Site icon ETHIO12.COM

የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር 100 ሺህ ቤቶችን ለመገንባት ከጎጆ ብሪጅ ማህበር ጋር ተስማማ

የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር በመዲናዋ 100 ሺህ ቤቶችን ለመገንባት ከጎጆ ብሪጅ ማህበር ጋር የውል ስምምነት ተፈራርሟል። የከተማ አስተዳደሩ የመኖሪያ ቤት ችግርን ከማቅለል አንፃር የተያዘውን እቅድ ለመተግበር ሲባል አብሮ ለመስራት መስማማቱ ተገልጿል።

ይህ ማህበር በቅርቡ ከ1000 የሚልቁና ደረጃቸውን የጠበቁ ቤቶችን ለመገንባት የዲዛይን ስራ እያከናወነ መሆኑ ተጠቅሷል። በቀጣይም በዋነኛነት መካከለኛ ገቢ ያላቸውን ግለሰቦች የጋራ መኖሪያ ቤት ተጠቃሚ ማድረግ ላይ በማተኮር ቤት ተመዝግበው ለሚጠባበቁ እንዲሁም በማህበር ተደራጅተው እየተጠባበቁ ለሚገኙ የመንግስት ሰራተኞችን ለመደገፍ ማለሙ ተገልጿል።

የማህበሩ ስራ አስኪያጅ አቶ አልማው ጋሪ ማህበሩ ቤቶችን በእቅዱ መሰረት ሰርቶ ለማስረከብ እና ሀላፊነቱን ለመወጣት እንደሚንቀሳቀስ ገልጸዋል።

የከተማው ቤቶች ልማትና አስተዳደር ቢሮ ሀላፊ ዶ/ር መስከረም ዘውዴ በበኩላቸው በከተማው ያለውን የጋራ መኖሪያ ቤት ችግር ለማቅለል ይዞ የመጣውን አማራጭ ሃሳብ በመቀበል አስተዳደሩ ከማህገሩ ጋር በጋራ እንደሚሰራም በማስታወቅ የጋራ የመግባቢያ ፊርማ ተከናውኗል።

ጎጆ ብሪጅ የግል ይዞታ ኖሯቸው መገንባት ያልቻሉ ግለሰቦችን በማህበር በማደራጀት ከቦታቸው ሳይነሱ ደረጃውን የጠበቀ ቤት ለመገንባት በማለም ከ3 ዓመታት በፊት የተደራጀ ማህበር ነው።

በጥላሁን ካሳ EBC


Exit mobile version