Site icon ETHIO12.COM

ለተሻለ ነገ ዛሬ እንደማመጥ

ሞሼ ሰሙ

በጦርነት አሸንፎም ሆነ ተሸንፎ ልቡ የፈቀደውን ያደረገ ስርዓት፣ መንግስት ወይም ቡድን በዓለም ላይ የለም፡፡ ይዋል ይደር እንጂ ጦር አውርድ ባዮች እርስ በርሳቸው ተጫርሰውና ሕዝብ አጫርሰው አቅማቸው ሲሟጠጥና ጉልበታቸው ሲዝል ሁሉም ወደ ድርድር ጠረጴዛ መምጣታቸው አይቀርም፡፡ የትናንት አሳዳጅ የዛሬ ተሳዳጅ፤ የዛሬ ተሳዳጅ ደግሞ የነገ አሳዳጅ፣ ትናንት ግፍ ተፈጸሞብኛል ባይ ዛሬ ግፍ ፈጻሚና ሂሳብ አወራራጅ ተራ በተራ በመሆን ሁላችንም በአዙሪት ውስጥ ተዘፍቀን እንደምንዳክር በተግባር እያየነው ነው፡፡

ጦርነት መፍትሔ አይሆንም፣ ሆኖም አያውቅም ቁጭ ብለን ሰጥቶ በመቀበልና በመርህ እንደራደር ሲባል ሌላ ተአምር ኖሮ ሳይሆን ጦርነት የመጨረሻውን ሽንፈት ለመበቀል በትንንቅ ውስጥ ተዘፍቀን ወደ ከፋ እልህ፣ መጠፋፋት፣ ጭካኔና ማምለጫ ወደሌለው አዙሪት ውስጥ መግባትን የግድ ስለሚል ነው፡፡ ዛሬ ላይ ጦርነቱ ከአንዱ ሕዝባዊ ትግል ወደ ሌላው ሕዝባዊ ትግል ተሸጋግሮ ታጠፋኛለህ ወይም አጠፋሃለሁ የሚል ሆኗል፡፡ ይህንን መጠፋፋት ለመቀልበስ ሲባል ሌላ ሕዝባዊ ትግል ልታዋልድ ሀገራችን በምጥ ላይ ነች፡፡

በዚህ ሂደት ጦርነቱም እየተባዛ በመቀጠል፤ አዳዲስ ጦረኞች ከየራሳችን ክልላዊ እምብርት ተዋልደውና ተራብተው በቅርቡ ሁሉን አቀፍ ጦርነት ውስጥ ተዘፍቀን መፍትሔው እንደ ሰማይ ሊርቀን እንደሚችል እገምታለሁ፡፡ እዚህ ላይ የጎረቤት ሀገሮችና የዓለም አቀፍ ማህበረሰብን ጣልቃ ገብነት ጨምሩበት እንግዲህ !

ሰርቢያ፣ ሶርያ፣ የመንና ሶማሊያ ሪዋንዳ ወዘተ (Sectarianism) በሴክቴርያኒዝም ብጥስጥሳቸው የወጣውና አንዳንዶቹ አጠብቂኝ ውስጥ ተቀርቅረው የቀሩት፣ በዚህ ዘመን ከንግግር ይልቅ አንዳቸው አንዳቸውን በጦርነነት ለማሸነፍ እንችላለን ብለው በመታበያቸውና ትልልቅ ጦርነቶችን ቀስቅሰው እልፍ ትንንሽ ጦርነቶችን መጸነስና መወለድ በመቻላቸው ነው፡፡

ዛሬ ኢትዮጵያ ከዚህ ውጥንቅጥ ብዙም የራቀች አይደለችም፡፡ በየአቅጣጫው የጦርነት ነጋሪት ጉሰማው እያደገና እየጎላ በመምጣት ከአንድ ጦርነት ውስጥ ሌላ ጦርነት እየተረገዘና እየተወለደ ጥላቻውና እልቂቱም በመስፋፋት ላይ ነው፡፡ ጎረቤት ሀገሮች ዛሬ ፈራ ተባ ቢሉም ቀን እየጠበቁልን እንደሆነ መገመት ይቻላል፡፡ ምዕራባውያም በለመዱት መንገድ የቀሰቀሱትና ያባባሱትን ጦርነት ሲከር በቅጡ ሳያቦኩና ሳይጋግሩ ጥለውን እንደሚፈረጥጡ የታወቀ ነው፡፡ ወገን፣ ለራሳችን ያለነው እራሳችን ብቻ ነን፤ ለተሻለ ነገ ዛሬ እንደማመጥ እላላሁ!!


Exit mobile version