Site icon ETHIO12.COM

24 ሠዓታት በወታደር ህይወትክፍል 6 – ትልልቅ ሰንጋ – በደረቅ ኮሾሮ – መከላከያ ላይ የተፈጸመ ግፉ አጀማመር

የእነሱ ክፍል አባላት ያሉበት ሥፍራ እንደደረሱ እሥረኛ መሆናቸው ተናግሯቸው ከበድ ያሉ ዕቃዎች ተሸክመው በሁለት ረድፍ በሚጓዘው ሠራዊት መሀል እንዲጓዙ ተነገራቸው።ያ ሁሉ የበዓል ዝግጅት ተሠርዞ ለምን በአስቸኳይ ሥፍራውን መልቀቅ እንደተፈለገ አልጠየቁም። ቢጠይቁም የሚመልስላቸው የለም። ምናልባትም በታችኛው ክፍል ደረጃ የሚያውቀው ላይኖርም ይችላል።ጉዞ በማታ እንደመሆኑ መጠን በዝግታ ነው።

የዚህ ታሪክ ባለቤት በአድዋ አካባቢ የትንሳኤ በዓልን እንዲያከብርና በሥልጠና የደከመ አእምሮውን ዘና እንዲያደርግ ተፈቅዶለታል። እናም ኮሚቴዎች ተዘጋጅቶ እንቅስቃሴ ተጀምሯል። እንግዲህ ቅኝቱ በዚህ ቀን 24 ሠዓታት ውስጥ የተከናወነውን ይዳስሳል።በዕለቱ የሠራዊቱ ወታደራዊ ክበቦች ያለ ወትሮው ቢራ አምጥተው፣ እዚያው ምሽግ ውስጥ የተፈጠረ በባህላዊ ፍሪጅ እንዲያቀዘቅዙ ተዘዋል።

በባህላዊ ፍሪጅ ጉድጓድ ቆፎሮ፣ ቢራዎች ጉድጓዱ ውስጥ በመክተት ጆኒያ አልብሶ ላዩ ላይ ውሃ ማርከፍከፍ ነው። ከሰዓታት በኋላ ቀዝቃዛ መጠጥ መጎንጨት ብቻ ነው፡፡በዋዜማው ከጥበቃ ነፃ የሆኑ አባላት አጎራባች ክፍሎች ካሉ ጓደኞቻቸው ተገናኝተው እየተጨዋወቱ ፣አንድ ሁለት እያሉ ነበር። እየጨመረ ሲሄድ ፀቦች እየተፈጠሩ ወታደራዊ ፖሊሶች ላይ ሥራ አበዙ።የፀቡ ምክንያት ግን በአብዛኛው የወጣቶቹን ብዙ የመጠጥ ልምድ ያለመኖርና ለበርካታ ወራት አሊያም ከዓመት በላይ ከምንም ዓይነት መሠል መዝናኛ ርቆ በሥራ መቆየትን የሚያመለክት ነበር።

ከሁለቱ ኮከቦች የትኛው የበለጠ ያምራል ዓይነት ነገር። በርግጥ ጥቂት ሲቪል የክበብ አስተናጋጆችም የፀቡ መንስኤ እንደነበሩ መካድ የትረካውን ተዓማኒነት ያጎድላል።ለበዓሉ ዝግጅት መቶዎች የራሳቸውን ኮሚቴ ያዘጋጃሉ ብለናል። ታዲያ አንዷ የመቶ የሚገዛው ነገር የተሻለ ይሆን ዘንድ አንዱን የአካባቢው ማለትም የአድዋ ተወላጅ የግዥ ኮሚቴው አባል ያደርጋሉ። ወቅቱ ጦርነት ስለነበር ቅርብ ሆነ ሩቅ የቤተሰብ ፍቃድ አይፈቀድም።

የጦርነቱ ወቅት እየተቃረበ ሲመጣ ለምስጢር ሲባል ፖስታም ተከልክሏል። እናም ይሄ የአካባቢው ተወላጅ የኮሚቴ አባል ለዓመታት ቤተሰቦቹን አይቶ አያውቅም። ከአፉ የማይጠፉት እናቱ አደይ ደግሞ በጣም ናፍቀውታል።አሥር ሠዓት ግዜያቸውን ጨርሶ ወደ ክፍሉ እንደሚደርሱ እቅድ ይዘው ስድስት ሠዓት አድዋ ከተማ ደረሱ።

“አንዴ በቁም እናቴን ዓይኗን አይቼ፣ እንዳታስብ እናንተን የመሣሠሉ ጓዶች እንዳሉኝ ነግሬያት እንመለስ’ የሚለው ልመናውን በፍፁም መቋቋም አልቻሉም። ምንም ወታደር ቢሆኑ የሀገር ፍቅር ከቤተሰብ ፍቅር ቢበልጥባቸውም እናት አላቸው። ያውም ኢትዮጵያዊት እናት።ሲደርሱ ግን ነገሮች ተገለባበጡ። አደይ አንድ ዓይነት ከጓደኞቹ ጋር የለበሰውንና በአብዛኛው በከባዱ ሥልጠና ምክንያት የተመሣሠለው ልጃቸውን እንደለዩ ጩኸታቸውን አቀለጡ።

ነገሩ ሲረጋጋ ወደ ቤት እንዲያስገቧቸውና እንዲያስተናግዷቸው ለሌሎች ሰጥተው ነጠላቸውን በማንጠልጠል ወደ ቤተክርስቲያን በረሩ።ዘመድ ፣ አዝመድና ጎረቤቱ ሰባቱን ጓደኛሞች አገላብጦ እስኪ ስሙ ሌሎቹ የመጠበትንና የቤተሰብ ሁኔታ ሲጠይቁ የመጡበትን አከባቢ የሚያውቅ ትውዝታውን ሲተርክላቸው ከቤትና ከጎረቤት የመጣው ጠላ አረቄ ታክሎበት ረጅም ሠዓት ወሰደ።

የትግራይ ህዝብ እንኳን የወለደው ልጁ ታክሎበት ዩኒፎርም የለበሰውን ሁሉ ሲያይ ስሜቱ ተመሣሣይ ነው። እንኳን ቤቱ ተገብቶ በመንገድም ጠላና ምግብ ይዞ ካልበላችው በፍቅር እያለ ያስቸግራል።ወደ ክፍላቸው በተባለው ሠዓት መመለስ ቀርቶ ከምሽቱ አንድ ሠዓት ድረስ ለወጥ መሥሪያ አስፈላጊ የሆኑ ሽንኩርት፣ ቲማቲምና ወዘት አልተገዙም ነበር።

ግማሹ ሞቅ ብሎት በተሳሰረ አንደበት የፈለገው ይምጣ እንኳንም አደ…ይን እምዬን እናቴን ተዋወቅሁ ብሎ የጓደኛውን እናት አንገት አቅፎ ማልቀስ ጀምረዋል።ግማሹም በተከፈተው ሙዚቃ አሰቡን ጥሎ ይደንሳል። ሳቅ – ለቅሶ ፣ ለቅሶ – ለቅሶ። የአድዋን ስዋ (ጠላ) ደግሞ የሚያውቀው ያውቀዋል።እንደምንም የአዋቂዎች ምክርና ተግፃፅ ተጨምሮበት፣ የሚገዛው ዕቃ ከሠፈር ተዋጥቶ፣ በአከባቢው ወጣቶች መንገድ መሪነት የጦር ሠፈራቸው ሲደርሱ ባዩት ነገር አባላቱ በአንድ ጊዜ ስካራቸው ብን ብሎ ጠፋ።ያ ሁሉ የበዓል ግርግር የለም።

ለመዝናኛ ክበብ ለስንቅና ትጥቅ ማስቀመጫ ለጋራ መመገቢያ ወዘተ የተሠሩ ድንኳኖች ፈርሰዋል። መፀዳጃ የለ ፣ የእርጥብ እና የደረቅ ቆሻሻ ማስወገጃ ጉድጓዶች ተደፍኗል።አባላቱ ሠፈራቸው የደረሱት ለበዓል የታረዱ በሬዎች ሥጋ እንዲቀበር፣ አስፈላጊ ዕቃዎች በተሽከርካሪ እንዲጫኑ ተነግሮ የሠው ሐይል ቁጥጥር ተደርጎ ወደ አልታወቀ ሥፍራ ለግዳጅ የእግር ጉዞ ለማድረግ ሠራዊቱ በቅደም ተከተል ጉዞ ለመጀመር ሠልፍ ከያዘ ቦኋላ ነው።

የእነሱ ክፍል አባላት ያሉበት ሥፍራ እንደደረሱ እሥረኛ መሆናቸው ተናግሯቸው ከበድ ያሉ ዕቃዎች ተሸክመው በሁለት ረድፍ በሚጓዘው ሠራዊት መሀል እንዲጓዙ ተነገራቸው።ያ ሁሉ የበዓል ዝግጅት ተሠርዞ ለምን በአስቸኳይ ሥፍራውን መልቀቅ እንደተፈለገ አልጠየቁም። ቢጠይቁም የሚመልስላቸው የለም። ምናልባትም በታችኛው ክፍል ደረጃ የሚያውቀው ላይኖርም ይችላል።ጉዞ በማታ እንደመሆኑ መጠን በዝግታ ነው።

ከኋላና ከፊት መልዕክት ይተላለፋል። ከፊት አብሪ ከጎንና ጎን ጥበቃ አለ። ቁጢጥ ሲባል ሠልፉ ወደ ተቃራኒ አቅጣጫ ዞሮ አባላቱ በመቀመጫቸው መሬት ሳይነኩ እግራቸው ላይ ቁጢጥ ይላሉ። እንዲህ እያሉ ሲነጋ አባላቱ እራሳቸውን ያገኙት ሴሮ የተበለ የውሃ ነጥብ ያለበት ሰፊና በሳር የተሸፈነ ሥፍራ ላይ ነው።

ለትንሽ ሠዓታት እረፍት ተደረገና ጦሩ ተጣጠበ። ለትልልቅ ሰንጋ የተዘጋጀው ሆድ እራቡን በደረቅ ኮሾሮና እስቃጥላ አስታገሰ። እናም ጉዞው ቀጠለ። በቀን ጉዞው እነሱ በሚጓዙበት አቅጣጫ ሌላ ክፍል ይጓዟል። የሚተዋውቁት ምናልባትም ከዓመት በላይ የተለያዩ የሠፈር ልጆችም ሆኑ ዘመዳሞች በድንጋጤ ሲተያዩ በናፍቆት ውስጥ ሆነው ለሰከንዶች የእጅ ሠላምታ ተሰጣጥቶ ከማለፍ ውጭ ሌላ ዕድል አልነበራቸውም። የወታደር ህይወት ፍቅር ፣ መተሳሰብ እኔ ልቅደም ፣ ፍጹም ወንድማዊ ቤተሰባዊነት ፡፡

በሌላ የ24 ሠዓታት ትረካ እንገናኛለን። ሻለቃ ፈይሳ ናኔቻ

መከላከያ ፊስ ቡክ


Exit mobile version