Site icon ETHIO12.COM

ታዳጊ አልባ የትግራይ መንደሮችን

Mesay Mekonnen

የህወሀት ቡድን ማንሰራራት የሚችለውን ያህል አንሰራርቷል። ከዚህ በላይ ወዴትም ሊለጠጥ አይችልም። መቃብር ፈንቅሎ ከወጣና መቀሌን በዊልቸርና ክራንች ታግዞ ከያዘ በኋላ ነፍስ ያለው ሁሉ እንዲታጠቅና እንዲሞትለት የክተት አዋጅ ለፍፎ አቅም ሊፈጥርለት የሚችልን ነገር ሁሉ በማድረግ ወደፊት ለመግፋት ተጣጥሯል። የመጨረሻው ጡዘቱ ላይ ደርሷል። ከእንግዲህ ወደላይ የሚያሳድገው ሃይል አይኖርም። ወደጎን የሚለጥጠው አቅምም የለውም። መሄድ የሚችለውን ያህል ሄዷል።

የትግራይ መንደሮችን ታዳጊ አልባ እንዲሆኑ በማድረግ፡ ከእርሻ መሬቶች ላይ ገበሬውን በማንሳት ለጦርነት ማግዷል። የቀረው እናት ማህጸን ውስጥ የሚገኝ ጽንስ ካልሆነ በቀር ለስክሪፕቶና እርሳስ ያልጠነከረን እጅ ክላሽ እንዲጨብጥ በማድረግ በዓለም ታሪክ የጭካኔ ጥግ የታየበትን ዘግናኝ ትራጄዲ በመፈጸም ተመዝግቧል። ከእንግዲህ ምን ሊያደርግ ይችላል?

ከጦር ግንባሮች የምንሰማቸው ወሬዎች ጥንቃቄን የሚፈልጉ ናቸው። የሟሸሸው የህወሀት ቡድን ከከፈተው አስቀያሚ ጦርነት ባሻገር በወሬ ሀገር ለማሸበር ሰፊ እንቅስቃሴ እያደረገ ይገኛል። ህወሀት በምላሱ አዲስ አበባ ደርሷል። በመሬት ላይ ግን ትግራይን ተረካቢ ትውልድ እንዳይኖራት በሚያደርግ ጦርነት ውስጥ ይንደፋደፋል።

በማህበራዊ መገናኛ መድረኮች በተሰማሩ የወሬ ሰራዊቶቹና ከማዶ ሆነው በሚያራግቡለት የምዕራቡ ሚዲያዎች አማካኝነት ሰማይ ምድሩን በሀሰተኛ የድል ዜናዎችና ገድሎች አጥልቅልቆታል። ጦር ከፈታው ወሬ የፈታው እንደሚባለው በዚህ በኩል ያለው ወገንም ለፕሮፖጋንዳው እጅ በመስጠት ሲረበሽና ሲጨነቅ ይስተዋላል። አንዳንድ ወገኖች በውስጥ መስመር በሚልኩት መልዕክት ውስጥ የማነበው ጥልቅ የሆነ ባዶ ፍርሃትን ነው። እንዲህ ዓይነቱ ስሜት ለጠላት ወገን ከሚሳይል ምት የላቀ፡ ገዢ መሬት ከመቆጣጠር የተሻለ ድል የሚያስገኝለት ነው።

ምንም እንኳን የኢትዮጵያ ህዝብ ከመንግስት የሚያገኘው መረጃ ውሱንና ዘግይቶ የሚመጣ ቢሆንም የገጠመንን ፈተና ከግምት ያስገባ፡ የጠላትን አረመኔያዊና ሃላፊነት የጎደለው የእብደት እንቅስቃሴ ታሳቢ ያደረገ ስነልቦና ልንላበስ ግድ ይላል።

የኢትዮጵያ ህዝብ ላይ ጦርነት የከፈተው የህወሀት ቡድን በዓለም የቀደመ ታሪክ ያልተከሰተ፡ ወደፊትም ሊፈጠር ይችላል ተብሎ የማይገመት እጅግ አደገኛ የሆነ ፈተና ደቅኖብናል። የአዶልፍ ሂትለር የመጨረሻዎቹ ወራት እንደሆነው በሰው ጎርፍ፡ በህጻናት ማዕበል ጦርነትን ለማሸነፍ የህወሀት ቡድን ቆርጦ ተነስቷል።

ከአፋር፡ ከራያና ከአደርቃይ ግንባሮች የምንሰማቸው ወሬዎች የሟሸሸው የህወሀት ቡድን ትርጉም ለሌለው ጦርነት የሚልካቸው አዛውንቶችና ህጻናት እንደቅጠል እየረገፉ መሆናቸውን ነው። እነዚህ በሀሽሽ የናወዙ፡ አብዛኞቹም ባዶ እጃቸውን የተላኩት የትግራይ ህጻናትና አዛውንቶች ጥይት ወደሚጮኽበት፡ የመትረየስ ላንቃዎች ወደሚያስካኩበት የኢትዮጵያ ሃይሎች በደመነፍስ ሲግተለተሉና የእሳት እራት ሲሆኑ ላየ የፈጣሪ እርግማን እንጂ ሌላ ምንም ሊል አይችልም።

የኢትዮጵያ ህዝብ ይህን መረዳት ይኖርበታል። አሁን የገጠመን ጦርነት ዓለም የሚያውቀው ዓይነት ጦርነት አይደለም። ወይም የህወሀትን አከርካሪ ለመስበር ከ8ወራት በፊት የተደረገው ጦርነትም አይደለም። ይህ በባህሪው የተለየ፡ ሽንፈቱንም ድሉንም ለመግለጽ የማይመች ጦርነት ነው። የህወሀት ቡድን ብቻዬን አልሞትም በሚል የትግራይን ህዝብ ይዞ ለመጥፋት ከውሳኔ ላይ ደርሶ የከፈተው እጅግ አደገኛ ጦርነት ነው።

መሬት በመያዝ፡ ከተሞችን በመቆጣጠር፡ ገዢ ቦታዎችን በማስለቀቅ ውጤቱ የሚነገር፡ ድሉ የሚበሰር ዓይነት ጦርነት አይደለም። በማህበራዊ ሚዲያዎች ላይ እየተካሄደ ያለውን ጦርነት ከእነዚህ መለኪያዎች አንጻር በመለካት ሽንፈት ገጠመን አልያም ድል አገኘን የሚል ስሜት የሚንጸባረቅበት መሆኑን ታዝቤአለሁ። ይህ ትክክል አይደለም። መሬት ላይ ያለውን እውነትና የጦርነቱን ያልተለመደ አደገኛ ባህሪ በቅጡ መፈተሽ ግድ ይላል።

መሬት ከመያዝና ከተሞችን ከመቆጣጠር ባሻገር መታየት የሚገባው ጦርነት ነው። የእርዳታ እህል እየበላ ህዝብን ከዳር እስከዳር ለጦርነት የማገደውን ህወሀትን ለማስወገድ የኢትዮጵያ ህዝብ ለሽብር ወሬዎችና ፕሮፖጋንዳዎች እጅ ካለመስጠት ጀምሮ ሂደቱን ሃላፊነት በተሞላውና የዜግነት ግዴታን በተወጣ መልኩ ነገሮችን መከታተል ይኖርበታል።

የህወሀት ቡድን የሚችለውን ያህል አድርጓል። በእነአሜሪካ ድጋፍ መውጣት ያለበትን ሁሉ ወጥቷል። ከዚህ በኋላ ወደላይም ሆነ ወደጎን መሄድ አይችልም። በእርግጥም ህወሀት መንገዳችን ላይ የተገተረ የዘመኑ ጎልያድ ነው። ወደሰላምና እድገት ፊታችንን እንዳንመልስ ልብሳችንን እየጎተተ ወደኋላ ሊያስቀረን እየተንፈራገጠ ያለ ቡድን ነው። ከማንም በላይ ለትግራይ ህዝብ ምጽዓት ይዞ የመጣ ታላቅ መርገምት ነው። ይህን በተስፋ መቁረጥ ጥልቅ ስሜት ውስጥ የሚሰቃይን ቡድን ለማጥፋት የጊዜ ጉዳይ እንጂ የማይቻል ሆኖ አይደለም።

በራሱ ጊዜ የሚጠፋ እንደሚሆን ቢታመንም በቀለብ ሰፋሪዎቹ ምርኩዝነት የተወሰኑ ጊዜያትን እያስጨነቀን መቆየቱ አይቀርም። ሰከን ብለን፡ ለአሉባልታና ለፕሮፖጋንዳ እጅ ሳንሰጥ፡ ግንባር ላይ ታሪክ እየሰራ ላሉት ውድ የኢትዮጵያ ልጆች ደጀንነታችንን በሁሉ መስክ ካረጋገጥን ህወሀት ከኢትዮጵያ ትከሻ ላይ እንደተወገደው ሁሉ ከትግራይ ምድርም ለአንዴና ለመጨረሻ ጊዜ ግባዓተ መሬቱ ተፈጽሞ ከእነቆሻሻ ስብዕናው ታሪክ ሆኖ ይቀበራል። አሁንም ሁሉ ነገር በእጃችን ነው።

Exit mobile version