Site icon ETHIO12.COM

ኢትዮጵያ ዝቅተኛ የደመወዝ ወለልን የሚወስነውን ቦርድ ልታቋቁም ነው

በኢትዮጵያ የዝቅተኛ የደመወዝ መጠንን የሚወስነው የደመወዝ ቦርድ ሊቋቋም መሆኑን ቢቢሲ ከሠራተኛና ማኅበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴርና ከኢትዮጵያ ሠራተኛ ማኅበራት ኮንፌዴሬሽን ካገኘው መረጃ መረዳት ችሏል።

በአሁኑ ወቅት የዝቅተኛ ደመወዝ ወለልን የሚወስነው ቦርድ ማቋቋሚያ ደንብ የተረቀቀ ሲሆን በሠራተኛና ማኅበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴር የበላይ ኃላፊዎች ምክክር ሲደረግበት ቆይቶ ደንቡ ወደሚፀድቅበት ወደ ሚኒስትሮች ምክር ቤት ለመላክ በዝግጅት ላይ ነው ተብሏል።

ይህ ቦርድ በኢትዯጵያ እስካሁን ድረስ ሲሰራበት የነበረው በአሰሪና ሠራተኞች ስምምነት የሚወስኑትን የአከፋፈል ሁኔታ በመቀየር የደመወዝ መጠን ላይ የሚወስን መሆኑን አቶ ፍቃዱ ገብሩ በሠራተኛና ማኅበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴር የሰላማዊ ኢንዱስትሪ ግንኙነት ዳይሬክተር ለቢቢሲ ተናግረዋል።

ይህ ዝቅተኛ የደመወዝ ወለል የሚመለከታቸው ሠራተኞች ከተቀመጠው በታች እንዳይሆን የሚያደርግ ሲሆን፤ የቅጥር ግንኙነት ባለበት ሁሉ የሚሰራ ይሆናል። ደንቡ በአሁኑ ሰዓት በመጠናቀቅ ላይ ሲሆን ከዚያ በኋላም የቦርዱ መቋቋም የሚቀጥል ይሆናል።

የዝቅተኛ የደመወዝ መጠን ምን አይነት ሁኔታዎችን ማካተት ይገባዋል? በምንስ ይወሰን? የሚሉትን ሁኔታዎች የሚወስነው ይህ ቦርድ በአራት አካላት የሚዋቀር ነው። አባላቱም በዋነኝነት ሠራተኞችና አሰሪዎች፣ መንግሥት፣ እንዲሁም የሲቪክ ማኅበራት የሚካተቱበት ይሆናል።

የሲቪክ ማኅበራት የሚባሉት የባለሙያዎች ማኅበራት ሲሆኑ ለምሳሌም እንደ ኢትዮጵያ የኢኮኖሚ ባለሙያዎች ማኅበርና የከፍተኛ የትምህርት ተቋማትን የመሳሰሉት በዚህ ቦርድ ውስጥ ተሳታፊ እንደሚሆኑ አቶ ፍቃዱ ይናገራሉ።

የደመወዝ ቦርዱ ዝቅተኛውን ወለልን የሚወስነው የባለሙያዎቹ ማኅበራት የሚያቀርቧቸውን መረጃዎችና የተለያዩ ጥናቶችን ግብአት በማድረግ፤ በተለይም በአገሪቱ ማክሮ ኢኮኖሚ ላይ ሊያመጣ የሚችለውን ተፅእኖ በጥልቀት በማየት እንዲሁም የአሰሪዎችና ሠራተኞቸን ጥቅሞች ከግምት ውስጥ በማስገባት እንደሆነ አቶ ፍቃዱ ያስረዳሉ።

አቶ ፍቃዱ እንደሚሉት ምንም እንኳን የአገሪቱን ሁኔታ በጥልቀት በማየት ዝቅተኛ የደመወዝ መጠን ቢወሰንም በመርህ ደረጃ ግን ዓለም የሚከተላቸውን መሰረታዊ ጉዳዮች የሚያካትት ይሆናል።

እነዚህ መሰረታዊ የሚባሉትም ሠራተኞቻቸውና ቤተሰቦቻቸው ለመኖር የሚያስፈልጋቸው መጠን እንዲሁም በሌላ በኩል ኩባንያዎች፣ ተቋማትና አሰሪዎች የመክፈል አቅም ምን ይመስላል የሚለውን ያጤናል ይላሉ።

የኢትዮጵያ ሠራተኛ ማኅበራት ኮንፌዴሬሽን ፕሬዚዳንት አቶ ካሳሁን ፎሎ በበኩላቸው ደንቡ ወደ ከሠራተኛና ማኅበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴር ከመላኩ በፊት ከመንግሥት፣ ከሠራተኞችና ከአሰሪዎች እንዲሁም ሌሎች የሚመለከታቸው አካላትን በማካተት የሦስትዮሽ ምክክርና ውይይት ተደርጎበታል ይላሉ።

እንደ ሠራተኛ ማኅበር የራሳቸውን ጥናት እያካሄዱ ቢሆንም ሠራተኞችን በመወከል በዋነኝነት አንድ ሠራተኛ በደመወዙ መኖር መቻል አለበት የሚለውን ፅንሰ ሃሳብ የያዘ ነው ይላሉ።

ዝቅተኛ የደመወዝ ወለል የአንድን ሠራተኛ የኑሮ ደረጃ የቤት ኪራይ፣ መብራት፣ ውሃ፣ የትምህርት ቤት ክፍያ እንዲሁም ሌሎች ወጪዎች ተደምረው ለአንድ ሰው ኑሮ በአማካይ ምን ያህል ይበቃል የሚለው ከግምት ውስጥ መግባት አለበት ይላሉ።

በዚህም አንድ ሠራተኛ ራሱን አስተዳድሮ በአማካኝ ሦስት ወይም አራት ልጅ ማሳደግ የሚችልበት መጠን ሊሆን ይገባል ይላሉ። 

እንደ ምሳሌም የሚያነሱት በኢትዮጵያ ባሉ ኢንዱስትሪ ፓርኮች ተቀጥረው የሚገኙትን ሠራተኞችን ነው። አብዛኞቹ ከ750 አስከ 1000 ብር በወር ተቀጥረው የሚሰሩ ሠራተኞችን ጉዳይ “አሳዛኝና ሊሻሻል የሚገባው” ስለመሆኑ ማሳያ እንደሆነ ይጠቅሳሉ።

“አብዛኛው ሠራተኛ ምሳ በልቶ እራት መድገም የማይችል ነው። አንድ ሺህ ብር በኢትዮጵያ የኑሮ ሁኔታ ውስጥ ገበያ ተወጥቶ ምንም አይገዛም። አንድ ሳምንትም የሚያቆየው አይደለም። ከዚህ አንፃር እነዚህ ነገሮች ይሻሻላሉ ብለን እንጠብቃለን። ቢያንስ ሌላ ነገር ማድረግ ባይችል በልቶ ማደር ይችላል” ይላሉ።

እነዚህንም ግምት ውስጥ ማስገባት አለበት የሚሉት አቶ ካሳሁን ይህም ሁኔታ በባለሙያዎች ተጠንቶ ግብዓት ይሆናል ይላሉ።

“ሆኖም ጉንጭ አልፋ ክርክር ሳይሆን መሬት ላይ ያለው ሳይንሳዊ ነገርን የተከተለ ነገር መኖር እንዳለበት በኛ በኩል ስንከራከርም፣ ስንወያይም፣ ስንመካከርም እሱን መሰረት አድርጎ ስለሚሆን ይሄንን ጥናት እያካሄድን ነው ያለነው” ይላሉ።

አቶ ፍቃዱም በበኩላቸው የደመወዝ ቦርዱ ሠራተኞች ማግኘት የሚገባቸውን ብቻ ሳይሆን ኩባንያዎች መክፈል የሚችሉበትን ሚዛናዊነቱን በጠበቀ መልኩ የሚደራደሩበት መድረክ እንደሚሆን ያሰረዳሉ። 

መንግሥትም በነዚህ አካላት ላይ የማደራደር ሚና የሚኖረው ሲሆን በመጨረሻም ሠራተኞችና አሰሪዎች የተስማሙበት እንዲሁም ባለሙያዎች ጥናት ያደረጉበት ሆኖ በሕግነት ይፀድቃል ይላሉ።

በተለይም እነዚህ ባለሙያዎች በማክሮ ኢኮኖሚው ላይ ይህ ቢወሰን ምን ያመጣል የሚለውን ነፃ አስተያየት እንዲሰጡ የማድረጉ ጉዳይ ትኩረት ሊሰጠው እንደሚገባ ይጠቁማሉ። 

በኢትዮጵያ ውስጥ በአጠቃላይ የማይቀጠረው ሰው 80 በመቶ ሲሆን የእርሻ ዘርፉ በአብዛኛው ከኢ-መደበኛ የሚመደብ ሲሆን በቤተሰብ ደረጃ የሚከናወን ነው። 

ገበያው ላይ የኢ-መደበኛውና መደበኛ ቅጥሩ ላይ ገበያ ያላቸው ተፅእኖና መመጣጠን ሊታይ ይገባዋል ይላሉ። እንደ ምክንያትነትም የሚያቀርቡት “ደመወዝ ተከፋዮችና ደመወዝ የሌላቸው ግለሰቦች በገበያው ላይ እኩል ተሳትፎ ስላላቸው ነው” ይላሉ።

ከዚህም በተጨማሪ እነዚህ ባለሙያዎች በአገሪቷ የወቅቱ ሁኔታ ለምሳሌ ግሽበት፣ የገበያ መዋዠቅ፣ ወረርሽኞችንና ሌሎች ጉዳዮችን ከግምት ውስጥ በማስገባት ክለሳ የማድረግ ሥራ ወቅቱን የሚቋቋምበት ሁኔታ ሊሰራ እንደሚገባ የሚጠቁሙት አቶ ፈቃዱ፤ በተለይም አገሪቱ እያለፈችበት ካለችው የዋጋ ግሽበት ጋር ተያይዞ ዝቅተኛ የደመወዝ ወለልን መወሰን አስፈላጊ ነው ይላሉ።

“ሠራተኛው የመግዛት አቅሙ ወርዷል። ሠራተኛው አሁን በሚያገኘው ደመወዝ መግዛት አልቻለም። በልቶ ማደር አይችልም” ብለዋል።

ዝቅተኛ የደመወዝ ወለል የሚመለከተው በአገሪቱ አሰሪና ሠራተኛ አዋጅ የሚተዳደሩትን ወይም በቀጣሪና በቅጥር ግንኙነት ያሉትን ነው። 

በአጠቃላይ መደበኛ የሆነውን የሥራ ዘርፍ ላይ የተሰማሩ የግል ዘርፉ ኩባንያዎች፣ ተቋማት እንዲሁም የመንግሥት የልማት ድርጅቶችን ይመለከታል። 

ዝቅተኛ የደመወዝ ወለሉ የመንግሥት ሠራተኞች (ሲቪል ሠራተኞችን) አያካትትም እንዲሁም ኢ-መደበኛ የሆነውን የሥራ ዘርፍንም እንደማያካትት አቶ ካሳሁን ያስረዳሉ።

የመንግሥት ሠራተኞችን ዝቅተኛ የደመወዝ ወለል ቦርዱ ለምን እንደማይወስን የሚናገሩት አቶ ፍቃዱ መንግሥት ቀጣሪ ስለሆነ ያው መንግሥት አትራፊ ስላልሆነ መሰረታዊ የሚባሉ ነገሮችን ወስዶ ነው የሚከፍለው ይላሉ።

BBC Amharic

Exit mobile version