ETHIO12.COM

ቦሌ ከዓመት በላይ ጸሃይና ምግብ ተከልክላ፣ አየተቆለፈባት፣አየተበደበች የኖረችው አህት ነጻ ወጣች

ፖሊስ ወደ ስፍራው ሲደርስ ተጠርጣሪዋ ሰራተኛ እንደሌላት በመናገር ልትደብቃት ብትሞክርም ሰራተኛዋ ግን አልጋ ውስጥ ሆና ስትጮኽ ፖሊስ በመስማቱ ከስቃይ ሊያድናት እና አሰሪዋንም በቁጥጥር ስር ሊያውላት መቻሉን አቶ ዮሐንስ ገልፀዋል።

በቦሌ ክፍለ ከተማ የቤት ሰራተኛዋን በአሰቃቂ ሁኔታ ከ1 ዓመት በላይ ከቤት እንዳትወጣና የፀሃይ ብርሃን እንዳታገኝ በማድረግ፣ ምግብ በመከልከል ከፍተኛ ድብደባ ስትፈፅም የነበረች ተጠርጣሪን በቁጥጥር ስር ማዋሉን ፖሊስ ተገለፀ።

የወንጀል ድርጊቱ የተፈፀመው በክፍለ ከተማው ወረዳ 8 ሲ.ኤም.ሲ አልታድ መንደር ተብሎ በሚጠራው አካባቢ ነው፡፡ የቦሌ ክፍለ ከተማ ፖሊስ መምሪያ የሴቶችና ህፃናት ወንጀል ምርመራ ማስተባበሪያ ኃላፊ ረዳት ኢንስፔክተር ኤርሚያስ ጋቸኖ እንደገለፁት አንዲት ግለሰብ በቤት ሰራተኝነት የቀጠረቻትን የ20 ዓመት ወጣት በተደጋጋሚ በመደብደብ፣ ምግብ በመከልከል፣ በር በመቆለፍ ከቤት እንዳትወጣ እና የፀሃይ ብርሃን እንዳታይ እያደረገች ስትበድላት ቆይታ የቤቱ አከራይ ለፖሊስ በሰጡት ጥቆማ በቁጥጥር ስር ውላ ምርመራ እየተጣራባት ይገኛል።

የግል ተበዳይ የሆነችው ወጣት ጥሩአለም ደጉ በቤት ሰራተኝነት ከተቀጠረች ጊዜ ጀምሮ ለ1 አመት ከ2 ወር ያህል ከባድ የሆነ ስቃይ ሲደርስባት እንደነበር በመግለፅ ፖሊስ ደርሶ ህይወቷን እንዲያተርፍላት ለቤቱ አከራይ በአጋጣሚ ባገኘችው የመስኮት ቀዳዳ ወረቀት ፅፋ መስጠቷን ተናግራለች ።

የቤቱ አከራይ አቶ ዮሐንስ ኃ/ጊዮርጊስ በበኩላቸው ሰራተኛዋን የተቀጠረች ቀን ብቻ ማየታቸውንና በተደጋጋሚ ያስቀጠራትን ደላላ ስለ ልጅቷ ጉዳይ መጠየቃቸውን ተናግረው በወረቀት ተፅፎ በመስኮት የተወረወረላቸውን መልዕክት ካገኙ በኋላ ለአቅራቢያቸው ፖሊስ ጣቢያ መጠቆማቸውን ገልፀዋል፡፡

ፖሊስ ወደ ስፍራው ሲደርስ ተጠርጣሪዋ ሰራተኛ እንደሌላት በመናገር ልትደብቃት ብትሞክርም ሰራተኛዋ ግን አልጋ ውስጥ ሆና ስትጮኽ ፖሊስ በመስማቱ ከስቃይ ሊያድናት እና አሰሪዋንም በቁጥጥር ስር ሊያውላት መቻሉን አቶ ዮሐንስ ገልፀዋል።

ህብረተሰቡ በአካባቢው የሚፈፀሙ የወንጀል ድርጊቶችን ለፀጥታ አካላት ሊጠቁምና በሴቶች ላይ የሚፈፀሙ ጥቃቶችን ለመከላከል አካባቢውን በንቃት ሊመለከት እንደሚገባ ረዳት ኢንስፔክተር ኤርሚያስ ጋቸኖ መልዕክታቸውን አስተላልፈዋል፡፡ ዘገባ፡- ምክትል ሳጅን አዳነ ደስታ


Exit mobile version