Site icon ETHIO12.COM

የሰብአዊ መብቶች ኮሚሽን ያልተሟላ ጥሪ አቀረበ

“ትግራይ ክልል የሲቪል ሰዎችን ሁኔታ ለማሻሻል አፋጣኝ እርምጃዎች ሊወሰዱ ይገባል” ሲል የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብቶች ኮሚሽን ሙሉ ያለሆነና ለሁሉም ወገኖች በኩል ደረጃ ስሜት ያላጋራ ጥሪ አቀረበ። ጥሪው ወቅታዊ ቢሆንም ለምን ሁሉንም ችግሮች እንዳልዳሰሰ የተሰጠ ምክንያት የለም።

ኮሚሽኑ በማህበራዊ ዓመዶች ባሰራጨው ጥሪ መንግስት ትግራይን ለቆ መውጣቱን ልክ እንደ ነጮቹ አሞግሷል። ከዛም የመብራት፣ የውሃ፣ የስልክና የተለያዩ አገልግሎቶች መቁረጥ በሲቪል ሰዎች ላይ ያስከተለውን ችግር አሳሳቢነት አሁንም ነጮቹ እንደሚሉት አቅርቧል። በትግራይ ያለውን ሰብአዊ ቀውስ ለማስታገስ መንግስት ሊተባበርና የተጓደሉትን ሊያሟላ እንደሚገባ ጠይቋል። በትግራይ ያሉ ተማሪዎችን ጉዳይ ሲያነሳ ግን መታፈናቸውን፣ የተገደሉ ስለመኖራቸው ያለው ነገር የለም።

ከሁሉም በላይ በትግራይ ” ከዳችሁን፣ ባንዳዎች” በሚል ከአርባ በላይ ንጽሃን በአመለካከታቸው እንደተገደሉ በምስልና በማስረጃ ይፋ ቢሆንም ዶክተር ዳንኤል ” አሳሰቡ፣ አመለከቱ” በተባለበት ጥሪ በትግራይ ነጻ አውጪ ሰራዊት ስለተገደሉና ስለታፈኑ ዜጎች ምንም አልተባለም። ዶክተር የማይካድራን ሪፖርት ጥቅል ግኝት ይፋ አለማድረጋቸውና ክልሉን ሲያስተዳድር በነበረው ሃይል ፖሊስ፣ ልዩ ሃይልና ሳምሪ በተባለ የወጣቶች አደረጃጀት ጭፍጨፋው መፈጸሙን በቅድመ ሪፖርታቸው ካወጁ በሁዋላ በመካከሉ ” የትሀንግ አመራሮች ትዕዛዝ ስለመስጠታቸው ማስረጃ የለም” ካሉ በሁዋላ አብዛኞች እየተጠራጠሯቸው ነው። የኮሚሽኑ ጥሪ ከታች ይገኛል።

ትግራይ ክልል፡ የሲቪል ሰዎችን ሁኔታ ለማሻሻል አፋጣኝ እርምጃዎች ሊወሰዱ ይገባል

የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብቶች ኮሚሽን (ኢሰመኮ) ሰኔ 21 ቀን 2013 ዓ.ም. የፌዴራል መንግስት በትግራይ ክልል የተኩስ አቁም ማወጁን ተከትሎ የግንኙነት መሰመሮች በመቋረጣቸው፣ በክልሉ ነዋሪዎች የሚገኙበት ሁኔታ እንደሚያሳስበውና መንግስት የነዋሪዎችን ደኅንነት ለማስጠበቅ የሚረዱ እርምጃዎች በአፋጣኝ ሊወስድ እንደሚገባ ገለጸ።

በክልሉ የተቋረጡ መሰረታዊ አገልግሎቶችን መመለስና በትግራይ ክልል ስላለው ተጨባጭ የፀጥታ ሁኔታና የሰብአዊ እርዳታ አቅርቦት በቂ መረጃ መስጠት፣ በዚህ ረገድ ያሉ ክፍተቶችን ለማረምና የሚመለከታቸውን ባለድርሻ አካላት የተቀናጀ ትብብር ለመፍጠር ቀዳሚ እርምጃዎች ናቸው።

ለግጭቱ ሰላማዊ መፍትሔ ለማፈላለግ የሚደረገው ጥረት አስፈላጊነት እንደተጠበቀና በክልሉ ለሚደረጉ የሰብአዊ እርዳታ አቅርቦቶች ጥበቃና ለተደራሽነቱ ትብብር እንደሚቀጥል መገለጹ የሚበረታታ ሆኖ፣ የሲቪል ሰዎች ደኅንነትና ሰብአዊ መብቶች ጥበቃ ቅድሚያ ሊሰጠው ይገባል።

በአሁኑ ወቅት በአብዛኛዎቹ የትግራይ አከባቢዎች የመብራት፣ የስልክ እና የውሃ አገልግሎት በመቋረጡ በክልሉ ነዋሪዎች ላይ ከባድ የኑሮ ጫና እያስከተለ ይገኛል። የባንክ አገልግሎት መቋረጥና የጤና አገልግሎት አቅርቦትና ተደራሽነት ውሱንነት ችግሩን አባብሶታል።

በትግራይ ክልል የሚንቀሳቀሱ ሀገራዊና ዓለምአቀፍ የእርዳታ ድርጅቶች የኤሌክትሪክ እና የስልክ አገልግሎት መቋረጥን ጨምሮ የሌሎች አቅርቦቶች እጥረት የሰብአዊ ድጋፉን በከፍተኛ ደረጃ እንደጎዳውና በተለያዩ አካባቢዎች የሚኖሩ ነዋሪዎች፣ የሀገር ውስጥ ተፈናቃዮች እና ስደተኞች ስለሚገኙበት ሁኔታ ማወቅ አስቸጋሪ እንዳደረገው ይገልጻሉ።

በአዲስ አበባ ከተማ የትግራይ ክልል ተወላጅ የሆኑ ነዋሪዎችና የሚዲያ ሰዎችን ጨምሮ፣ ሌሎች ከጉዳዩ ጋር ግንኙነት አላቸው በሚል ተጠርጥረው የታሰሩ ሰዎችን ሁኔታ ኮሚሽኑ በመከታተል ላይ ይገኛል። ይህም በነዋሪዎች ላይ ማንነትን በመለየት ለጥርጣሬ እና መድልዎ የሚያጋልጥ ተግባር እንዳይሆን ስጋት የሚያሳድር ነው።

በተጨማሪም፣ በክልሉ ዩኒቨርሲቲዎች የሚማሩ ወጣቶች ወላጆችና ቤተሰቦች ተማሪዎቹ በአሁኑ ወቅት ስለሚገኙበት ሁኔታ ተገቢው ምላሽ እና ማብራሪያ እንዲሰጣቸው የሚመለከታቸውን የመንግስት አካላት በመጠየቅ ላይ ይገኛሉ።

የኢሰመኮ ዋና ኮሚሽነር ዶ/ር ዳንኤል በቀለ የነዋሪዎችን ደኅንነት ማረጋገጥ ቀዳሚው የመንግስት ግዴታ መሆኑን አስታውሰው፣ “በክልሉ የሚገኙ ነዋሪዎች ስላሉበት ሁኔታ የተገቢው መረጃ ማነስ ከተለያዩ አቅጣጫዎች ከሚደመጡ ዘገባዎችና ንግግሮች ጋር ተዳምሮ ነዋሪዎችን ስጋት ላይ የሚጥል ነው።

የተኩስ አቁሙ በሁሉም በግጭቱ ተሳታፊ በነበሩ ወገኖች ሁሉ በቁርጠኝነት መከበር እና የመሰረታዊ አገልግሎቶች በአፋጣኝ መመለስ፣ አጠቃላይ ሁኔታውን ለማሻሻል፣ በትግራይ ክልል ለተፈጠረው ችግር ዘላቂ መፍትሔ ለማፈላለግ፣ እንዲሁም ሰብአዊ አቅርቦቱ እንዳይቋረጥ የሚደረገውን ጥረት የሚያግዝ ነው።

በተጨማሪም ማንኛውም አይነት እስር ሁልጊዜም ሕጋዊ ሥርዓትን የተከተለ ሊሆን ይገባል” ብለዋል። ዋና ኮሚሽነሩ አክለውም በየትኛውም የሀገሪቱ ክፍል የሚገኙ የመንግስት እና መንግስታዊ ያልሆኑ አካላት ሁሉ ሁኔታውን የሚያባብሱ፣ በሕዝቦች መካከል ጥላቻና ጥርጣሬን ሊፈጥሩ ከሚችሉ ንግግሮች እንዲቆጠቡ ጥሪ አቅርበዋል።

Exit mobile version