Site icon ETHIO12.COM

ግብጽና ሱዳን የሁለተኛው የውሃ ሙሌት ሳይካሄድ አስገዳጅ ውል እንዲፈረም ዓለምን ጫና እንዲፈጥር በጋራ ጥሪ አቀረቡ

ሱዳንና ግብጽ በካርቱም ከመከሩ በሁዋላ የዓለም አቀፉ ማህበረሰብ ኢትዮጵያ ላይ ጫና እንዲያደርግና ሁለተኛው የውሃ ሙሌት ከመጀመሩ በፊት አስገዳጅ ውል እንዲፈረም ጫና እንዲፈጥሩ የሚጠይቅ፣ ጥቃማቸውን ለማስከበር በጋራ እንደሚሰሩ የሚያስታውቅ መግለጫ አውጥተዋል።

ኢትዮጵያ ሁሌም ለድርድር የተዘጋጀች አገር መሆኗን፣ ግድቡም ሆነ የውሃው ሙሌት ሁለቱንም አገራት እንደማይጎዳ፣ የመጉዳትም ዓላማ እንደሌላትና ቁጥር ጠቅሳ ዜጎቿን መብራት ተተቃሚ ለማድረግ የያዘችውን ፍትሃዊ አቋም በምንም መልኩ የመቀየር ፍላጎት እንደሌላት ማስታወቋ ይታወሳል። ይህ አቋም የኢትዮጵያዊያን ሁሉ ነው።

ግድቡ በየዓመቱ ጎርፍ ለሚጠርጋት ሱዳን እጅግ ጠቃሚ እንደሆነ በራስዋ ምሁራን ሳይቀር የሚነገራትና ቀደም ሲል በአገር ደረጃ ከጥቅሟ አንጻር የኢትዮጵያ ወገን የነበረቸው ሱዳን ተገልብጣ የግብጽ አጋር ከሆነች በሁዋላ ድንበር በመውረር፣ ከግብጽ ጋር በየብስ፣ በአየርና በባህር የጦር ልምምድ በማድረግና ለጦርነት ዝግጅት በማድረግ ጫናውን ተባባሪ ከሆነች በሁዋላ አዲስ የያዘችው አቋም በውስጥ መከፋፈል መፍጠሩ እየተነገረ ነው። ቢቢሲ መግለጫውን እንዲህ አቅርቦታል።

ሁለቱ አገራት በከፍተኛ ባለሥልጣኖቻቸው አማካኝነት ካርቱ ም ላይ ተገናኝተው ከተወያዩ በኋላ ከኢትዮጵያ ጋር ከስምምነት እንዲደረስ ዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ ጣልቃ እንዲገባ ባወጡት መግለጫ ላይ ጠይቀዋል።

ሱዳንና ግብጽ የውሃ ሙሌቱ ከመጀመሩ በፊት ከኢትዮጵያ ጋር ግድቡን በሚመለከት ግዴታን የሚያስቀምጥ ሕጋዊ አሳሪ ስምምነት እንዲደረስ በተደጋጋሚ ሲጠይቁ የነበረ ሲሆን ኢትዮጵያ ግን አገራቱ የሚፈልጉት ስምምነት በውሃው የመጠቀም መብቷን የሚጋፋ መሆኑን በመግለጽ ሳትስማማ ቆይታለች።

በዚህም ግንባታው ከ80 በመቶ በላይ መጠናቀቁ የተገለጸው የህዳሴው ግድብ የመጀመሪያው ዙር የውሃ ሙሌት ባለፈው ዓመት ከተከናወነ በኋላ ሁለተኛው ዙር ከሳምንታት በኋላ በሚኖረው የክረምት ወቅት እንደሚከናወን አሳውቃለች።

ግብጽና ሱዳን ግን ሁለተኛው ዙር የውሃ ሙሌት ከመከናወኑ በፊት አገራቱ ከስምምነት ላይ መድረስ እንዳለባቸው እየወተወቱ ቢገኙም ኢትዮጵያ ግን ድርድሩ እየተካሄደም ቢሆን ግንባታውና የውሃ ሙሌቱ እንደሚካሄድ ገልጻለች።

በዚህ ወቅት ነው ግብጽና ሱዳን በውጭ ጉዳይና በመስኖ ሚኒስትሮቻቸው አማካይነት ተገናኝተው ከተወያዩ በኋላ ግድቡን በተመለከተ ኢትዮጵያ እየወሰደችው ያለው የተናጠል እርምጃ ጉዳትን እንደሚያስከትልባቸው በመግለጽ የሁሉንም አገራት ጥቅም ባስከበረ ሁኔታ ከስምምነት እንዲደረስ እንዲያግዙ የዓለም አቀፉን ማኅበረሰብ የጠየቁት።

አገራቱ ባወጡት መግለጫ “ኢትዮጵያ ጥቅማችንን ችላ በማለት የተናጠል እርምጃን እየወሰደች ነው” በማለት ሁለተኛው ዙር የግድቡ ሙሌትም የዚሁ አካል ነው በማለት ወቅሰዋል።

ኢትዮጵያ ሁለተኛውን ዙር የውሃ ሙሌት የምታከናውነው በተያዘለት ዕቅድ መሰረት መሆኑን በመግለጽ በድርድሩ ውስጥ ለመቀጠል ነገር ግን የውሃ ሙሌቱን በተያዘለት ጊዜ እንደምታካሂድ በተደጋጋሚ አሳውቃለች።

የኢትዮጵያ መንግሥት ባለሥልጣናት በመጪው ክረምት ቀጠሮ የተያዘለት ሁለተኛው ዙር የውሃ ሙሌት በምንም ዓይነት መልኩ እንደማይራዘምና ለዚያ የሚያበቃ አሰራርና ምክንያት እንደሌለ አቋማቸውን ገልጸዋል።

ሱዳንና ግብጽ ለአካባቢያዊና አህጉራዊ ደኅንንት እንዲሁም የጋራ ጥቅማቸውን ለማስጠበቅ ተባብረው እንደሚሰሩ በመግለጽ በዚህም ኢትዮጵያ በቅን ልቦናና በመልካም ፖለቲካዊ ፈቃደኝነት ላይ በተመሰረተ ሁኔታ እንድትደራደር በአካባቢያዊ፣ በአህጉራዊና በዓለም አቀፍ ደረጃ ግፊት እንዲደረግባት ጥረት እንደሚያደርጉ ተገልጿል።

የአፍሪካ ሕብረትና አሜሪካ በተለያዩ ወቅቶች ሦስቱን አገራት ለማሸማገል ለተራዘመ ጊዜ ጥረት ሲያደርጉ የቆዩ ቢሆንም በየትኛውም ድርድር ሁሉንም ከሚያስማማ ውጤት ላይ ለመድረስ አልቻሉም።

ግብጽና ሱዳን የታላቁ ሕዳሴ ግድብ የምናገኘውን የውሃ መጠን ይቀንሰዋል በሚል ተደጋጋሚ ተቃውሞ ሲያቀርቡ የቆዩ ሲሆን ኢትዮጵያ ግን የግድቡን ውሃ ለ65 ሚሊዮን ዜጎቿ የኤሌትሪክ ኃይል ለማቅረብ የምጠቀምበት በመሆኑ ችግር አይፈጥርም በማለት ስጋታቸው ተገቢ እንዳልሆነ ስትገልጽ ቆይታለች።

ከአራት ቢሊዮን ዶላር በላይ በሆነ ወጪ ግንባታው እየተካሄደ ያለውና ግንባታው ከተጀመረ አስር ዓመት የሆነው ታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ ከአፍሪካ ትልቁ እንደሆነ የሚነገር ሲሆን፣ ከአምስት ሺህ ሜጋ ዋት በላይ የኤሌክትሪክ ኃይል ማመንጨት የሚችል አቅም ያለው ግዙፍ ግድብ ነው።

የግድቡ የመጀመሪያ ዙር የውሃ ሙሌት ባለፈው ዓመት ክረምት ላይ የተከናወነ ሲሆን ሁለተኛው ዙር ደግሞ በመጪው የሐምሌ ወር እንደሚከናወን ኢትዮጵያ ያስታወቀች ሲሆን፤ በሚጥለው ዓመት በተወሰነ ደረጃ ኃይል ማመንጨት እንደሚጀምር ይጠበቃል።


Exit mobile version