጋሉ፤ አይሆንም” ማለታቸው የሚታወስ ነው።

ይህ አቋም ዛሬ ኢትዮጵያ ከአሜሪካ ጋር ከገባችው አጣብቂኝ አንጻር የት ድረስ ይዘልቃል? የሚለው እያነጋገረ ባለበት በአሁን ወቅት ነው “በሰላማዊ መንገድ፣ ጉርብትናና ወዳጅነት ሳይፈርስ ኤርትራ ሰራዊቷን ታስወጣለች፤ ጉዳዩን ለኛ ተውት” የሚሉ ወገኖች የተነሱት።

አንዳንድ አፍቃሪ ትህነግ የሆኑ እንደሚሉት አሜሪካ ያቀረበችው የድርድርም ሆነ ይፈጸም የምትላቸው ጉዳዮች ለኢትዮጵያ መንግስት ከባድ አይደለም። እንደ እነዚሁ ሰዎች ገለጻ ኢትዮጵያ የኤርትራ ሰራዊትን ብታስወግድ በቀላሉ ከገባችበት አጣብቂኝ ትወጣለች።

ዋናውን ሚስጢር፣ ነገር ግን ገሃድ ጉዳይ የሚዘሉት እነዚህ ክፍሎች የአማራ ክልልን አዲስ አበባ ሆነው  “ ወራሪ” ሲሉ ይጠራሉ። ለትህነግ የሚከራከሩትን ያህል ለወላቃይት ህዝብ ውሳኔና ለራያ ሕዝብ ማንነት እኩል እውቅና መስጠት አይፍለጉም። የማይካድራን ጭፍጨፋ በጭራሽ አያነሱም።

ለኦሮሞ ተቆርቋሪ ሆነው የሚቀርቡት እነዚህ አዲስ አበባ ሆነ የሚያሰራጩት፣ አቶ ጌታቸው ረዳ ከበረሃ የሚናገሩትና ነጮቹ በመግለጫቸው የሚያወጡት አንድ መሆኑ ጉዳዩ የተሳሰረና የተጋመደ መሆኑንን ያመላክታል። ይህ እስከ ታተመ ድረስ ኢትዮጵያን ኤርትራ ” እስከ ቀራኒዮ” ያሉ ይመስላል። የአፍሪቃ ቀንድ ለውጥ አስለተው በኢሳያስና በአብይ መቃብር ላይ አዳዲስ የሃይል አሰላለፍ እየነደፉ የሚጽፉም እየታዩ ነው።


Exit mobile version