Site icon ETHIO12.COM

የመቐለ ዞን ማረሚያ ቤት በቀጣይ ሳምንት ስራ ይጀምራል

የመቐለ ዞን ማረሚያ ቤትን በቀጣይ ሳምንት ስራ ለማስጀመር የሚያስችሉ ዝግጅቶች እየተጠናቀቁ ነው። ማረሚያ ቤቱ በህግ ማስከበሩ ወቅት የጁንታው ቡድን አባላት ታራሚዎቹ እንዲለቀቁ በማድረጉ ከፍተኛ ውድመት ደርሶበታል።

በዚህም የእንጨት ስራ መለማመጃ ማሽነሪዎች፣ ኮምፒውተሮች፣ የቢሮ እቃዎች፣ የብረታ ብረት ስራ መለማመጃና መስሪያ ማሽኖች፣ የህንጻ መስሪያ ግብአቶች፣ የታራሚ መኝታና መገልገያዎች፣ ሰነዶች፣ የጥበቃ ማረፊያዎችና ሌሎችም ቁሳቁሶች ዘረፉ የተፈጸመባቸውና እንዲወድሙ የተደረጉ መሆኑን የማረሚያ ቤቱ ኃላፊ ኮማንደር ዮሀንስ ወንድሙ ለፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬት ተናግረዋል።

በማረሚያ ቤቱ የደረሰው ጉዳትም ከ100 ሚሊየን ብር በላይ የሚገመት ሲሆን፥ ጉዳቱን ያደረሱትም በቀጥታ የክልሉ ርእሰ መስተዳደር በነበሩት ጥቅምት 17፣ 2013 ዓ.ም በተጻፈ ደብዳቤ የተለቀቁት እስረኞችና አንዳንድ የአካባቢው ነዋሪዎች መሆናቸው ተረጋግጧል።

ከ1ሺህ 500 በላይ እንዲፈቱ የተደረገበት የመቐለ ዞን ማረሚያ ቤት ወደ ስራ ባለመግባቱ፣ በመቐለ ከተማ በወንጀል የሚጠረጠሩ አካላትን በቁጥጥር ስር ከዋሉ በኋላ ማረሚያ ቤት ባለመኖሩ በዋስ እንዲለቀቁ እየተደረገ ነው።

በዚህ ምክንያት ተጠርጣሪዎች በተደጋጋሚ ወንጀል ሲሳተፉ መገኘታቸው የተረጋገጠ ሲሆን፥ ይህም የከተማዋን ጸጥታ ደህንነት በዘላቂነት ለማረጋገጥ በሚደረገው ጥረት እንቅፋት እየሆነ ነው።

የክልሉ ጊዜያዊ አስተዳደር ችግሩን ታሳቢ በማድረግ በማረሚያ ቤቱ ላይ ጥገናዎችን እያደረገ ሲሆን፥ የግብአትና መሰል አቅርቦቶችን በማሟላት ላይ ነው።

የማረሚያ ቤቱ ኃላፊ ኮማንደር ዮሀንስ ወንድሙ አሁን ላይ ማረሚያ ቤቱ በከፊል ስራ ለመጀመር የሚያስችለው ዝግጅት የተደረግ ሲሆን፥ የታራሚዎች የደንብ ልብስ እና የጥበቃ መሳሪያ እንዲሁም የመመገቢያ ተጨማሪ በጀት ብቻ ነው የሚቀረው ብለዋል። ይህም ለሚመለከተው አካል እንዲያውቅ ተደርጎ እስከ ቀጣይ ሳምንት ይሟላል ተብሎ ይጠበቃል።

ማረሚያ ቤቱን ከቀጣይ ሳምንት ጀምሮ አገልግሎት እንዲሰጥም ከፍተኛ ጥረት እየተደረገ ነው ተብሏል።

በኃይለየሱስ ስዩም ፋና ብሮድካቲንግ

Exit mobile version