Site icon ETHIO12.COM

“ሥራዬን ከብር ጋር አላያይዘውም” የጥርስ ሐኪም ራሄል አክሊሉ

እግሬ ተሰብሯል፣ ሆዴን አሞኛል፣ ቸግር ገጥሞኛል ማለት የተለመደ ነው።ጥርስ የለኝም፣ የአፌ ጠረን ተቀይሯል … ማለት ግን አይታሰብም። ምክንያቱን የጥርስ ችግር የስነልቦናም ጉዳይ ነውና። እናም ከጥርስ ጋር በተያያዝ የስነ ልቦናቸው የተጎዳ እና ሲናገሩና ሲስቁ አፋቸውን የሚሸፍኑ ሰዎችን በመርዳት ፈገግ ሲሉ ማየትና የተጫናቸውን የሃፈረት መጋረጃ መግፈፍ ከምንም በላይ አኩሪ ተግባር ነው።

መንገድ ነው። ጉዞ ነው። የሚፈልጉበት ቦታ ለመድረስ በመንገዱ ላይ መጓዝ ግድ ነው። መንገዱ ሁሉ ደስ የሚያሰኝ አይሆንም። ደስ ባማያሰኝ መንገድ ላይ ሳይራመዱ የሚፈልጉት ቦታ መድረስ የሚታሰብ ነገር አይደለም … ራሄል አክሊሉ የስኬቷን ሚስጢርና የህይወቷን ፍልስፍና የምታስረዳው በዚህ መልኩ ነው።

“ሰው” ትላለች ራሄል “ሰው በሃሳቡ ወይም ለመሆን የሚፈልገውን ነገር ሲያቅድ የሚሰማው እርካታና መሆን የፈለገውን ነገር ሲሆን የሚሰማው ስሜት ከተለያየ ህይወት ትመሳቀልበታለች፤ እርካታም ትለየዋለች” የሚለው እምነቷ ወጤታማ እንዳደረገት ትናገራለች።

በርካታ ቋንቋዎችን የምትናገረዋ የጥርስ ሃኪም ራሄል አክሊሉ የምትኖረውና የተማረችው ኖርዌይ ነው። ቀደም ሲል ጀርመን አገር ነበረች። “ሙሉ ሰው አደረገኝ” ስትል የምታሞካሸውን የኖርዌይ ዜግነት ያለው ባለቤቷ ዮን ሚክለቡስትን ያገባቸው ከ21 ዓመት በፊት ነው። ኖሃ እና ዴቪድ የሚባሉ ሁለት ልጆች አሏቸው።

ባለቤቷ ዮን “ራሄል የማትሸነፍ፣ የማትወደቅ፣ እጇን የማትሰጥ ጠንካራ ሰው ናት። ሚስት ብቻ ሳትሆን እናትም፣ ጓደኛም… ናት” ሲል ይገልጻታል። “ነገሮች የተበላሹና የማይሆኑ መስለው ቢታዩም አትታክትም። ነገሮችን እንደ ሁኔታው ማስኬድና ማከናወን የምትችል ጥሩ እናት፣ መልካም ሚስት፣ ሁል ጊዜም  ወደ ግቧ እንድትደርስ አግዛታለሁ። ምክንያቱም ለማንኛውም ዓይነት ድጋፍ ትመጥናለችና።”

ግልጽና ሳቂታዋ ዶክተር ራሄል በሙያዋና በተለያዩ ጉዳዮች ዙሪያ እንግዳ ካደረጋት ዛጎል ጋር ቃለምልልስ አድርጋለች። እንደሚከተለው ይነበባል።

ዛጎል- ባለቤትሽ ኖሽክ (የኖርዌይ ተወላጅ) ነው?
ራሄል- ሳቅ፣ አዎ!! ምነው?

ዛጎል- የፍቅር ህይወትሽን ለመስማት፤
ራሄል- ድንገት ነው የተገናኘነው። ይገርማል። ከዛሬ ሃያ አንድ ዓመት በፊት

ዛጎል- ወደኋላ ልመልስሽ፣ ድንገት የት? እንዴት?
ራሄል- ሳቀች። እሱ መሃንዲስ ነው። ለስራ ጀርመን በነበረበት ወቅት ድንገት አንድ መናፈሻ ውስጥ ይመጣል። እኔ ከጓደኞቼ ጋር ተቀምጬ እየተጫወትን ነበር። ጀርመናዊ እንዳልሆነ ስለ ገባንና ብቻውን ስለነበር እኛን ተቀላቅሎ እንዲቀመጥ ነገርነው። ለምን ብቻውን ይሆናል በሚል…

ዛጎል- ስለዚህ ጠብሰሽው ነዋ?
ራሄል – ኖ ኖ ኖ… ብቻውን ተቀምጦ ስለነበርና እንግዳ መሆኑ ስለተሰማን እኛ ጋር እንዲቀመጥ ጋበዝኩት። አወራን፣ ስድስት ወር ያህል  እንደ ማንኛውም አይነት ጓደኛ ሆነን ቆየን። ከዛ ተመልሶ አገሩ ሄደ።

ዛጎል- በቃ?
ራሄል- ከዛ ከተወሰነ ጊዜ በኋላ ተመልሶ መጣ። ደወለልኝ። ተመልሶ ለስራ እንደመጣ ነገረኝ። ሲደውልልኝ ስራ ጉዳይ ስለነበረኝ ዘግይቼ መጣሁለት። ቆይቼ ስረዳ የመጣው ለስራ ሳይሆን እኔን ፍለጋ ነበር። እንደውም በእኔ ምክንያት ስራውን ሊያጣ እንደነበር ተነገረኝ። በቃ በዛው አለቀ። አሁን ሁለት ልጆች አሉን።

ዛጎል- ሰርግ ተደረገ? ወይስ …
ራሄል- ስድስት ዓመት ከኖርን በኋላ የሰርግ ወግ የመሞሸር ሃሳብ መጣብኝ። ከዛም ኢትዮጵያ ሄድንና ተጋባን። ሰርግ አደረግን።

ዛጎል- ተወጂዋለሽ? “አዎ” በማለት ሳይሆን ትርጉም ባለው መልኩ አስረጂኝ፤
ራሄል- በልጅነቴ ብቻዬን ስለነበርኩ ሳገኘው ሙሉ ሰው አደረገኝ። የምደገፍበት ሰው ሆኖ አገኘሁት። እንደ ወንድም፣ አባት፣ ወዳጅ…. ነው። ብናደድ እንኳን ክፉ ነገር አይወጣውም። ፍጹም ታጋሽና የጠለቀ ስብእና ያለው ሰው ነው። ባህሪው መላክም የሚባል ነው።

ዛጎል- ብዙ ታላቅሽ ነው እንዴ?
ራሄል- አዎ! አስር ዓመት ይበልጠኛል። ስንጋባ እኔ ሃያ ነበርኩ። ግን አቋሙ ስፖርተኛና የተስተካከለ ስለነበር ሲነግረኝ እንጂ እንደሚበለጠኝ ብዙም አላሰብኩም ነበር።

ዛጎል- ግን እሱ አይሰጋም ነበር?
ራሄል- ወደፊት በእድሜዋ የሚሆናትን ታገባለች በሚል ይሰጋ ነበር። እጅግም ይንከባከበኝ ነበር። ሳቅ…..

ዛጎል- ይህንን ስትረጂ በየእለቱ ምን ታደርጊ ነበር?
ራሄል- ጭንቀቱን ስለምረዳ ሁል ጊዜም ሰላም እንዲሰማው አደርግ ነበር። በግልጽ እነግረው ነበር። ፍጹም እንዲህ ያለውን ጉዳይ እንዳያስብ ለማድረግ እጥር ነበር። የቆየ ታሪክ ነው። ወደ ኖርዌይ የመጣሁት እኮ 2001 ነው።

ዛጎል- ወደ ጀርመን የመጣሽው በልጅነትሽ ነው? በጀርመን ቤተሰቦች አሉሽ?
ራሄል- አዎ ያሳደጉኝ ቤተሰቦች አሉኝ።

ዛጎል- ኮንስበርግ ነበርሽ፤ ምን ተሰሪ ነበር? እንዴትስ ወደ ትምህርቱ ዓለም ገባሽ?
ራሄል- ቋንቋ ስለምችልና በወቅቱ እኔ ብቻ ስለነበርኩ ኮሙናው የማስተርጎምና አንዳንድ ስራዎች ያሰራኝ ነበር። አዲስ ነገር የለውም። በነገራችን ላይ ፈረንሳይኛ፣ እንግሊዝኛ፣ ኖሽክ፣ ጀርመንኛ እችላለሁ። ኮሙናው ሲያሰራኝ መማር ስለምፈልግ በትርፍ ጊዜዬ ካልሆነ እንደማልሰራ ተስማምተን ነበር። ምክንያቱም መማር እፈልግ ነበር። ክፍያው ብዙ ቢሆንም መማር እንዳለብኝ አስብ ስለነበር ስለ ክፍያው አልነበረኝም….

ዛጎል- ከዛስ?
ራሄል- ከዛማ ኦስሎ ዩኒቨርሲቲ ገባሁ። ሳላስበው የጥርስ ሃኪም ሆንኩ።

ዛጎል- ሳላስበው ማለት ምን ማለት ነው? ሳትፈልጊ ወይስ…..
ራሄል- ሃሳቤ ሚዲካል ዶክተር መሆን ነበር። በመካከሉ ወደ ጥርስ ህክምና ሳላስበው ታጠፍኩ። ወደድኩት ። ሙያው ትልቅ እንደሆነ በተረዳሁ መጠን ህክምና ውስጥ ለመግባት ማሰቤ የሚፈጥርብኝ ደስታ ህይወቴን ውበት ሰጠው…

ዛጎል- ማሰብ ወይስ መሆንና መገኘት?
ራሄል-ሃኪም መሆንም ሆነ የተለያዩ ሙያዎች ባለቤት መሆን የተለየ ሰው አያደርግም።የተለየ ጉዳይ የሚከናወነው ራስህ ውስጥ ነው። እኔ ሃኪም ለመሆን ሳልምና አሁን ሃኪም ከሆንኩ በሁዋላ የሚሰማኝ የደስታ ስሜት እኩል ነው።

ዛጎል- የጥርስ ሃኪም መሆን እኮ ከፍተኛ ገንዘብ ያስገኛል?
ራሄል- አዎ! ውድ ነው። ከሰራህ ታገኛለህ። እኔ እያልኩ ያለሁት የጥርስ ሃኪም ሆኜ ብር አገኛለሁ፣ ሃብታም እሆናለሁ፣ ቪላ እገዛለሁ….. በሚል ህልም አይደለም። በግሌ እንዲህ ያለውን አስተሳሰብ አልወደውም። አደገኛም ይመስለኛል። ለህይወት ደስታ የሚነፍግና እስከወዲያኛው እርካታ ቢስ የሚያደርግ ነው፤

ዛጎል- ብር አልወድም እያልሽ ነው?
ራሄል- አይደለም። ብር ለማግኘት አስቤና አልሜ ግን ሙያውን አልወደድኩትም። ሃኪም ለመሆን ያሰብኩት ሙያውን ገንዘብ አመርትበታለሁ ብዬ አይደለም። አስተሳሰቡም ትክክል አይደለም። አብዛኛውን ጊዜ አንድ ሙያ ከያዝኩ በኋላ ወይም አንድ ነገር ከሆንኩ በኋላ ይህንን አገኛለሁ በሚል ሂሳብ መመራት አደጋ እንዳለው መረዳቴን ለማሳየት ነው። አብዛኛውን ጊዜ በዚህ ዓይነት አስተሳሰብ የተጓዙ ሰዎች የፈለጉትን ነገር ከሆኑ በኋላ የሰሩት ሂሳብ ሳይሳካ ሲቀር ህይወታቸው መራራና ደስታ የራቀው ይሆናል።

ዛጎል- ለምሳሌ እኔ ብታመም በነጻ ታክሚኛለሽ?
ራሄል- ሲጀመር በነጻ ለመታከም ማሰብ አግባብ አይደለም። ግን ከታመምክና እኔ ጋር ከመጣህ፣ መክፈል የማትችል ከሆነ እየታመምክ አትመለስም። አንተ ብቻ ሳትሆን ማንም። ስም መጥቀስ ባልፈልግም በቅርቡ አንድ እህት ኤርትራዊ ናት ታማ እኔ ጋር መጣች። ገንዘብ የላትም ነበር። እናም አክሜ በነጻ እንድትሄድ አደረኳት። እኔ ይህንን እውቀት የሰጠኝ እግዚአብሔር ነው። የማክመው በእጄ ነው። እሷን በመርዳቴ አልጎዳም። ከገንዘብ በላይ የእሷ እርካታ የሚሰጠኝ ደስታ ልዩ ነው።ሌሎችም አሉ። ከዚህ ይልቅ ሌሎች ጉዳዮችን ብናነሳ?

ዛጎል- ተቀጣሪ ነሽ?
ራሄል- ትምህርቴን እንደጨረስኩ መምህሬ የራሱን ከሊኒክ ሰጠኝ። አሁን የራሴ ክሊኒክ አለኝ። በትምህርት ቤት ተወዳጅ ነበርኩ…. ትስቃለች… በውጤትም ደረጃ እወደድ ነበር። እናም መምህሬ…

ዛጎል- አቅምሽን አይቶ ነው የሰጠሽ? ማለትም ብቃትሽን?
ራሄል- ለምን እንደተሰጠኝ ፕሮፌሰርን ብትጠይቀው ያስረዳሃል። እኔ ክሊኒክ እንዳለኝ ያነሳሁት በሙያዬ ለዜጎቼ እንዲሁም አገልግሎቱን ለሚፈልጉ ሁሉ ማበረከት የምችበትን አግባብ አምላኬ እንዳዘጋጀልኝም ጭምር ለመናገርና በዚህም እጅግ ደስተኛ መሆኔን ለማሳየት ነው።

ዛጎል- እና ህይወት አልጋ በአልጋ ሆኖልሻል ማለት ነው?
ራሄል- ይገርማል። ለምሳሌ ዩኒቨርስቲ ውስጥ የውጭ አገር ዜጋ በመሆን ብቻ የሚያጋጥም ችግር አለ። ጠይቀህ እንኳን መልስ ላታገኝ ትችላለህ። ውስጥህ የሚያዝንበት አጋጣሚዎች አሉ። ሆኖም ግን በጽናት በመስራት አልፌዋለሁ። የማያስፈልጉኝን ነገሮች አልፌ የሚያስፈልጉኝን ነገሮች እንደምደርስ አምኜ ስለገባሁበት ተሳክቶልኛል። አብዛኞች እጃቸውን የሚሰጡት የማይፈልጉትን ነገር መስራት ስለማይወዱ የሚወዱት ቦታ ወይም ነገር ጋር ሳይደርሱ ይቀራሉ። ይህ እውነት ነው። የምትፈለገው ቦታ ለመድረስ አቋራጭ ብሎ ነገር የለም።

ዛጎል- ህይወትን በፈለጉት መንገድ መምራት ከባድ ነው እያልሽ ነው?
ራሄል- አዎ!! ሕይወት ከባድ ነው። መሰጠት/commitment/ የሚባለው ጉዳይ እዚህ ላይ ወሳኝ ነው። ዝም ብሎ ተወልዶ፣ አድጎ፣ አርጅቶ መሞት ሕይወት አይደለም። ህይወት ግብ ያስፈልገዋል። ህይወትን ከባድ የሚያደርገው ግብ በማስቀመጥ መጓዝ ሲጀመርና ከተቀመጠው ግብ ለመድረስ ዓላማን በማሰብ የሚደረገው ጉዞ ሲጀመር ነው። እና ሕይወት ጉዞ ነው። ወደ ግብ የሚደረገው ጉዞ በምቹ ሁኔታ ብቻ የታጀበ አይደለም።አንዳንዴ ያለህበት ቦታና ግብህ ሊለያዩብህ ይችላሉ። አንዳንዴም ያለህበት ቦታ ግብህን ለማሳካት መሰናክል ሊሆን ይችላል ብላህ ልታስብም ትችላለህ። ነገር ግን በዚህ አይነቱ መንገድ ስታልፍ በከፍተኛ ደረጃ ባለ ድል የሚያደርጉ የተለያዩ ስብዕናዎችን ትላበሳለህ። ጽናት፣ ትዕግስት፣ ዝቅ ማለት፣ አለመውደቅ፣ እጅ አለመስጠት፣ አሸናፊነት፣ መፍትሄ የመፈለግ ዘዴን … የመሳሰሉት ወርቅ የሆኑ የህይወት ማስዋቢያ ቅመሞች ከውስጥህ ጋር ይዋሃዳሉ…

ዛጎል- በተለይ ስለችግር ያለሽ ተሞክሮ አለ?
ራሄል- በስያሜ ልንለያይ እንችላለን። ከላይ እንዳልኩት ተወልዶ፣ አድጎ፣ ሸምግሎ መሞት በሚለው ሂሳብ አሁን ባለሁበት ቦታ ላይ ሆኜ ችግር አለ ብዬ ለመናገር አልችልም። ከዛ ባለፈ ግን መቸገር ጥሩ ነው። የችግሩ አይነት ቢለያይም ችግርን ማየት የሌሎችን ችግር ለመረዳት መስታዋት ሆኖ ያገለግላል። እግዚአብሔር ሰዎችን በተለያየ መንገድ ውስጥ ያሳልፋቸዋል። በዛ ውስጥ ደግሞ ለወደፊት የሚሆን የህይወት ስንቅ ያሲዛቸዋል። ልክ በመንፈሳዊ ህይወት እንደተማርነው ሁሉ በስጋዊ ዓለም ውስጥም ሁሉም ነገር መማሪያ ነው….

ዛጎል- ቀደም ሲል የጥርስ ችግር በተለየ ከስነ ልቦና ጋር አያይዘሽ ነበር
ራሄል- ኦ! አዎ! ሕመሙን ለአፍታ እንርሳውና አንድ ጥያቄ እንጠይቅ። ጥርሱ የተሰበረ፣ የወለቀ ወይም የረገፈበት ሰው መሳቅ ያቆማል። ነጻነት ስለማይሰማው ከሰዎች ጋር ያለውን ግንኙነት ይቀንሳል። ያቆማል። ዝምታን ይመርጣል። አፉን መያዝ፣ መሸፈንና በጥርሱ አለመኖር ሳቢያ ማህበራዊ ግንኙነቱ ላይ የደረሰውን ቀውስ ያስባል። ይህ ከባድ ችግር ነው። እንዲህ ያሉ ሰዎች ህክምና ሲመጡ መርዳት ልዩ ስሜት አለው። እንዲህ ያሉ ሰዎች ተስተካክልው ፈገግ ብለው መመልከት ያረካል። በጥርሳቸው አለመኖር ወይም መጓደል የተቸገሩና የተሸማቀቁ ሰዎች ፈገግ ሲሉ…. እንዴት ላስረዳህ? የተቸገረው ሰው በደንብ ይገባዋል። የጠረን መለወጥ ችግርም ተመሳሳይ ነው። ዋናው መቋጫ ግን የማህበራዊ ግንኙነትን መልሶ ማበጀትና መጠገን ትልቅ ሃላፊነት ይመስለኛል። ለእኔ ሃላፊነቱን በጨዋነት ወስጄ ሰዎችን ማስደሰት የደስታዬ ሁሉ መሰረት ነው።

ዛጎል- አረዳድሽ ሆን ብለሽ ወደ ሙያው የገባሽ እንደሆነ ያመላክታል
ራሄል- አይደለም። በፍጹም። ቀደም ብዬ ገልጨዋለሁ። እኔ ሜዲካል ሃኪም ለመሆን ነበር ያሰብኩት። በመካከሉ ነው ወደ ጥርስ ህክምና ያዘነበልኩት። ውስጡ ከገባሁ በኋላ ወደድኩት። በነገራችን ላይ በሜዲካል ፋኩሊቲ የተወደድኩና የተሳካልኝ ተማሪ ነበርኩ።ትክክለኛ ስፍራዬም እዛ ነበር። ውጤቴም ጥሩ ነበር። ስላስበው ሶስተኛ ዓመት ላይ ወደ ጥርስ ሃኪምነት ተዛወርኩ።

ዛጎል- ደስተኛ ነሽ ማለት ነው?
ራሄል- ቀደም ብዬ በገልጽኳቸው ምክንያቶች ደስተኛ ነኝ። እጅግ ደስተኛ ነኝ!!

ዛጎል- የጥርስ ሕክምና ውድ ነው። ሕመሙ ደግሞ ፋታ አይሰጥም፤ ምን ሃሳብ አለሽ?
ራሄል- እውነት ነው። የጥርስ ሕመም በባህሪው ከባድ ነው። ክፍያውም ውድ ነው። እንደ ባለሙያ ግን እኔ ማለት የምፈልገው ለምን እንታመማለን በሚለው ዙሪያ ነው። አንድ ሰው በየጊዜው ጸጉሩን ለመስተካከል ወደ ጸጉር ቤት እንደሚሄደው ለጥርሱም ተመሳሳይ ስራ መስራት ይገባዋል። በጥርስ ህክምና አንድ ሰው ታሞ ጥርስ ሃኪም ዘንድ ከሄደ “ዘገየ” ነው የሚባለው። ሳይዘገይ የጥርስ ሃኪም ጋር የሚሄድ ሰው ወጪውም ቀላል ነው። ታሞ ከሄደ ግን ወጪው ይጨምራል። ስለዚህ የጥርስ ሃኪም ጋር መሄድ ግድ ነው። እዚህ ያለንበት አገር ጥርሳቸውን ይጠብቃሉ። ለጥርሳቸው ውበት ይጨነቃሉ። ዋጋ ይሰጣሉ። ጥርስ ውበት ስለመሆኑ ነጋሪ አያስፈልጋቸውም። እኛም እዚህ እስከኖርን ድረስ ተመሳሳይ ልምድ ልናዳብር ይገባል። በስራ ቦታ፣ በመዝናኛ ቦታ፣ በተለያዩ አጋጣሚዎች ጥርስ ቀድሞ የሚታይ ውበት ነውና።

ዛጎል- አሁን አንቺ የግል ክሊኒክ ባለቤት ነሽ። ትምህርትሽን እንደጨረሽ ነው የክሊኒክ ባለቤት የሆንሽው። ትምህርትሽን እንደጨረሽ የኪሊኒክ ባለቤት ስትሆኚ የተለያዩ ስሜቶች ይኖሩሻል። በተለየ ግን የተሰማሽ ምንድን ነው?
ራሄል- አስቀድሜ እንደገለጽኩት እኔ ጋር ስሪ ብሎ የግል ክሊኒኩን የሰጠኝ መምህሬ ነው። የግል ኪሊኒክ ለመክፈት ብዙ ወጪ ይጠይቃል። ቀላልም አይደለም። ግን ይህ መልካም ሰው ይህንን ሲያደርግልኝ ቅድሚያ ያስታወስኩት የአገሬን ሰዎች ነው። የችግሩን መጠን ስለማውቀውና በርካታ መረዳት ያለባቸው፣ መታከም የማይችሉ ሰዎች ስላሉ።….. ከዝምታ በኋላ ቀጠለች … አየህ በዚህ ስራ የራስህ የሆነ ክሊኒክ ካለህ ራስህ እንድትወስን ይረዳሃል። ስለዚህ መርዳት ያለብህን ትረዳለህ። ማድረግ የፈለከውን ታደርጋለህ። ወሳኙ አንተ ነህ። ይህንን እድል ላመቻቸልኝ አምላክ ከፍተኛ ምስጋና አለኝ። የሚገርመው አንዳንዴ ትንሽ ነገር አድርገህ ሰዎችን ታስደስታልህ ራስህም ትደሰታለህ። እውነት ለመናገር ብዙ ጊዜ ስራዬን ከብር ጋር አላያይዘውም።

ዛጎል- ይንን ቃለ ምልልስ ለሚያነቡ ኢትዮጵያዊያን እና አማርኛ ማንበብ ለሚችሉ ሁሉ ምን ትያቸዋለሽ?
ራሄል- እኔ ስራ ትቼ ነው ወደ ትምህርት ያተኮርኩት። ምክንያቱም ዓላማዬ ነበርና። የሆነ ቦታ ላይ ገንዘብ ማግኘት በርካቶችን ከፈለጉበት እንዳይደርሱ ይጎትታቸዋል። አንዳንዴም በሚጠሉት ነገር ውስጥ ገብተው እንዲቀሩ ያደርጋቸዋል። በዛው ኖሮ ዓለምን መሰናበት ይመጣል። እኔ ሁሌም የሚያስደስተኝ ነገር ነው የማደርገው። ወይም ቀደም ብዬ እንዳልኩት በማልፈልገው መንገድም ቢሆን አልፌ የሚያስደስተኝ ነገር መያዝ የህይወቴ መመሪያ ነው። ሰዎች ይህንን ቢረዱ ደስ ይለኛል። ማንኛውንም ፈተና የማለፍ ቁርጠኛነት አስፈላጊ ነው። ትግል ደስ ይላል። እኔ ሃብታም ብሆንም ሃኪም ነኝ። ደሃም ብሆን ሃኪም ነኝ። እርካታዬ ሃኪም በመሆኔ ብቻ ነው። ሰው እኔ ጋር መጥቶ ታክሞና አርፎ ሲወጣ ማየት ያስደስተኛል።

ዛጎል- አሁን በደረስሽበት ደረጃ ኩራት ይሰማሻል?
ራሄል- ምንድን ነው ኩራት? እኔ ሃኪም መሆን ሳስብ ደስተኛ ነበርኩ። አሁን ሃኪም ሆኜም ያ ደስታ ነው ያለኝ። ፍላጎቴን በማሳካቴ እረካለሁ። ዝና ክብር ብሎ ነገር የለም። ሽንት ቤት ብጠርግ፣ ጽዳት ብሰራ፣ ሌላ አገር ሄጄ አታክሚም ብባል… እኔ ሃኪም ነኝ በቃ!! ባልስራ እንኳን ልጆቼን እያከምኩ እኖራለሁ። ሙያዬን ከምንም ነገር ጋር አላያይዘውም። ቁም ነገሩ ሰዎችን መርዳት ነው። መረዳት የሚገባቸውን ማገዝ ነው። ሃኪም ከሆንኩ በኋላ ጥሩ አገልጋይ መሆንና፣ በአገልግሎቴ መደሰት ብቻ ነው አላማዬ። የመለስኩልህ መሰለኝ። ሰው የአንድ ሙያ ባለቤት ስለሆነ አይደሰትም። የአንድ ሙያ ባለቤት በመሆን ይህን አገኛለሁ፣ ይህንን እገዛለሁ፣ ወዘተ በማለት በቁሳዊ ነገር ስኬቴን አስቤ ህይወቴን ደስታ ማሳጣት አልመኝም። ፍላጎቴም አይደለም። ብዙ ጊዜ የግባችንን ስኬት ቁሳዊ ነገር ላይ ካደረግነው ህይወታችን ሁሉ የተመሳቀለ ይሆናል። እንዲህ ያለውን ሃሳብ አልወደውም። አምላክም በመጠን ኑሩ ብሎናል እኮ። አሁንም ደግሜ እናገራለሁ ሃኪም በመሆኔ ብቻ ደስተኛ ነኝ። ስራዬን ከኑሮዬና ከሌሎች ነገሮች ጋር ማያያዝ አልፈልግም።

ዛጎል- ወደ ቤትሽ ልመልስሽ፣ ከባለቤትሽ ጋር የባህል አለመጣጣም አልጋጠማችሁም?
ራሄል- ጥሩ ነገር አስታወስከኝ። ባለቤቴ ዮኒ እኔ የማላውቀውን ሁሉ ያውቃል። ስለ ኢትዮጵያ ባህል ያነባል። ስለ ምግባችን በፊልም ያያል። የበዓል ቀኖችን ያውቃቸዋል። የባህል ልብሶች ይገዛልኛል። ለማወቅ የተዘጋጀ ሰው ነው። መልካም የትዳር ጓደኛ እንዳለኝ ሁሌም አስባለሁ። ክፉ ነገር አይወጣውም። ቀና ነው። በልጅነቴ ከአገር ቤት ወጥቼ የጀርመን ወላጆቼ ስላሳደጉኝ እሱ ሙሉ ያደረገኝ ያህል ይስማኛል። አከብረዋለሁ። ደስተኞች ነን። ልጆቻቸንም /ኖሃና ዴቪድ/ እጅግ ደስተኞች ናቸው። አይበቃህም?

ዛጎል- እርዳታ የሚፈልጉ እንዴት ያገኙሻል? ድረ ገጽ አለሽ?
ራሄል- ክሊኒኬም የሚገኘው Storgate 38, 0182 Oslo ነው። በፌስቡክ  Tannlege Rahel Myklebust

(ቃለምልልሱም ፎቶዎቹ የተገኙት ከዛጎል ነው)

Exit mobile version