Site icon ETHIO12.COM

“አርሶአደሩን ወደ እርሻው በመመለስ የደረሰውን ጉዳት እንዲያካክስና ከእርዳታ እንዲወጣ ታስቦ እየተሰራ ነው”


በትግራይ አርሶ አደሩ አርሶ በማምረት የደረሰውን ጉዳት በማካካስ ከእርዳታ መውጣት እንዳለበት ታስቦ እየተሰራ መሆኑን የትግራይ ክልል ጊዜያዊ አስተዳደር የግብርናና ገጠር ልማት ቢሮ ምክትል ቢሮ ኃላፊ አቶ ብርሃኔ አርዓያ ገለጹ፡፡

በምርት ዘመኑ አንድ ነጥብ አንድ ሚሊዬን አባወራ አርሶአደሮችን በግብርና ለማሳተፍ የተያዘው እቅድ እንዲሳካም ሁሉም ባለድርሻ የሚጠበቅበትን እንዲወጣ ጠይቀዋል፡፡

እንደ አቶ ብርሃኔ ገለጻ፤ ቢሮው የተፈጠረውን ችግር ለማቃለል እና ወደነበረበት ለመመለስ ለመስራት እንዲያስችለው በመጀመሪያ የደረሰውን ጉዳት ምን ያህል ነው በሚል ጥናት አድርጓል፡፡ በዚህም በአምስት ዞኖች የጥናት ቡድን በመላክ እንዲለይ የተደረገ ሲሆን፤ የጥናት ቡድኑ በለየው መሰረትም በአብዛኛው በተለይም ገጠራማ አከባቢዎች ከፍተኛ ጉዳት እንደደረሰ ተረጋግጧል።

ቢሮውም የደረሰውን ውድመት መመለስ በሚያስችል መልኩ የአስቸኳይ እርዳታ እቅድ በማውጣት ለሚመለከታቸው አካላት (ለፌዴራል መንግስትም፣ ድጋፍ ለሚሰጡ አጋር አካላትም) አድርሷል፡፡

አጠቃላይ ግብርናውን ወደነበረበት ለመመለስ የተለያዩ ሥራዎች እየተከናወኑ መሆናቸውን ጠቅሰው፤ እስካሁን ባለው ሂደት ከወደብ መምጣት ከነበረበት 800ሺህ ማዳበሪያ ውስጥ 300 ሺው የደረሰ ሲሆን፤ ቀደም ሲል ከነበረው 214 ሺህ ኩንታል ጋር ሲዳመር ወደ 514 ሺህ ኩንታል ወደወረዳዎች እየተከፋፈለና እስካሁንም 210 ሺህ 795 ኩንታል ለገበሬው ደርሷል ብለዋል።

በወንድወሰን ሽመልስ (መቐለ)(ኢ.ፕ.ድ)

Exit mobile version