Site icon ETHIO12.COM

በመቐለ ከተማ መደበኛ የመማር ማስተማር ሥራ ተጀመረ


በመቐለ ከተማ የሚገኙ የመንግስትና የግል ትምህርት ቤቶች መደበኛ የመማር ማስተማር ሥራ ዛሬ መጀመራቸውን በክልሉ ጊዜያዊ አስተዳደር የከተማው ትምህርት ጽህፈት ቤት አስታወቀ።

የጽህፈት ቤቱ ተወካይ ወይዘሪት ገነት መብራቱ ለኢዜአ እንዳሉት፤ የመማር ማስተማር ሥራው የተጀመረው በከተማዋ በሚገኙ 32 የመንግስት እና ከ30 በላይ የግል ትምህርት ቤቶች ነው።

ትምህርት ቤቶቹ የመማር ማስተማር ሥራውን የጀመሩት ቀደም ሲል ከመምህራን፣ ከወላጆችና በየደረጃው ከሚገኙ የመንግስት አመራት አካላት ጋር መግባባት ላይ በመደረሱ እንደሆነ ገልጸዋል።

የትምህርት ቁሳቁስ ችግር ላለባቸው ተማሪዎች ድጋፍ እየተደረገ መሆኑን አመልክተው ጉዳት የደረሰባቸው ትምህርት ቤቶችን የማስተካከልና በቁሳቁስ የማሟላት ሥራ መከናወኑን አስታውቀዋል።

በመቐለ በሚገኙ ሰባት ክፍለ ከተሞች ውስጥ መደበኛ ትምህርቱ ሲጀመር ሁሉም መምህራን መገኘታቸውን የገለጹት ወይዘሪት ገነት፤ ተማሪዎችም እየገቡ መሆኑን መናገራቸውን ኢዜአ ዘግቧል።

Exit mobile version