የጉምሩክ ኮሚሽን ኮንትሮባንዲስቶች፣ የወንጀሉ ተባባሪ የኮሚሽኑ ሰራተኞችን እና የፖሊስ አባላትን በቁጥጥር ስር ማዋሉን አስታወቀ

የጉምሩክ ኮሚሽን ከፌደራል ፖሊስ ጋር በመተባበር ከ3 ወር በላይ የፈጀ የኦፕሬሽን ስራ በመስራት የኮንቶሮባንድ እቃዎች፣ ኮንትሮባዲስቶችንና ተባባሪዎቻቸውን በቁጥጥር ስር ማዋሉን ኮሚሽነር አቶ ደበሌ ቀበታ በዛሬው ዕለት በሰጡት መግለጫ አስታውቀዋል፡፡

ኮንትሮባዲስቱ በአዋሽ መቆጣጠሪያ ጣቢያ የፌደራል ፖሊስ ሀላፊ የሻለቃ አዛዥ የሆነ ግለሰብን በጥቅም በመደለልና ከፌደራል ፖሊስ አባላትና እና ከአዋሽ ጉምሩክ ቅ/ጽ/ቤት ሁለት ሁለት ሰዎችን መልምሎ እንዲያሰማራ በመመሳጠር የኮንትሮባንድ እቃዎችን በቀላሉ ለማሳለፍ እየሰራ መሆኑን ጥቆማ የደረሰው የጉምሩክ ኮሚሽን፣ ሚስጥራዊነቱ የተጠበቀ የኦፕሪሠሬሽን ስራ ለ3 ወር በመስራት መጋቢት 23 /2013 ዓም የኮንትሮባንድ እቃዎቹ፣ ኮንትሮባንዲስቶች እና ተባባሪዎቻቸው ጭምር በቁጥጥር ስር መዋላቸው ተገልጿል፡፡

በዚህም 6 ሚሊዮን 196 ሺ ብር ግምታዊ ዋጋው ያለው ልባሽ ጨርቅና ተስማሚነቱ ያልተረጋገጠ የፊት ክሬም፣ 3 የፌደራል ፖሊስ አባላት፣ ዋናው ኮንትሮባንዲስት እና የኮንትሮባንድ እቃውን ሲያጓጉዝ የነበረ ሾፌር፣ አንድ የአዋሽ ጉምሩክ ቅ/ጽ/ቤት ሰራተኛ፣ ኮንትሮበዲስቱ እንዳይያዝ ሽፋን ሲሰጥ የነበረ አንድ የመተሃራ ፖሊስ አዛዥ በድምሩ 7 ተጠርጣሪዎችን በቁጥጥር ስር ማዋል መቻሉ ነው የተገለጸው፡፡

በጉቦ መልክ ሊሰጥ የነበረ 2 መቶ ሺ ብርም በቁጥጥር ስር ውሏል ተብሏል፡፡ኮሚሽኑ ስርቆት ትንሽ የሌለው መሆኑን በማመን እነዚህ ከውስጥና ከውጭ ተደራጅተው ለስርቆት የተባበሩት አካላት በዚህ አፕሬሽን በቁጥጥር ባይውሉ ኖሮ ነገ ትላልቅና ሀገር ጎጂ የኮንትሮባንድ ዕቃዎችን ላለማመላለሳቸው ዋስትና የለም ብሏል በመግለጫው፡፡

የጉምሩክ ኮሚሽን ባለፉት 8 ወራት ብቻ 2.2 ቢሊዮን ብር በላይ ግምታዊ ዋጋ ያላቸው ልዩ ልዩ የገቢና የወጭ የኮንትሮባንድ እቃዎችን በቁጥጥር ስር ማዋሉ የተገለጸ ሲሆን፣ ይሄኛውን ልዩ የሚያደርገው ኮንትሮባድን ይቆጣጠራሉ ተብለው ሀላፊነት የተሰጣቸው አካላት በስርቆቱ ተሳታፊ መሆናቸውና በአንጻሩ ሀላፊነታቸውን በአግባቡና በታማኝነት እየተወጡ ባሉ የጉምሩክ ኮሚሽንና የፌደራል ፖሊስ አባላት ባደረጉት ክትትል የኦፕሬሽን ስራው መሳካት መቻሉ ነው ተብሏል፡፡

የጉምሩክ ኮሚሽን ኮሚሽነር አቶ ደበሌ ቀበታ ሀገርና ህዝብ የጣለባቸውን ሀላፊነት ለመወጣት ከፍተኛ ዋጋ ለከፈሉ የአዋሽ ጉምሩክ ቅ/ጽ/ቤት አመራሮችና ሰራተኞች፣በኦፕሬሽኑ ለተሳተፉ የፌደራል ፖሊስ ምርመራ ቢሮ እና የወንጀል መከላከል ዘርፍ፣ስራውን ከመጀመሪያ ጀምሮ በማቀድና በመምራት ለውጤት ላበቁት የጉምሩክ ህግ ማስከበር ዘርፍና የኢንተለጀንስ አመራሮችና ባለሙያዎችን ምስጋና ማቅረባቸውን ከገቢዎች ሚኒስቴር ያገኘነው መረጃ ያመለክታል፡፡

See also  ሰበር መረጃ - ትህነግ ወልቃይትና ራያ በጊዜያዊነት በፌደራል መንግስት እንዲተዳደሩ ሃሳብ አቀረበ

Leave a Reply