ETHIO12.COM

ቻይና አጋርነቷን ከመርህ አንጻር በገሃድ አስታወቀች፤ በመቐለ ያሉ ጤና ተቋማት በሙሉ ሥራ መጀመራቸው ተገለጸ

ቻይና በኢትዮጵያ ጉዳዮች የውጭ ጣልቃ ገብነትን ትቃወማለች ብለዋል የውጪ ጉዳይ ሚኒስትሯ፡፡የቻይናው የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዋንግ ይ፤ በኢትዮጵያ ውስጣዊ ጉዳዮች የሚደረግ ጣልቃ ገብነትን አገራቸው እንደምትቃወም መናገራቸው ሲጂቲኤን ዘግቧል፡፡

የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ ዋንግ ይን ጠቅሶ ሲጂቲኤን እንደዘገበው፤ ቻይና በኢትዮጵያ ጉዳዮች የውጭ ጣልቃ ገብነትን ትቃወማለች።የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ ይህንን ያሉት ከኢትዮጵያው አቻቸው ጋር በተለያዩ ጉዳዮች ዙሪያ በስልክ ከተወያዩ በኋላ ነው።

የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩን ዋንግ ይ “ሁለቱ አገራት የሚተባበሩ አጋሮች ናቸው” ብለዋል፡፡ሲጂቲኤን በድረ ገጹ የቻይናው የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር “ኢትዮጵያ ብሔራዊ ደኅንነትና መረጋጋቷን የመጠበቅ መብት አላት” ማለታቸውን አስነብቧል።

“ኢትዮጵያ ውስጣዊ ጉዳዮቿን በዋነኛነት በራሷ ጥረት መፍታት አለባት ዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ የኢትዮጵያን ፍቃድ አክብሮ ድጋፍ መስጠት ነው ያለበት ማዕቀብ መጣልም የለበትም” ማለታቸውም ተዘግቧል።የቻይናው የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ከኢትዮጵያው አቻቸው ጋር ባደረጉት የስልክ ውይይት፤

“ቻይና በትግራይ ክልል ያለውን ሰብዓዊ ቀውስ ለማርገብ እርዳታ ለመስጠት ፍቃደኛ ናት የመጀመሪያው ዙር የምግብ እርዳታም ተልኳል” መባሉን ዢንዋ ዘግቧል።ቻይና በኢትዮጵያ የውስጥ ጉዳይ ጣልቃ ያለመግባት ፖሊሲን በማራመዷ አቶ ደመቀ፤ ማመስገናቸውንም ዘገባው አስነብቧል።

ከወራት በፊት በተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የጸጥታው ምክር ቤት ውስጥ በትግራይ ክልል የተከሰተውን ቀውስ በተመለከተ ውይይት በተደረገበት ጊዜ የኢትዮጵያ መንግሥትን ደግፈው ከቆሙ አገራት መካከል በምክር ቤቱ ድምጽን በድምጽ የመሻር ሥልጣን ያላት ቻይና አንዷ ነበረች።

በሌላ ዜና

በመቐለ ከተማ የሚገኙ የጤና ተቋማት ሙሉ በሙሉ ወደስራ መግባታቸውን የትግራይ ክልል ጊዜያዊ አስተዳደር ጤና ቢሮ አስታወቀ፡፡ የጤና ተቋማት ሙሉ በሙሉ የወደሙባቸው እና ራቅ ብለው ባሉ አከባቢዎች የጤና አገልግሎቱን ተደራሽ ለማድረግ እንዲቻልም በ60 ተንቀሳቃሽ ክሊኒኮች አገልግሎት እየተሰጠ መሆኑ ተጠቁሟል፡፡

በቢሮው የድንገተኛ ህክምና እንዲሁም የፈውስና ተሃድሶ የሥራ ሂደት አስተባባሪ የሆኑት ዶክተር አቤኔዘር ዕጸድንግል እንደገለጹት፤ በጥቃቱ በክልሉ በርካታ የጤና ተቋማት በከፊል እና ሙሉ በሙሉ ወድመዋል፡፡ እነዚህን ጤና ተቋማት ወሰድራ ለማስገባት በተከናወኑ ተግባራት ግን በርካቶችን ጠግኖና ግብዓት አሟልቶ ወደስራ ማስገባት የተቻለ ሲሆን፤ በመቐለ ያሌ ጤና ተቋማት ግን ሙሉ በሙሉ አገልግሎት በመስጠት ላይ ይገኛሉ፡፡

እንደ ዶክተር አቤኔዘር ገለጻ፤ በጤና ዘርፉ እንደ አገር ምሳሌ የሚሆን እንቅስቃሴ የነበረበት የትግራይ ክልል በጥቃቱ በርካታ የጤና ተቋማት ወድመዋል፡፡ በዚህም የህግ ማስከበር እርምጃው እንደተጠናቀቀ በተወሰነም ቢሆን አገልግሎት መስጠት የሚችሉ የጤና ተቋማት ቁጥር ከ50 ያልበለጡ ነበሩ፡፡ይህ ደግሞ በክልሉ የጠየና አገልግሎት ለመስጠት የሚደረገውን ጥረት አዳጋች አድርጎት የነበረ ሲሆን፤ ከፌዴራል መንግስትና አጋሮች ጋር በተደረገ ርብርን በርካታ የጤና ተቋማትን ጠግኖና ግብዓት አሟልቶ ወደስራ ማስገባት ተችሏል፡፡

በዚህም በመቐለ ከተማ ያሉ የጤና ተቋማት ሙሉ በሙሉ ሥራ የጀመሩ ሲሆን፤ ጤና ተቋማት ተጠግነው ወደስራ ባልገቡባቸው አከባቢዎች ለመድረስም በ60 ያህል ተንቀሳቃሽ ጀክሊኒኮች በመታገዝ እየተሰራ ይገኛል ብለዋል፡፡በመቐለ ከተማ ከሚገኙ የጤና ተቋማት መካከል በዓዲ ሹምዱሑን ጤና ጣቢያ እና በየካቲት 11 የመጀመሪያ ደረጃ ሆስፒታል አገልግሎቱ እየተሰጠ መሆኑን ዝግጅት ክፍላችን የተመለከተ ሲሆን፤ የየጤና ተቋማቱ ኃላፊዎች እንደገለጹትም የጤና ተቋማቱ በሙሉ አቅማቸው አገልግሎት እየሰጡ ይገኛል፡፡ ኢፕድ በወንድወሰን ሽመልስ (መቐለ)


Exit mobile version