Site icon ETHIO12.COM

“አሜሪካ በትግራይ ክልል ያለው ቀውስ እንዲረጋጋ ፍላጎት የላትም” ኤርትራ

አሜሪካ በትግራይ ክልል ያለው ችግር እንዲረጋጋ ፍላጎት እንደሌላትና በተቃራኒ ችግሩ እንዲባባስ እያደረገች ነው ስትል ኤርትራ ወቀሳ መሰንዘሯ ተሰምቷል፡፡

የኤርትራው የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር መስሪያ ቤት ለተባበሩት መንግስታት ድርጅት የጸጥታው ምክር ቤት ትላንት ሰኞ በላከው ደብዳቤ ደብዳቤ እንደገለጸው የባይደን አስተዳደር በትግራይ ክልል ያለው ሁኔታ እንዳይረጋጋ ፍላጎት እንደሌለው መግለጹ ተዘግቧል፡፡

ለዚህም አሜሪካ ላለፉት 20 ዓመታት ለአሸባሪው ህወሃት ቡድን ስታደርግ የነበረውን ድጋፍ በማስታወስ ለችግሩ መከሰት ኤርትራን ተጠያቂ ማድረግም መሰረት የሌለው እንደሆነ ገልጿል፡፡የኤርትራ ውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ኦስማን ሳልህ ለተባበሩት መንግስታት ድርጅት የጸጥታው ምክር ቤት የጻፉት ደብዳቤ አሜሪካ በኢትዮጵያ የውስጥ ጉዳይ ላይ በምታደርገው ጣልቃ ገብነትና እየፈጠረች ባለችው ያልተገባ ጫና ተጨማሪ ችግር እንዲፈጠር እያደረገች መሆኑንና ችግሩ እንዳይቀረፍ እንቅፋት እየሆነች እንደሆነ የሚገልጽ ይዘት ያለው መሆኑን በዘገባው ተገልጿል፡፡

በተጨማሪም ኤርትራ ለተባበሩት መንግስታት ድርጅት የጸጥታው ምክር ቤት በላከችው ደብዳቤ ላይ አሜሪካ የሽብር ቡድኑ ቀደሞ ወደ ነበረበት ስልጣን ለመመለስ ፍላጎት እንዳላትም መግለጹ ተነግሯል፡፡

የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ ኦስማን ሳልህ የህወሃት ቡድን አሁን ሀገሪቱን እያስተዳደረ ያለውን የዶ/ር አብይ አስተዳደርን በዓለም አቀፉ ማህበረሰቡ ዘንድ አሉታዊ ገጽታ እንዲይዝ የሚያደርጉ የተዛቡ መረጃዎችን በማሰራጨት መወጠሩን ጠቅሰው የተባበሩት መንግስታት ድርጅት የጸጥታው ምክር ቤትም ፍትህን ማረጋገጥ የሚያስችሉ እርምጃዎች መውሰድ ይጠበቅበታል ብለዋል፡፡

ሚኒስትሩ አክለውም የአሜሪካ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር መስሪያ ቤት ሰሞኑን በኢትዮጵያና በኤርትራ ባለስልጣናት እና በወታደራዊ ሀላፊዎች ላይ የጣለውን የጉዞ ዕገዳ በተመለከተም ተገቢነት የጎደለው እና በሀገራት የውስጥ ጉዳይ ጣልቃ የመግባት አንዱ ማሳያ ሲሉ መተቸታቸውን አልጀዚራ በዘገባው አስነብቧል፡፡


Exit mobile version