ETHIO12.COM

አትሌቲክስ ፌዴሬሽን ” ሽንፍላው ቤት”

on Day 7 of the Rio 2016 Olympic Games at the Olympic Stadium on August 12, 2016 in Rio de Janeiro, Brazil.

መሮጥ፣ በሩጫ ጀግና መሆን፣መልካም ባህሪና ተወዳጅነት ቢደመሩ የአመራር ጥበበን ሙሉ ክህሎት አያላብሱም፤ በትምህርትና በእውቀት የማይደገፍ ተፈጥሮ የተሳካ መሪ አያደርግም። መለስ ” ዘበኛም ቢሆን” በሚል ለፓርቲ ታማኝ ሾሙ። ከዛ ዲግሪ አላቸው እንዲባል ” ከወፍጮ ተቋማት” በግዢ እንዲታደሉ አደረጓቸው። ለውጡ ሲመጣና ሁሉም ደጅ ሲከፈት ሲክተሩ ሁሉ የተንኮታኮተ የካድሬ ጉሮኖ መሆኑ ታየ። ለዚህ ነው አዲሱ መንግስት ሹመት በሜሪይ እንዲሆን የወሰነው። ይህ በቀጥታም ባይሆን በተዘዋዋሪ ሁሉም ጋር ቫአለም ዓቀፍ ህጎችን ተንተርሶ ሊተገበር ይገባል።

ጽሁፉ ሲጨመቅ

በኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌዴሬሽን ውስጥ ለዓመታት የሚሰራው የነበረው ህገወጥነት ስፍር ቁጥር የለውም። አንዳንዱ ከማሳዘን አልፎ ህሊናን የሚፈትን ነው። የአትሌቶቹን የዕውቀት ደረጃና አቅም ያገናዘበ ክፉ ተግባር ይፈጸም ነበር። መቶ አለቃ ዱቤ ጅሎና ደራርቱ ቱሉ የአትሌት ተወካይ ሆነው አትሌቲክ ፌዴሬሽን ስራ አስፈሳሚ ሆነው ረዥም ዓመታት ስለሰሩ በቂ ምስክርና ሰነድም ናቸው።

ሲዘረፍ፣ አድልዎ ሲደረግ፣ ያለ አግባብ አትሊቱ ሲንገላታ፣ ከህግ ውጭ ውድድር ሲከለከሉ፣ ውድድር ሜዳ ከገቡ በሁዋላ በአንድ ስልክ ከውድድር ሜዳ ሲታገዱና ከትራክ ላይ በፖሊስ እንዲባረሩ ሲደረግ የአትሌት ድምጽ የነበሩት ሻለቃ ደራርቱና “የተከበሩ” ዱቤ ጅሎ ያዩ፣ ይሰሙና አብረው ይወስኑ ነበር። ይህ ሃቅ ነው። ይህን ሃቅ ለዓመታት በሪፖርተር ጋዜጣ ላይ ስዘገብ ነበር። በወቅቱ እጅግ ልብ የሚነኩና በከፍተኛ ደረጃ ሊያስጠይቁ የሚችሉ ጥፋቶና ወንጀሎች ቢፈጸሙም ተቆጣጣሪ አካሉ ደንታ አልነበረውም።

በውቅቱ አትሌቶች ላይ ከዘር ልዩነት ጀምሮ ሲፈጸም የነበረው ጸያፍ ድርጊት በመበርከቱ፣ ሰሚና ፍትህ ሰጪ አካል በመጥፋቱ፣ ተደራጅቶ መታገል አስፈላጊ በመሆኑ እኔ አስተባባሪ ሆኜ አዲስ የአትሌቶች ማህበር ተቋቋመ። ሃይሌ፣ብረሃኔ፣ ስለሺ፣ ጌጤ፣ አሰፋ መዘገቡ፣ ገዛኸኝ አበራ … ያሉበትና በሃይሌ ገብረ ስላሴ ሰብሳቢነት የሚመራ ማህበር ተመስርቶ ስራ ጀመረ።

ሃይሌ ከሲኒማ ቤቱ ግርጌ ቢሮ ፈቅዶ ስራውን የጀመረው የአትሌቶች ማህበር ለዓለማአቀፉ የአትሌቶች ማህበር ደብዳቤ ላከ። ማህበሩ እንኳን ደስ አላችሁ ሲል ወዲያው ምላሽ ሲሰጥ እነ ዱቤ ጅሎ ጦር ሰበቁ። ፌዴሬሽኑ አካኪ ዛራፍ ብሎ መግለጫ ሰጠ። አትሌቶችን ሰብስቦ “ከአዲሱ ማህበር ጋር ብትተባበሩ የውጭ ጉዞ አግዳለሁ” ሲል አስጠነቀቀ።

አዲሱ ማህበር በአራራት ሆቴል ባደረገው ስብሰባ በርካታ አትሌቶች ተገኝተው በደላቸው ተናገሩ። ስብሰባ ፍርድ ቤት እስኪመስል በደል እንደ ጉድ ወረደ። ያ ሁሉ ሲሆን ዱቤ ጅሎ የሚመራውና ሻለቃ ደራርቱ ምክትል የሆኑበት “ተለጣፊው” የአትሌቶች ማህበር ምን ይሰራ እንደነበር መገመት ትርፉ ህምም ብቻ ነበር። አንዱን ለምሳሌ እንዲሆን ላንሳ

ብርሃኔ አደሬ ” የኢትዮጵያ ህዝብ ብራስልስ ለቅሶ ተቀምጫለሁና ድረሱልኝ” ስትል በእንባ ያሰማችው ጩኸት በሪፖርተር እሁድ ጋዜጣ የግንባር ዜና መሆኑንን ተከትሎ ረብሻ ተፈጠረ። በወቅቱ ብርሃኔ በመልካም አቋም ላይ ነብረች። ነገር ግን ከአቴንስ ኦሊምፒክ አሰናብተዋታል። በምትኳ የተመረጠችው ደራርቱ ስትሆን በሰዓት፣ በውድድር ብዛትና በውቅታዊ ብቃት ከብረሃኔ ጋር መወዳደር አትችልም ነበር።

ብርሃኔ ብራስልስ ድምጿን አጥፍታ ሄዳ ከሮጠች ያለ አግባብ ከአቴንስ ኦሊምፒክ መባረሯ ትክክል እንዳልሆነ ስለሚያጋልጥ ብራስልስ ደርሳ፣ ልብስ አውልቃ፣ አሟሙቃ፣ የመወዳደሪያ ትራክ ውስጥ ከገባች በሁዋላ በስልክ በተላከ መልዕክት እንደ ሌባ ተጎትታ እንድትወጣ ተደረገ። ይህ ዜና ዓለም አቀፍ መነጋገሪያ ሆነ። የብርሃኔ ጩኸት ሁሉም በሆዱ ይዞት የነበረውን ብሶት ፈነቀለው። አራራት ሆቴል በተደረገው ስብሰባ ጉድ ተነገረ። ይህ ሁሉ ሲሆን ዱቤ ከልካይና አጋጅ፣ ደራርቱ ፍትሃዊ ባለሆነ ምርጫ ተወዳዳሪ ሆነው የኢትዮጵያ አትሌቶች ተወካይ ሆነ በፌዴሬሽኑ የስራ አስፈጻሚ ኮሚቴ ባለ ድምጽ አባላት ነበሩ። እንግዲህ አዲስ ማህበር ለማቋቋም መነሻው ይህና ይህን መሰል በርካታ ችግሮች ነበሩ።

አቴንስ የሃፍረታችን ሜዳሊያ

በዚህ መልኩ ተበላን

በ2004 የአቴንስ ኦሊምፒክ የሴቶች አስር ሺህ ሜትር ውጤት እንደማይመጣ አስቀድመው በሪፖርተር ማስጠንቀቂያ ለሰጡ አካሎች ዱቤ ብቻ ሳይሆን የውቀቱ የስፖርት ሚኒስትር መላኩ ጴትሮስ ” ብርሃኔንን እኔ እቀዳማታለሁ” የሚል ዕብለት የተሞላው ምልሽ ሰጡ። ቀኑ ደረሰና ደራርቱ፣ እጅጋየሁ ዲባባና እግረ ቅጭኗ ወርቅነሽ ኪዳኔ ተሰለፉ። ወርቅነሽ ከውድድሩ በሁዋላ እዛው አቴንስ ሆና ” ረዳት አጥቼ ተቃጠልኩ” የሚል ልብን የሚነካ ቃለ ምልልስ ለሪፖርተር ሰጠች።

ውድድር ተጀምሮ እስኪያልቅ በሚባል ደረጃ ወርቅነሽ ዙሩን አክርራ ስትመራ እጅጋየሁና ደራርቱ አይግዟትም ነበር። ሶስት ዙር አካባቢ ሲቀር ለመጣት ብትሞክርም አልሆነም። ደራርቱና እጅጋየሁ ሲጠባበቁ፣ አንዱ ሌላውን ሲሽፍን የቻይናዋ Xing Huina እየተራመደች ሄዳ ወርቅ አጠለቀች። በዚህ ሃፍረት የተሞላበት ሽንፈት የተተየቀ፣ የተሞገተ፣ ወይም ስልጣኑንን ያጣ አንድም አካል የለም። አልነበረም። ይልቁኑም በተቃራኒው ሹመት ተሰጥቷል።

የሃይሌ ማፈግፈግ

በአገራችን በመረጃ መሞገትና በአመክንዮ ማሰብ ያልተለመደ በመሆኑ ብዙ ጊዜ ስማቸው የገነኑ ሰዎችን መንካት አግባብ እንዳልሆነ ይታሰባል። እነሱም ይህን ሰለሚያዉቁ ስማቸው በሚነሳበት ጉዳይ ላይ ሳይሆን ባልተባሉት ጉዳይ ማንባትና የተተቹበትን ጉዳይ ትተው ከጉዳዩ ጋር ግንኙነት በሌለው መንገድ ትችቱን ሳይሆን ተቺውን ለማሳጣት ይመርጣሉ። አንዳንዴም ማልቀስ ሁሉ አለ።

ሃይሌ ይህ ማህበር ሲቋቋም መሪ ነበር። ሃላፊነቱን በትልቅ ስሜት ሲረከብ ከትልቅ ሞገስ ጋር ነበር። እንደ አንጋፋ አትሌት ጉዳዩ ስለሚመከተው ማህበሩ ገና ከጅምሩ እጅግ ተስፋ ተጥሎበት ነበር። የማውቃቸው የውጭ ሚዲያ ሰራተኞች ሳይቀሩ መረጃ ሲጠይቁኝ ተስፋዬ ከፍተኛ እንደነበር ስገልጽም ነበር። ስራ አስፈጻሚዎቹ እጅግ ጥልቅ በሆነ ቁጭት ስሜት ነበር የሚሰሩት።

በዚህ መካከል ድንገት አንድ ዜና ተሰማ። የፌዴሬሽኑ ባሪያ የሆነው የአትሌቶች ማህበር ሊቀመንበር፣ የቴክኒክ ክፍል ሃላፊ፣ የፌዲሬሽኑ ስራ አስፈጻሚና የትሌቶች ማናጀር ኮሚሽን ኤጀንት ሽርክና ያለው ዱቤ ጅሎ ” የታላቁ ሩጫ በኢትዮጵያ ታግዶ ፈቃዱ ይነጠቃል” ሲል መግለጫ ሰጠ። ዜናው በማለዳ ከተማውን ሞላው። የመንግስት ሚዲያዎች ደጋገመው ዜናውን ሄዱበት። መከረኛ የውጭ ጉዞ ስላለ ዜናው ተወቀጠ። ሃይሌ ከዛን ቀን ጀምሮ አዲሱን ማህበር ትቶ ጠፋ። እባካችሁን ጠይቁልኝ። ዝርዝር ውስጥ ከገባሁ ስለ ታላቁ ሩጫ የውጭ አገር አካውንቶችና “ትርፍ አልባ” ተብሎ “አትራፊ” ስለነበረው ድርጅት መዘባርቅ ይሆንብኛልና እዚህ ላይ ፍሬን እይዛለሁ። ሙግት የሚፈልግ ካለ ግን …

ከዛ ምን ሆነ?

የስፖርት ቤተሰቡን በመቀራረብና በውጭ ጉዞ ላይ በተመሰረተ ግንኙነት የተሳሳተ መረጃ ሲሰጡት ከነበሩ ሚዲያዎች ጋር ግብግብ የመፍጠር ያህል በኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌዴሬሽን የቆሸሸ አሰራር ሪፖርተር ብዙ ሲዘግብ ነበር።በሪፖርተር በግል እኔ ብቻ ሳልሆን መላው የድርጅቱ ሰራተኞች ከትንሽ እስከ ትልቅ ተሳትፎ ነበራቸው። ለድል ዜና ዕርዕስ ስነመርጥ እንኳን የነበረው ተሳትፎ የምረሳው አይደለም። ሪፖተር በወቅቱ ስፖርቱ ዙሪያ የከረረ ርዕሰ አንቀስ ሁሉ ያዘጋጅ ነበር።

በወቅቱ ስለ አትሌቶች አበክሮ ይሟገት የነበረው ሪፖርተር መሰረት ደፋር እንዳትመረጥ ተደርጎ ስለነበር ከባለሙያዎች በተገሰባሰብ መረጃ መሰረት ጉዳዩን አገራዊ አጀንዳ በማድረግ መሰረት አቴንስ ሄዳ ትራኩ ላይ ተንሳፋ በ5000 ወርቅ ማግኘቷን ማስታወስ ለዛሬ ሃሳቤ አስፈላጊ ሆኖ አግኝቸዋለሁ። መሰረት አዲስ አበባ እንደገባች በመኖሪያ ቤቷ ከሪፖርተር ጋር ባደረገችው ቃለ ምልልስ ” የወርቅ ሜዳሊያው ለሪፖተር ነው” ማለቷ ብቻ ሳይሆን ነብስ ይማርና አስቀድመው ስህተት ሰርተው የነበሩት ዶክተር ወልደምስቀል በገሃድ ይቅርታ ጠይቀዋል።

ይህንና ይህን መስለ ችግሮች አዝሎ በጥቂት ውጤታማ አትሌቶች ስምና ዝና ሲያዘግም የኖረው አትሌቲክስ ፌዴሬሽን ተወርቶ የማያልቅ፣ ተዝቆ የማይጠራ ሽንፍላ የሆነ ቤት ነው። በተለይም ስለ ዱቤ ጅሎ ሲታሰብ በርካታ ገሃድ የሚታዩ የህግ ጥሰቶች ይስተዋላሉ። አብሮ በአትሌት ተወካይነት የራ አስፈሳሚ ኮሚቴ አባል፤ የቲክኒክ ኮሚቴ ሰብሳቢ፣ በሁዋላም የቴክኒክ ክፍሉ ተቀጣሪ ሃላፊ የሆኑበት አግባብ የቤቱን ሽንፍላነት የሚያሳይ ነው።

አቶ ዱቤ እንኳን በሹመት ስፖርቱን ሊመሩ ቀርቶ በወንጀል ሊጠየቁ የሚገባቸው፣ በህግ በሚከለከል ተግባር ተሳትፈው የአትሌቶች ማናጀር በመሆን ከያንዳንዱ አትሌት የአሸናፊነት ክፍያ አስራ አምስት በመቶ ሲዘርፉ የኖሩ ናቸው። አቶ ዱቤ ( ተከበሩ የፓርላማ አባል) የአትሌት ማናጀርነቱን ስራ ሲሰሩ የነበሩት በፌዴሬሽኑ የቴክኒክ ክፍል ዳይሬክተርነት ወንበር ላይ ተቀምጠው ሲሆን የንግድ አጋራቸው ደግሞ ዶናዶኒ የሚባሉ ጣሊያናዊ ነበሩ።

አብረዋቸው የሚሰሩት ጣሊያናዊው ማናጀር ዶናዶኒ የያዛቸው አትሌቶች ቅድሚያ አበራታች መድሃኒት በመቃም ተጥርጥረው ምርመራ ሲደረግባቸው እንደነበር፣ ለዚህ ሪፖርት አያመችም እንጂ ሌሎችም ከመድሃኒት ጋር የተያያዙ አጉል ድርጊቶች ሲፈጸሙ ዱቤ አያውቁም ብሎ ማሰብ የዋህነት ነው ። አትሌቶቹ ሲያሸንፉ ለሚገኘው ጥቅም በማሰብ መድሃኒት ማለማመዱ ኢትዮጵያን በማትታወቅበት የዶፒንግ ሊስት ውስጥ አስገብቷት ምን ያህል ፈተና እንዳጋጠመን የመንግስት ሚዲያዎች ሳይቀሩ ሲዘግቡ ነበር።

ዱቤ የብቃታቸውም ጉዳይ ቢሆን እጅግ መነጋገሪያ ነው። ይህንኑ ጉዳይ ማታ ማታ ኮተቤ የሚያስተምሯቸው፣ ቀን ቀን እሳቸው የቴክኒክ ኮሚቴ ሰብሳቢ ሆነው የሚጠርንፏቸውና በረድፍ የውጭ አገር እድል የሚሰጧቸው መምህራን የሚያውቁት ሃቅ በመሆኑ አልፈዋለሁ። ስለዚህ እንደ ዱቤ ጅሎ አይነት ሰው የኢትዮጵያን ስፖርት እንዲመራ የፈቀዱ ሁሉ ሊያፍሩ ይገባል የሚል እምነት አለኝ። በሩጫም ቢሆን ይህ ነው የሚባል ታሪክና ልምድ የሌለው፣ በበረሃ ውድድሮች ለማድመቂያ የሚሳተፍ ከመሆኑ በዘለለ ሌላ ገድልም. ልምድም፣ ዝናም የለውም።

ሻለቃ ሃይሌ ገብረስላሴ ምን ሸክኮት ወንበሩን ለሻለቃ ደራርቱ አስረክቦ ፌዴሬሽኑንን እንደተለየ በግልጽ ባይታወቅም፣ ዱቤ ፌዴሬሽኑ ውስጥ ዛሬም ድረስ እጁ ረዥም እንደሆነ መረጃዎች አሉ። የፌዴሬሽኑ ጸሃፊ አቶ ቢልልኝ ከአገሪቱ ህግ ባፈነገጠ መልኩ የአማተር አገልጋዮች በሚወከሉበት የፌዴሬሽን መሪነት ላይ ሲቀመጡ ዱቤ የስፖርት ሚኒስትር ሆኖ አጽድቋል።

አቶ ቢልልኝ መቆያ የዳርት ፌዴሬሽን ፐሪዚዳንት ናቸው። በተመሳሳይ የአትሌቲክስ ፌዴሬሽን ጸሃፊ ናቸው። ሻለቃ ደራርቱ ይህ ታውቃለች። ዱቤም ይህን ጠንቅቆ ያውቃል። ታዲያ ሁለቱ የረዥም ጊዜ ወዳጆች እንዴትና ለምን ህግ ሲጣስ ዝም አሉ? ዱቤ በምን ድፍረት ህግ እየተጣሰ መሆኑንን እያወቀ የአቶ ቢሊልኝን ፐሬዚዳንትነት አጸደቀ? አትሌቲክስ ውስጥ እያለ ምን ግንኙነት ስለነበራቸው ነው ህግ እንዳያስከበር ያነቀው? ይህ ሰፊ ማብራሪያ የሚፈልግ ጉዳይ ነው። ሻለቃ ደራርቱም ለዚህ ጉድይ ምላሽ ልትሰጥ ግድ ያላታል።

ሰሞኑንን የተፈጸመውን አሳዛኝ ታሪክ ለማንሳት ያለውፈውን እንደማሳያ አነሳሁ እንጂ ጉዳዬ ወዲህ ነው። ለሜቻ ግርማ በዶክተር አያሌው ውሳኔ ከቶኪዮ ኦሊምፒክ መሰናበቱን እንደሰማሁ ግለ ታሪኩን አየሁ። አትሌቱ በዓመት ጊዜ ውስጥ ከአርሲ ተነስቶ ስሙ አለም ላይ የገነነ ብቁና ድንቅ አቋም ያለው ሯጭ ነው። ሲሮጥን አስቸጋሪውን የ3000 መሰናክል ውታ ውረድ ያለበት የሩጫ አይነት ነው።

ሌላ ሰው ለማስገባት አሰልጣኞቹ ወግዱ ተብለው በህክምና ውሳኔ ከዋናው የቶኪዮ ቡድን የተቀነስው ለሜቻ በውሳኔው ንዴት ተንደርድሮ ሞናኮ በመሄድ አዲስ ክብረወሰን አስመዝግቦ ሲያሸንፍ ዶክተር አያሌውን ” አፍረሃል” ብሎ የጠየቀ ሚዲያ የለም። ፌዴሬሽኑን ሲያስተነቅቁ የነበሩ አሰልጣኖችን አስተያየት የተየቀ፣ እሱንም ያናገር ስለመኖሩ አልተሰማም። እንደ ስፖርት የበላይ ሃላፊ ዱቤ ጅሎ ” ነገሩ እንዴት ነው?” ማለቱ አልተሰማም። ሻለቃ ደራርቱም ብትሆን ስለያዘችው አቋም ያሳበቀችን ወፍ የለችም።

በዚህ ሁሉ ፍትጊያ ውስጥ አልፎ በአኖካና በኦሊምፒክ ኮሚቴ ትንቅንቅ ለሜቻ ከዋናው የቶኪዮ ልዑክ ዝርዝር ውስጥ መካተቱ ሲሰማ እአቴንስ ኦሊምፒክ ወቅት ራሳችን በራሳችን ላይ ያወጅነው ሃፍረታቸን ታወሰኝ። ዛሬ ይህን ስጽፍ የ800 እና 3000 መሰናክል ተወዳዳሪዎች ቶኪዮ መግባታቸውን ስምቻለሁ። ለሜቻም አለ።ስነልቦናውን የጎዱት ለሜቻ ባይሳካለት ተጠያቂው ማን ይሆን? አስቡበት። ዛሬው ቶኪዮ በገባው ልዑክ ዶክተር አያሌው ግን የሉም። “ለምን ዛሬ አብሬ ከነ ለሜቻ ጋር አልሄድኩም” እያሉ እያለቀሱ ነበር። እንደውም በብስጭት ከአቶ ቢልልኝ ጋር ሆነው ሰልፍ ለማደረጃት እየሰሩ መሆኑ ተሰምቷል። እዛ ላላቹህ የሚዲያ ሰዎች መረጃ ለማቀበል ያህል ነው።

የቶኪዮ ኦሊምፒክ በኮቪድ 19 መጋኛ ምክንያት አገሮች ኮታ አላቸው። የሚገቡ ሲኖሩ የሚለቁ ይኖራሉ። በዚህ ምክንያት የዶክተር አያሌው ተራ በ27 እንደሆነ መረጃው ያሳያል። ከዚህ ውጭ ያለው ሩጫ ሁሉ ትርፉ መላላጥ ነው። ለመስከረሙ መንግስት ምስረታ ያድርሰን ዱቤን ጨመሮ መርካቶች ወድ እርሻና ጥቃቅን ንግዶች ይመለሳሉ እንበልና እንመኝ!!


Exit mobile version