Site icon ETHIO12.COM

የጸጥታው ምክር ቤት በህዳሴ ግድብ ዙሪያ የሚያደርገውን ስብሰባ የሚቃወም ሰልፍ ማምሻውን በኒው ዮርክ ይካሄዳል

የተባበሩት መንግስታት ድርጅት (ተመድ) የጸጥታው ምክር ቤት የሚያካሄደውን ስብሰባ በመቃወም ዛሬ ማምሻውን በኒው ዮርክ በሚካሄደው ሰልፍ ለድርጅቱ የሚሰጥ ደብዳቤ መዘጋጀቱም ተገልጿል።

የጸጥታው ምክር ቤት ግብጽና ሱዳን ባቀረቡት ጥያቄ አማካኝነት በታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ ዙሪያ ዛሬ እኩለ ሌሊት ላይ ስብሰባ ያደርጋል።

በአሜሪካ በተለያዩ ግዛቶች የሚኖሩ ኢትዮጵያውያንና ትውልደ ኢትዮጵያውያን ምክር ቤቱ የጠራውን ስብስባ በመቃወም ኒው ዮርክ በሚገኘው የተመድ መስሪያ ቤት ተገኝተው ሰልፍ እንደሚያደርጉ በዋሺንግተን ዲሲ ሰላምና አንድነት ግብረሃይል ኢትዮጵያ አባል አቶ ዳዊት አላምቦ ለኢዜአ ገልጸዋል።

ሰልፉ በኢትዮጵያ ሰዓት አቆጣጠር ከምሽቱ 2 ሰዓት እስከ 4 ሰዓት ከ30 ድረስ እንደሚካሄድና በሺዎች የሚቆጠሩ ዳያስፖራዎች ይሳተፋሉ ተብሎ እንደሚጠበቅ አመልክተዋል።

በሰላማዊ ሰልፉ ላይ በኒው ዮርክ፣ ኒው ጀርሲ፣ ቦስተን፣ ኮኔቲከት፣ ቨርጂኒያ፣ ዴልዌር፣ ፔንሲልቫኒያ፣ አትላንታ፣ ዋሺንግተን ዲሲ፣ ሜሪላንድና በሌሎች አካበቢዎች የሚገኙ ኢትዮጵያንና ትውልደ ኢትዮጵያውያን ይሳተፋሉ ተብሏል።

“የፀጥታው ምክር ቤት በሕዳሴ ግድቡ ላይ የሚያደርገውን ጣልቃ ግብነት ማቆም አለበት” የሚለውን መልዕክት ማስተላለፍ ዋንኛው የሰልፉ አላማ እንደሆነ ነው አቶ ዳዊት የጠቆሙት።

የሰልፉ ተወካዮች ለጸጥታው ምክር ቤት የተጠራውን ሰልፍ በመቃወም የተዘጋጀውን ደብዳቤ ለድርጅቱ ያስገባሉ ብለዋል።

የደብዳቤው ይዘት ኢትዮጵያ ሕዝቧን የኤሌትሪክ ሃይል ተጠቃሚ ማድረግ፣ ኢኮኖሚያዊ ተጠቃሚ መሆንና ከተፋሰሱ አገራት ጋር በትብብር ማደግ እንጂ የታችኞቹን ተፋሰስ አገራት የመጉዳት ፍላጎት እንደሌላት የሚያስረዳ እንደሆነ አመልክተዋል።

ግድቡ የኢትዮጵያ የውስጥ ጉዳይ በመሆኑ ተመድ ጣልቃ መግባት እንደሌለበት በደብዳቤው ላይ መስፈሩንም ነው አቶ ዳዊት ያስረዱት።

“ኢትዮጵያ የውሃ ሃብቷን የመጠቀም መብቷን ማንም ሊከለክላት አይችልም፣ ኢትዮጵያ በጋራ የመጠቀም ፍላጎት እንጂ ማንንም የመጎዳት ፍላጎት የላትም፣ ዓለም በኢትዮጵያ ላይ የሚያደርገውን አፍራሽ ተጽእኖ ማቆም አለበት እንዲሁም ተመድበኢትዮጵያ የውስጥ ጉዳይ ጣልቃ መግባት የለበትም” የሚሉ ሀሳቦችን ያዘሉ መልዕክቶች በሰልፉ እንደሚተላለፉ ጠቁመዋል።

የሰላማዊ ሰልፉ አስተባባሪዎች በአሜሪካ የሚኖሩ ግብጻውያን በኒው ዮርክ ከተማ ሰልፍ እንደሚያደርጉ መረጃ እንዳላቸው ገልጸዋል።

“ኢትዮጵያውያንና ትውልደ ኢትዮጵያውያን በተፈቀደላቸው ቦታ ማስተላለፍ የሚፈልጉትን መልዕክት ብቻ እንደሚያስተላልፉና የግብጽ ሰልፈኞችም ባላቸው መብት ተጠቅመው ሀሳባቸውን ያስተላልፋሉ” ብለዋል።

ሰልፉ በዋሺንግተን ዲሲ ሰላምና አንድነት ግብረሃይል ኢትዮጵያና በኒው ዮርክ የሚገኙ የሲቪክ ማህበረሰብ ድርጅቶች ሰልፉን በጋራ ማዘጋጀታቸውን አመልክተው ኢትዮጵያዊያን ሁሉ በአገራቸው ጉዳይ አንድ በመሆን የውጪ ጫናዎችን እንዲመክቱ ጥሪ አቅርበዋል።

Ena

Exit mobile version