Site icon ETHIO12.COM

በህወሃት የሽብር ቡድን አባላት ሀብቶች ላይ ተጨማሪ ጥቆማ እንዲደረግ ጥሪ ቀረበ።

የሕወሃት የሽብር ቡድን አባላት የሆኑ ንብረቶችን በኪራይ፣በዉክልና በሌሎች መንገዶች ተይዘው በሚገኙ ሀብቶች ላይ ጥቆማ እንዲቀርብ ፌዴራል ጠቅላይ ዐቃቤ ሕግ ጥሪ አቀረበ፡፡

የሕወሃት የሽብር ቡድን አባላት፣ በራሳቸዉ በቤተሰቦቻቸዉና በቅርብ ሰዎች ስም የያዙት በአዲስ አበባና በሌሎች የክልል ከተሞች የሚገኝ ንብረት ላይ ማቅረብ እንደሚቻል ፌዴራል ጠቅላይ ዐቃቤ ሕግ ጠይቋል፡፡

የፌዴራል ጠቅላይ ዐቃቤ ሕግ የህወሃት የሽብር ቡድን በመከላከያ ሠራዊታችን የሰሜን ዕዝ ላይ ጥቃት ከፈጸመበት ማግስት ጀምሮ በጥፋት ቡድኑና አባላቱ ላይ የወንጀልና የሃብት ምርመራዎች ሲያከናዉን የነበረ መሆኑ ይታወቃል፡፡

በወንጀል የተገኘና በአገር ዉስጥ ወይም በዉጭ አገር የተደበቀ ሀብት ላይ ጥቆማ እንዲቀርብ ባቀረብነዉ ጥሪ መሰረት ከሕዝብ የተሰጡ ብዛት ያላቸዉ ጥቆማዎችና መረጃዎችን መሰረት በማድረግ የአሸባሪ ድርጅቱንና አባላትን ሃብት ጨምሮ በተደረገዉ የማጣራት ሥራ በርካታ ዉጤቶች ተመዝግበዋል፡፡

ለዚህም ተቋማችን ለሕዝቡ ከፍተኛ ምስጋና ያቀርባል፡፡ በአሁኑ ወቅት በሕወሃት የሽብር ቡድን አባላት ፣ በቤተሰቦቻቸዉና በቅርብ ሰዎች ስም በአዲስ አበባና በሌሎች የክልል ከተሞች ያሉ የማይንቀሳቀሱና ተንቀሳቃሽ ቋሚ ንብረቶችን በአካል በመለዬት የጥፋት ቡድኑ ንብረቶችንና ከንብረቶቹ የሚገኘዉን ገቢ ለሽብርና ሌሎች ወንጀሎች መጠቀም እንዳይችል ከሚመለከታቸዉ አካላት ጋር በመቀናጀት ሰፊ የመከላከል ሥራ እየተሰራ ይገኛል፡፡

ለፋይናንስ ደህንነት ማዕከል (FIC)፣ የኢፌዴሪ መከላከያ ሚኒስቴርና የብሔራዊ መረጃና ደህንነት አገልግሎት ላሳዩት የሥራ አጋርነት ከፍ ያለ ምስጋና አቅርቧል፡፡ ሥራዉን አጠናክሮ ለማስቀጠልና የሽብርና ሌሎች በአገር ኢኮኖሚ ላይ የሚፈጸሙ ወንጀሎችን በአግባቡ ለመከላከል ተጨማሪ ጥቆማዎችን መቀበል አስፈላጊ ሆኖ ተገኝቷል፡፡

የሕወሃት የሽብር ቡድን አባላት የሆኑ ንብረቶችን በኪራይ፣ በዉክልና፣ በአደራ፣ በጠባቂነት ወይም በሌላ ማንኛዉም መንገድ ይዛችሁ የምትገኙ ሰዎች ይህ ማስታወቂያ ከተነገረበት ጊዜ ጀምሮ በ 7 (ሰባት) ተከታታይ የሥራ ቀናት ዉስጥ ለፌዴራል ጠቅላይ ዐቃቤ ሕግ ሪፖርት እንድታቀርቡ፣ የሕወሃት የሽብር ቡድን አባላት፣ በራሳቸዉ በቤተሰቦቻቸዉና በቅርብ ሰዎች ስም የያዙት በአዲስ አበባና በሌሎች የክልል ከተሞች የሚገኝ ንብረት አስመልክቶ ከሕዝቡ ተጨማሪ ጥቆማዎች በአካል፣ በስልክና በኢሜል እንዲቀርብ እየጠየቅን በአካል መቅረብ ለማይችሉ ጥቆማ አቅራቢዎች በሚከተሉት የስልክና ኢሜል አማራጮች ማቅረብ ትችላላችሁ፡-
ሰልክ ፡- +251112733154
Email: – assetrecovery@eag.gov.et

የሪፖርትና ጥቆማ ማቅረቢያ ቦታ ልደታ ከፍተኛ ፍርድ ቤት ግቢ ዉስጥ በሚገኘዉ የጠቅላይ ዐቃቤ ሕግ ሕንጻ 1ኛ ፎቅ በወንጀል የተገኘ ሀብት ማስመለስ ዳይሬክቶሬት ጄነራል ነዉ፣ለሚቀርቡ ተጨባጭ ጥቆማዎች መንግስት ለጠቋሚዎች ማበረታቻ የሚሆን ተመጣጣኝ ክፍያ የሚፈጽም መሆኑን ተገልጸዋል፡፡

የህወሃት የሽብር ቡድን አባላት የሆኑ ንብረቶችን በኪራይ፣ በዉክልና፣ በአደራ፣ በጠባቂነት ወይም በሌላ ማንኛዉም መንገድ ይዘዉ እያለ ሪፖርት የማያደርጉ አካላት በሽብር አዋጁና አግባብነት ባላቸዉ ሌሎች ሕጎች ተጠያቂ እንደሚሆኑ ጠቅላይ ዐቃቤ ሕግ አስታውቋል። መረጃው የፌዴራል ጠቅላይ ዐቃቤ ሕግ ነው

Exit mobile version