Site icon ETHIO12.COM

ላይቤሪያ፣ ብሩንዲ፣ ሩዋንዳ ፣ሶማሊያ፣ በችግራቸው ወቅት ስለደረስክላቸው ውለታህን አልረሱም ከአማፂያን አብረው ደምህን አላፈሰሱም

24 ሠዓታትበውትድርናህይወት ክፍል 11 ( ልዩ ) – ትጠይቃለህእናምትወስናለህ

አንተ እኮ ለሀገር ሠላም ለህዝብ ደህንነት ለአንዴ ብቻ የምትኖራትን አንድ ህይወት ወደህ ፈቅደህ ለመስጠት ሠንደቅ ዓላማህ ፊት ቃል ገብተሃል።

ያለህን ሁሉ ሳትሰስት ሠጥተሃል። ሀገር ማለት ለአንተ ከሠሜን እስከ ደቡብ እስከ ምስራቅ ያለው መልክአ ምድር ፣ በውስጧ የሚኖሩ ህዝቦቿ እና መንግስቷ ናቸው።ለአንተ ሁሉም የሀገርህ ህዝብ እኩል የሚፈቀርና የሚከበር ነው።

በታሪክ አጋጣሚ አሊያም በሌላ ምክንያት ሁሉንም ህዝብ እኩል የማገልገል ፍላጎት ቢኖርህም አልቻልክም።በአንድ አከባቢ ለብዙ ዓመታት በመቆየትህ ከሌላው በተለየ መልኩ ያለህን ዕውቀት ጉልበትና ገንዘብህን ለአከባቢው ለግሰሃል።ቅር ብሎህ ግን አያውቅም።

ከተረፈህ ሳይሆን ካለችህ ላይ አካፍላህ ከረሃብና ከጥም ታድገሃል።ህመሙን ታመሃል።ችግሩን ተቸግረሃል።መንገድ ሆነህ ተረምዶበሃል።ትምህርት ቤት ሆነህ ተምሮበሃል።ሁሉንም ሆነህ ሁሉን በአንተ እንዲያገኙ አድርገሃል።

ለህዝብ ውሃም ፣ ምግብም ፣ መጠለያም ነህ።የመፅናኛ አለት ነበርክ።አብሬህ ስትኖር ከሚጠበቅብህ በላይ ሆነህለታል።ሐኪም፣ አስተማሪ ፣ ጧሪ ፣ ቀባሪ ፣ አራሽ ገበሬው ነበርክ።የሆንክለትና በኋላ የሆነብህ ፍፁም ተቃራኒ ቢሆንም ተስፋ አልቆረጥክም።

ምክንያቱም ውሸት ተደጋግሞ ሲነገር እውነት መስሎት እንጂ ያ ሁሉ የፍቅር ግድግዳ እንዴት በጥላቻ ትርክት በአንዴ ይናዳል ብለህ ይሆናል።ያሳደካቸው ህፃናት በድንህ ላይ ሲጨፍሩ እነሱን ይቅር ብለህ የመረዛቸውን መርዘኛ ውሻ ተገቢውን ቅጣት ሰጥተህ ደግም ሰፊ እጅህን እየዘረጋህለት ከመንግስትነት ወደ በረሃ አውሬ የተቀየረውን አውሬ በማደን ላይ ሳለ ከሌላው የሀገርህ ህዝብ በበለጠ የኖርክበት ካራ አንስቶበሃል።

እንኳን ከእጅ እየበላ ፣ ሆነህለት ከለላ በትናንቱ ስህተት ተፀፅቶ ፍቅሩን ያድሳል፣ አቅም ኖሮት የሚያደርግልህ ነገር ባይኖርም እሱን ለከፋ ድህነት፤ አንተን ለአሳፋሪ ክህደት የደረገህን በማፅዳቱ ሂደት በማገዝ ይክስሃል ተብሎ ሲጠበቅ የሆንክለትን ሳይሆን ዘር አስልቶ ከአውሬ ጋር በልቶሃል።

በህይወት እንዲቆይ ብሩህ ነገን እንዲያይ ስንዴ ስትሰፍርለት ውለህ ወደ ቀጣዩ ተግባር ለማለፍ ስትዘጋጅ ያ ወገን አጭበርብሮ ለጠላት ስንቅ ያቀብላል።ደክመህ ሲያገኝህ በውሃ ፋንታ መርዝ ያጠጣሃል።አጋጣሚ ሲያገኝ አንገትን በካራ ይቀላል።ሲመቸው የደበቀውን መሣሪያ አውጥቶ ከኃላ መትቶ ይጥለሃል።

አሁን ታመሃል

አሁን ታመሃል።የታመምከው በወገን መሀል በማራብህና በመጠማትህ ብቻ አይደለም።ሞቱም ያን ያህል ላይሆን ይችላል።ምክንያቱም ህይወት የሚያሳሳህ ሞት የሚያስፈራ አይደለህም።ለዓላማ መሞት ክብር መሆኑን አምነሃል።

ከሁሉም የበለጠ የከበደህ ሌላ ነው።ቁስልህ እንዳይሽር የሚያደርገው የቆሰልክበት መንገድ ፣ በማን? የትና መቼ የሚለው ነው።በወገን መከዳት ከመሞትና መቁሰል ይበልጣል።

ከላይቤሪያ፣ ብሩንዲ፣ ሩዋንዳ ፣ሶማሊያ፣ ሁለቱም ሱዳኖች ጋር ቋንቋ አትጋራም።ምናልባት ብዙ የሚለያያችሁ ነገሮች ይኖራሉ።በችግራቸው ወቅት ስለደረስክላቸው ውለታህን አልረሱም።ከአማፂያን አብረው ደምህን አላፈሰሱም።

ይሄ እኮ ቤትህ ነው።በደምህ ተለስኖ ፣ በሥጋ ተመርጎ ፣ በአጥንት ተማግሮ የተሠራ የራስህ ጎጆ ነው።ነዋሪዎቹ ደግሞ ቤተሰቦችህ ናቸው።ያንተ እምነት አይቀየርም።ብሔር ኢትዮጵያ እምነትህ ህዝቦቿ ናቸው። በዚያኛው ወገን ግን ይሁዳነትን የተለማመዱ በዝተዋል።

የማይመለሰው ጥያቄ

ትጠይቃለህ።በባዕዳን ምድር ያገኘኸው ክብርና ዝና ፣የላቀ ፍቅርና ምስክርነት ያለኝን ሁሉ በለገስኳቸው የራሴ ወገኖች ስለምን እንደ ተረቱ ሆነ?ወርቅ ለበደረ ጠጠር እህል ላበደረ አፈር ለኔ ይገባኝ ነበር?ትላለህ።

ትላንት አንበጣ ሳበር ውዬ ደክሞኝ ገደም ባልኩበት የገዛ ጓዴ ወግቶ ገደለኝ።የሱ ሲገርመኝ ሁለንተናውን የለወጥኩለት ወገኔ እንዴት ልጄን እነዚህ የተለዩ የታበዩ አካላት ይጎዱብኛል ይላል ተብሎ ሲጠበቅ በድኔን አፈር ነፈገው።ይሄ በየትኛው ሀገር ተፈጽሞ ያውቃል? ከቃልኪዳንና ፈልገን ካልተፈጠርንበት ብሔር የቱ ይበልጣል?

ጥያቄው አያልቅም።ያበሏቿው የሚያስበሉኝ፣ ከለላ የሆንኳቸው አሳልፎ የሚሰጡኝ፣ ከደመወዜ አዋጥቼ፣ ምግብ አብልቼ ፣ደብተር ገዝቼ ፣መጠለያ ና መማሪያ ሠርቼ ሰጥቼ ፣ያሳደኳቸው ህፃናት ስለምን ያለስሜ ይጠሩኛል?ከባህር የወጣ ዓሣ ያደርጉኛል?ብለህ ትጠይቃለህ?ምላሽ ግን አይኖርህም።

ሠላም ለኢትዮጵያ ፡፡ ድል ለጀግናው የህዝብ ልጅ !

ሻለቃ ፈይሳ ናኔቻ source Defence force official FB

Exit mobile version