Site icon ETHIO12.COM

“በትግራይ ጉዳይ የመንግስትን ሥራ ማቃለል ተገቢነት የለውም”፡- አቶ ደመቀ መኮንን


የትግራይን ጉዳይ በተመለከተ የኢትዮጵያ መንግስት ያከናወነውን ስራ በመቃወም የሚካሄደው ዘመቻ ተገቢ አለመሆኑን ም/ጠቅላይ ሚኒስትር እና የውጭ ጉዳይ ሚንስትሩ አቶ ደመቀ መኮንን ገለጹ።

አሁን የምንፈልገው ተጨባጭ ድጋፍ ነው ያሉት አቶ ደመቀ በሰብዓዊነት ሽፋን የኢትዮጵያን የግዛት አንድነት እና ትስስር እንዲሁም የመንግስትን ኃላፊነት የተመላው ተግባር ማቃለል ተቀባይት የለውም ብለዋል።

በትግራይ የሰብዓዊ እርዳታን ለማሳደግ እና ተደራሽ ለማድረግ፣ ማህበራዊ ትስስርን እንደገና ለመገንባት፣ እና መሰረታዊ አገልግሎቶችን ለመጀመር ከሁሉም ባለድርሻ እና ያገባኛል ከሚል አካል ጋር ለመስራት ኢትዮጵያ ዝግጁ መሆኗንም ነው አቶ ደመቀ በድጋሚ ያረጋገጡት።

ኢትዮጵያ በዚህ ወቅት የምትፈልገው የአጋሮችን ድጋፍ እንጂ ሁኔታውን የበለጠ የሚያባብስ ነገር አይደልም ብለዋል።

በጣም የሚያሳዝነው ሀገሪቱን በማይጠቅሙ መንገዶች ለማስጓዝ የሚደረጉ ጫናዎች ናቸው ያሉት አቶ ደመቀ ይህ ተግባር የወዳጅ አገራት ተግባር ተደርጎ አይቆጠርም ነው ያሉት።

የኢትዮጵያ መንግስት ይህን ፍትሀዊነት የጎደለው አካሄድ በእኩልነት ይቀበላል ተብሎ እንደማይጠበቅም ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሩ ገልፀዋል።

በኢትዮጵያ ላይ እየተደረገ ባለው የአገሪቱን መልካም ስም የማጉደፍ ዘመቻ ቅር መሰኘታቸውንም አቶ ደመቀ ተናግረዋል።

በዓም አቀፉ ማህበረሰብ ውስጥ ያሉ አንዳንድ ወገኖች በሰብዓዊነት ሽፋን የኢትዮጵያ የግዛት አንድነት፣ የአገሪቱን ሉአላዊነት በሚጋፋ መልኩ መንግስትን ለማዳከም ተልዕኮ ይዘው ሲሰሩ መመልከት ያሳዝናል ያሉት አቶ ደመቀ እነዚህ ግለሰቦች እና አጋሮች ከዚህ አፍራሽ ተልእኳቸው እንዲቆጠቡም አሳስበዋል።

በዚህ ረገድም በራሷ ዜጎች ላይ ርሃብን እንደጦር መሣሪያነት በመጠቀም በኢትዮጵያ ላይ የተለጠፉት ክሶች አጸያፊ ውሸቶች እና በምንም መንገድ ሰላም እና መረጋጋትን የሚያመጡ አለመሆናቸውን ጠቁመዋል።

በመጀመሪው ዙር ለ4.5 ሚሊዮን ህዝብ በትግራይ ክልል ምግብ አና ምግብ ነክ ያልሆኑ ቁሳቁሶች ድጋፍ ተደርጓል ብለዋል አቶ ደመቀ።

በሁለተኛው እና ሶስተኛው ዙር ደግሞ የድጋፍ ስራው ለ5.2 ሚሊዮን ዜጎች እንዲደርስ መደረጉን አንስተዋል።

እስከ አሁንም ድረስ 135 ሚሊዮን ዶላር የሚያወጣ 170 ሺህ 798 ሜትሪክ ቶን ምግብ መሰራጨቱን ያነሱት አቶ ደመቀ በአሁን ጊዜ የዓለም ምግብ ፕሮግራም፣ ወርልድ ቪዥን፣ ኬር፣ የትግራይ መረዳጃ ማህበር፣ ምግብ ለተራቡት እና መንግስት በክልሉ የምግብ ድጋፍ እያደረጉ መሆናቸውን ተናግረዋል። bi ena

Exit mobile version