ETHIO12.COM

በኦሮሚያ ታዳጊዎች በስነ-ምግባር ተኮትኩተው እንዲያድጉ ለማስቻል “ጋሜ” የተሰኘ አዲስ የልጆች ቻናል ከፈተ


የኦሮሚያ ብሮድካስቲንግ ኔትወርክ (ኦቢኤን) “ጋሜ” የተሰኘ አዲስ የልጆች ቻናል በመክፈት ዛሬ አገልግሎት አስጀምሯል።

ቻናሉን መርቀው ስራ ያስጀመሩት የኦሮሚያ ክልል ፕሬዚዳንት አቶ ሽመልስ አብዲሳ እንዳሉት፤ “ጋሜ ” የልጆች ቻናል በገዳ ስርዓት ውስጥ ታዳጊዎች

በተለይ የነገ ሀገር ተረካቢ ታዳጊዎች ባህላቸውን፣ ታሪካቸውንና ማንነታቸውን አውቀው እንዲያድጉ ቻናሉ የላቀ አስተዋጽኦ እንደሚኖረው ገልጸዋል።
የተቋሙ ሠራተኞች ሌት ተቀን ሠርተው ኦቢኤን ዛሬ ለደረሰበት ደረጃ ማብቃታቸውን ጠቅሰው አሁን በ17 ቋንቋዎች በማሰራጨትና የብዙሃን ልሳን በመሆን በሀገሪቷ ቀዳሚ ሚዲያ ነው ብለዋል።

የኦቢኤን የቦርድ ሰብሳቢ አቶ አዲሱ አረጋ በበኩላቸው፤ ኦቢኤን ከአንድ ቻናል በመነሳት ዛሬ ላይ ሶስተኛ ቻናል ላይ መድረሱን ተናግረዋል።

ተቋሙ የትውልድ ልሳን መሆን ችሏል ያሉት አቶ አዲሱ፤ ቻናሉ የልጆች መማማሪያ መሆኑን አስረድተዋል።

ይህ “ጋሜ” የተሰኘው ቻናል ሁለት ዘመናዊ ስቱዲዮዎች ያሉት መሆኑን ያስታወቁት ደግሞ የኦቢኤን ዋና ዳይሬክተር አቶ ዝናቡ አስራት ናቸው።
በአሁኑ ጊዜ ኦቢኤን በ14 የሀገር ውስጥና በሶስት የውጭ ቋንቋዎች እያሰራጨ እንደሚገኝ ያመለከቱት አቶ ዝናቡ፤ በዚህም የብሔር ብሔረሰቦች ልሳንና ድምፅ ላጡ ድምፅ መሆኑን በተግባር ያረጋገጠና በቅርቡ በቻይንኛና ፈረንሳይኛ ቋንቋዎች ስርጭት ይጀምራል ብለዋል።

ኦቢን ዛሬ ለደረሰበት ደረጃ የክልሉ መንግስትና የለውጡ አመራሮች ሚና የላቀ መሆኑን ጠቅሰዋል።

በሌላ በኩል የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት እና የኦሮሚያ ብሮድካስቲንግ ኔትወርክ ዛሬ አብሮ ለመስራት የሚያስችላቸውን የመግባቢያ ሰነድ ተፈራርመዋል።

በሁለቱ ተቋማት መካከል የመግባቢያ ሰነዱ መፈረሙ ያላቸውን ልምድ በመለዋወጥ በጋራ ለመስራት የሚያስችል መሆኑ ተመልክቷል።

የመግባቢያ ሰነዱን የተፈራረሙት በኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት ዋና ስራ አስፈጻሚ አቶ ሰይፈ ደርቤ እና የኦሮሚያ ብሮድካስቲንግ ኔትወርክ ዋና ዳይሬክተር አቶ ዝናቡ አስራት መሆናቸውን የዘገበው ኢዜአ ነው። via – OBN

Exit mobile version