ETHIO12.COM

አሽከርካሪ ዛፍ ላይ በማሰርና በጦር መሳሪያ በመታገዝ መኪና የዘረፉ 12 ግለሰቦች ተያዙ

May be an image of outdoors and tree
አሽከርካሪውን በዚህ መልኩ ነበር ያሰሩት

በምሥራቅ ሸዋ ዞን ተሽከርካሪ የዘረፉ 12 ግለሰቦች በቁጥጥር ስር ውለው ምርመራ እየተደረገባቸው መሆኑን ፖሊስ አስታውቋል። በዞኑ በአዳሚ ቱሉ ጅዱ ኮምቦልቻ እና ሊበን ወረዳዎች የተሽከርካሪ ዘረፋ ወንጀል የፈጸሙ 12 ግለቦች በቁጥጥር መዋላቸውን የዞኑ ፖሊስ መምሪያ የሚዲያ እና ኮሙዩኒኬሽን ኃላፊ ኮማንደር አስቻለው ዓለሙ ገልጸዋል።

ግለሰቦቹ ንብረትነቱ የሰላም ውኃ ማምረቻ ፋብሪካ የሆኑ አንድ ኤፍ ኤስ አር እና አንድ አይሱዙ እንዲሁም አንድ ሲኖ ትራክ በድምሩ ሦስት ተሽከርካሪዎችን ሚያዝያ 14 ቀን 2013 ዓ.ም ጨለማን ተገን በማድረግ መዝረፋቸውን ገልጸዋል።

ዘራፊዎቹ የሐሰት ሰሌዳ ቁጥር በተለጠፈባቸው ሁለት ቪትስ ተሽከርካሪዎች እና በጦር መሳሪያ በመታገዝ የተሽከርካሪ ዝርፊያውን መፈጸማቸውን ተናግረዋል።

ዘራፊዎቹ በተለይም የኤፍ ኤስ አር አሽከርካሪውን ዛፍ ላይ አስረው የዘረፏቸውን ተሽከርካሪዎች ይዘው መሰወራቸውን ኮማንደር አስቻለው ተናግረዋል። በዛፍ ላይ ታስሮ ያደረው አሽከርካሪ ለአካባቢው ኅብረተሰብ ባሰማው ጩኽት ፖሊስ ደርሶ ሕይወቱን ማትረፉን ገልፀዋል።

የዞኑ ፖሊስ መምሪያ በዛፍ ላይ ታስሮ ያደረን አሽከርካሪ መነሻ በማድረግ የምርመራ አባላትን በቡድን በማደራጀት ባደረገው ክትትል ተጠርጣሪ ዘራፊዎቹ የዘረፋ ወንጀሉን ለመፈጸም ሲጠቀሙባቸው ከነበሩ ተሽከርካሪዎች ጋር በቁጥጥር ስር ማዋሉን አመልክተዋል።

ፖሊስ ሌት ተቀን ባደረገው ክትትል የተዘረፉ ተሽከርካሪዎች ከተሸጡባቸው ድሬ ደዋ፣ አዲስ አበባ እና ሞጆ ከተሞች መያዛቸውን የገለጹት ኮማንደር አስቻለው፣ በቁጥጥር ስር የዋሉ ተጠርጣሪ ግለሰቦች ላይ ምርመራ እየተካሄደ መሆኑንም ማስታወቃቸውን የዘገበው ኢዜአ ነው።

ዜናው ኢቢሲ ነው


Exit mobile version