የአንዳርጋቸው ጽጌ የሀሳብ ስብራቶች !

ለአቶ አንዳርጋቸው ጽጌ ምክር ቢጤ ወርዉር ብባል ልል የምችለው ዘለግ ያለ የጥሞና ጊዜ reflection time እንዲወስድ ነው። ያለንበት ወቅት በማህበራዊ ሚዲያ የተላቆጠ ድንብርብሩ የወጣ ሁላችንም ያበድንበት የተዋከብንበት ዘመን ነው። አንዳርጋቸው ጽጌ በሳምንታት ጊዜ ውስጥ የዲያስፖራው ፖለቲካ አማኑኤል ሆስፒታልን የሚያስንቅ በቀውስ ውስጥ ያሉ ሰዎች መራከቢያ መንደር መሆኑን መረዳቱ አይቀርም። እጅግ አከብረው የነበረው አንዳርጋቸው ጽጌ ወጣቶችን ከህይወት ልምዱ ማስተማር ቢሳነው እንኳ መጪው ህይወቱ በሽምቅ ትግል ቅዠትና በዲያስፖራ እንካ ሰላንትያ ሲላሽቅ ማየት አልሻም።

አቶ አንዳርጋቸው ምንአልባትም ለሶስተኛ ጊዜ ” ፋኖ ተሰማራ እንደ ሆቺሚኒ እንደ ቼ ጉቬራ ” ውሳኔ ላይ መድረሱን በአደባባይ አስታውቆ ወደ ስደት ሀገሩ እንግሊዝ አምርቷል። አንዳርጋቸው እጅግ አከብራቸው ከነበሩ የኡትዮጵያ ፖለቲከኞች መሀከል ነው። በሶስት ምክንያቶች ። አንዳርጋቸው የተግባር ሰው ነው he can walk the talk kind of personality. አንዳርጋቸው ከብዙ የሀገራችን ፖለቲከኞች በተለየ የቁስና የገንዘብ ምርኮኝነትን ሲጠየፍ የኖረ ሰውም ነው። ከዚህም ባለፈ አንዳርጋቸው ሀሳቡን ከሀሜትና አሉባልታ ይልቅ በጽሁፍ በድፍረት በአደባባይ ማቅረብ የተካነ ፖለቲከኛም ነው። ከብዙ በጥቂቱ የእነዚህ የስብዕና ሰበዞቹ አድናቂ ነበርኩ።

የሰሞኑ የአንዳርጋቸው ውሳኔ ብዙ ግርምት ፈጥሮብኛል። ፖለቲከኞች ( በአጠቃላይ የሰው ልጅ ) እንደ ሽንኩርት በተነባበሩ ቅርፊቶች ውስጥ የተደበቁ ፍጥረቶች እንደመሆናቸው ይኼን ሰሞን አንዳርጋቸው ይዞት የመጣው የአቋም ለውጥ ቀድሞ በአደባባይ በንግግር ፣ በመጽሀፍና መገናኛ ብዙሃን ከሚያነሳቸው ሀሳቦች አንጻር ” ይሄን ሰው አላውቀውም ነበር ? ” ብዬ ራሴን እንድጠይቅ አስገድዶኛል። በዚህ ጽሁፌ አንዳርጋቸው ሰውዬውን ስም ሳላጎድፍ አዲሶቹ ሀሳቦቹ ላይ ጥያቄዬን አነሳለሁ።

* የምንስማማባቸው ነጥቦች

አንዳርጋቸው ጽጌ ብልጽግና መራሹ መንግስት ሀገር ማስተዳደር እንደተሳነው ፣ ሌብነትና ዝርፊያ የስርአቱ መገለጫ መሆኑን ተናግሯል። በዚህ እኔም እስማማለሁ የብልጽግና ሹሞች ለህዝብ የገቡትን ቃል ዘንግተው በህወሃት/ኢህአዴግ ዘመን በባሰ ህዝብ እየተማረረ ፣ አዲሶቹ ገዥዎች new ruling class ከመሆን የተሻገረ ፋይዳ እንዳላመጡ ብዙ ክርክር አያሻውም።

* ህወሃትና አንዳርጋቸው

አንዳርጋቸው ጽጌ ወዳጄ ከሚለው አቢይ አህመድ የተለየበት አንዱ ምክንያት የፕሪቶርያው የሰላም ስምምነትና አፈጻጸሙ ነው። በግሌ እንደተረዳሁት አንዳርጋቸው ህወሃት ቋንጃውም አንገቱም ተሰብሮ ቢቻል ህልውናው ጠፍቶ ቢሸነፍ ምርጫው ነው። በአንጻሩ አቢይ አህመድ ድርድሩ ለሁለቱም ወገኖች win- win situation እንዲፈጥር አድርጎ የመጣ ይመስለኛል ። በግሌ የኢትዮጵያ መንግስት ጦርነት ለህወሃት በተለይም ለትግራይ ህዝብ በፍጹም ተሸናፊነት የተጠናቀቀ እንዳይመስልና ቂም በቀል እንዳያረግዝ የሄዱበት መንገድ ተመራጭ ነው ባይ ነኝ። በባህላችንም ለተገዳዳሪህ የማርያም መንገድ መስጠት የኖረ ልማድ ነው።

የሁለተኛው ጦርነት አሸናፊ ቸርችል ጦርነት በተሸናፊው ወገን ፍጹም ውርደት ሊጠናቀቅ እንደማይገባ እንዲህ ግልጾታል In War: Resolution; In Defeat: Defiance; In Victory: Magnanimity; In Peace: Good Will.

See also  እንደ ሱዳን የመሆን ምኞትና ጥድፊያ - የነጻ አውጪ ጋጋታ

አንዳርጋቸው ጽጌ ከህወሃት ጋር ያለው ጸብ ለምን ጠርዝ ረገጠ ብዬ አልጠይቅም። ይልቅስ የአንዳርጋቸው ትውልድ ለጥቆም የእኛ መች ይሆን የእርቅና ስምምነት ህሳቤዎች የሚገቡን ስል ግን መጠየቄ ግድ ነው። እውነታውን ለሚረዳ ህወሃት ፣ ኦነግ ፣ ኦብነግ ፣ ብልጽግና ወዘተ ሙሉ ተሳትፎ የማያደርጉባት ኢትዮጵያ መቼም ሰላም አይኖራትምና በእንቶኔ መቃብር አብዮቱን አልያም ዲሞክራሲን እንገነባለን የሚል ቅዠት ልናቆም ግድ ነው። አለም ኔልሰን ማንዴላንና ዊልያም ዴክለርክን የጋራ የኖቤል ሽልማት የሰጣቸው ዴክለርክ የአፓርታይድ መንግስት መሪ እንደነበረ ዘንግቶት አይደለም አንዳርጋቸውም አቢይና ጌታቸው ረዳ ወዳጅነት አደባባይ ላይ እንደ አዲስ ፍቅረኛ ሲምቧቸሩ ቢመለከት ይሄ ትርኢት ሰላም ካዋለደ ይሁና ሊል በተገባው ነበር።

* ሽምቅ ውጊያ ፣ አብዮት ፣ ጦርነትና አንዳርጋቸው

ሌላው ድንጋጤ የፈጠረብኝ የአንዳርጋቸው ጽጌ ሰሞነኛ አቋም ለሶስተኛ ጊዜ ለብረት ትግል ድጋፍ ለማድረግ መወሰኑ ነው። አንዳርጋቸው ወጣት ሆኖ ከኢህአፓ ጋር ጠብመንጃ አንስቷል ፣ ለጥቆ የግንቦት ሰባትን የብረት ክንፍ ሊያደራጅ ኤርትራ ከትሟል ዛሬ ደግሞ ከሀገረ እንግሊዝ ሆኖ የአማራ በረኸኞችን አይዟችሁ ሊል ወስኗል።

የአንዳርጋቸው ሰሞነኛ አቋም ትልቁ ክፍተት fallacious assumption የአማራ ተዋጊዎች በብረት ትግል በበረቱ ወቅት ተሰሚነታቸው ይጨምራል የአማራ ህዝብ ጥያቄዎችም ለሀቀኛ ድርድር የሚቀርቡበት ጉልበት ይመጣል የሚል ይመስለኛል ። አንዳርጋቸው ትልቁ የሳተው ጉዳይ በብሄር ለብሄር የነፍጥ ግጭት መጠፋፋት እንጂ እንደራደር ብሎ መጨረሻ እንደሌለ ነው። እነ አንዳርጋቸው የአማራን የነፍጥ ትግል አስፈላጊነት በሚሰብኩበት በዚህች ደቂቃ they’re justifying the armed resistance of other ethnic militias on the other way. አማራ በብረት ትግል ሊመጣብን ነውና ወደ ውይይት እንሂድ ፣ ብሶቱን እንስማው የሚል ብሄረተኛ ማግኘታቸውን እንጃ።

ለአንዳርጋቸው መምከር ባይኖርብንም የብረት ትግልን ትጀምረዋለህ እንጂ መጨረሻውን አንተ አትወስነውም። በ1990 ዎቹ ላይቤሪያ ውስጥ ጸረ መንግስት ትግል የጀመሩት ፖለቲካ እናውቃለን የሚሉቱ ነበሩ። ወደ ኃላ ላይ ግን ጦርነቱን የመሩት እነ ጄነራል mosquito የተሰኙ የ 18 አመት ያልዘለላቸው ከቁርስ በፊት እንትኗን በማለዳ የሚያጨሱ እብዶች ነበሩ።

ጦርነትን የፖለቲካ መሳሪያ አድርገው ለሚሰብኩ ሰዎች ፣ የዛሬው አንጻራዊ ሰላም ላንገሸገሻቸው ወዳጆቼ ዘወትር የምሰጠው ምክር ” እዚያም ቤት እሳት አለ ” የሚል ነው። በዛሬይቱ ኢትዮጵያ እጁ ላይ እሳት ያልያዘ ብሄር የለም ተመራጩ መንገድ ሁሉም በትርክቱም በእጁም የያዘውን አጥፊ የጥላቻ እሳት አስቀምጦ የማያቋርጥን ውይይት ቋሚ የፖለቲካ ልማድ ማድረጉ ነው።

See also  ድህነት እና አስተሳሰብ ያላቸው ትስስር ምን ይመስላል ?

* እድሜ ፣ የህይወት ተሞክሮና አንዳርጋቸው

አንዳርጋቸው ጽጌ ሰሞኑን በሰጠው ቃለመጠይቅ አንድ ወቅት ላይ አቢይ አህመድ እንደ ሀገር መሪ ፣ ልምድ እንዳለው ፖለቲከኛ statesman ይናገር ዘንድ ምክር እንደለገሰው ነግሮናል። የእኔ ጥያቄ አንዳርጋቸው ራሱ እንደ ዕድሜ ጠገብ ፣ ባለብዙ ልምድና ተሞክሮ ባለቤት ፖለቲከኛ ይንቀሳቀሳል ወይ ? ነው ።

አንዳርጋቸውና የእርሱ ትውልድ ኢትዮጵያ አለኝ ያለችውን ጥሩ ትምህርት አስተምራቸዋለች። ከተማሪዎች ንቅናቄ አንስተው እስከ ሰሞኑ ግጭት ብዙ የፖለቲካ ውጣ ውረድ ውስጥ ቀጥተኛ ተሳታፊ እየሆኑ አሳልፈዋል። ይሄ ልምድና ተሞክሮ ቢያንስ ቢያንስ አንዳርጋቸው ዛሬ በሬ ሸጦ ክላሽ ለሚገዛ ወጣት ህይወቱ አጉል እንዳይቀጠፍ ማስተማሪያ ሊሆን ይገባ እንጂ የሽምቅ ውጊያ ምክር የሚሰጥበት የህይወት ተሞክሮ ባይሆን ይመረጣል።

እንደአለ መታደል ሆኖ በየዩኒቨርሲቲዎቹ እየዞረ ከህይወት ልምዱ በመነሳት ጽንፍ የረገጠን ብሄር ፖለቲካን የሰላም ጠንቅነት ፣ ያለመቻቻል ፖለቲካን ሀገር አፍራሽነት ሊሰብክ ይገባ የነበረው አንዳርጋቸው ዛሬም ይበሳጫል ፣ ዛሬም የቁጣና አልበገር ባይነት ፖለቲካን ያቀነቅናል ዛሬም ፋኖ ተሰማራን እንደ ትግል መዝሙሩ ያዜመዋል።

ማጠቃለያ

የዛሬ አራት አመት አንዳርጋቸው ጽጌ ከብዙ ብሄር የተወለዱ ኢትዮጵያውያን ቁጥር በሀገሪቱ ትልቅ ቁጥር እንዳላቸውና የዜግነት ፖለቲካን ለማዋለድ ትልቅ አቅም ሊፈጥሩ እንደሚችሉ በፍጹም እርግጠኛነት ይነግረን ነበር። የዛሬ አራት / አምስት አመት አንዳርጋቸው ጽጌ ከኦሮሞ ኢትዮጵያውያን ጋር የሚጋራው ትውልድ እንዳለው ቆጥሮ አዲስአበባ የአያቶቹ ከብቶች የግጦሽ ስፍራ እንደነበረች ያስረዳን ነበር። የዛሬ አስራ ምናምን አመት አንዳርጋቸው ጽጌ ” ላንቺ ነው ኢትዮጵያ ” ሲል ለአማራውም ፣ ለኦሮሞውም ፣ ለትግሬውም እኩል የምትመች ኢትዮጵያን በመስዋእትነት የማጽናት ግዴታን ዘምሮልን ነበር። የአንዳርጋቸውን ሰሞነኛ አቋም ባለፉት በርካታ አመታት በጽናት ይዟቸው ከነበሩት ህሳቤዎቹ ጋር ማስታረቅ ለእርሱ ካልሆነ በቀር ለብዙዎቻችን ከባድ ነው።

ይሄን ጽሁፍ ሳጠቃልል ለአቶ አንዳርጋቸው ጽጌ ምክር ቢጤ ወርዉር ብባል ልል የምችለው ዘለግ ያለ የጥሞና ጊዜ reflection time እንዲወስድ ነው። ያለንበት ወቅት በማህበራዊ ሚዲያ የተላቆጠ ድንብርብሩ የወጣ ሁላችንም ያበድንበት የተዋከብንበት ዘመን ነው። አንዳርጋቸው ጽጌ በሳምንታት ጊዜ ውስጥ የዲያስፖራው ፖለቲካ አማኑኤል ሆስፒታልን የሚያስንቅ በቀውስ ውስጥ ያሉ ሰዎች መራከቢያ መንደር መሆኑን መረዳቱ አይቀርም። እጅግ አከብረው የነበረው አንዳርጋቸው ጽጌ ወጣቶችን ከህይወት ልምዱ ማስተማር ቢሳነው እንኳ መጪው ህይወቱ በሽምቅ ትግል ቅዠትና በዲያስፖራ እንካ ሰላንትያ ሲላሽቅ ማየት አልሻም።

ነጻ አስተያየት – በ Samson Michailovich


Leave a Reply