Site icon ETHIO12.COM

ትህነግ ቅድመ ሁኔታ አንስቶ ድርድር ጠየቀ፤ “ክተቱ ለትህነግና ለኢትዮጵያ ጠላቶች እንጂ ለትግራይ ሕዝብ አይደለም”

አዲስ አበባ በሁለት ሳምንት ለመግባት የሚያግደው አንዳችም ሃይል እንደሌለ በይፋ ያስታወቀውና በቃል አቀባዩ ጌታቸው አማካይነት ትናንት ጎንደርና ወልቃይት በአሸባሪው ትህነግ እጅ መውደቁን ያወጀው ቡድን ያስቀመጠውን ቅድመ ሁኔታ ትቶ ድርድር እንደሚፈልግ ማስታወቁ ተሰማ። ለዚሁ ተግባር አዲስ አበባ የገቡ አሜሪካዊ አማላጆች መኖራቸውን ታውቋል።

ቀደም ሲል ስምንት ቅደመ ሁኔታዎችን አስቀምጦ የነበረው የትግራይ ሕዝብ ነጻ አውጪ ግንባር ” ድል በድል ሆኛለሁ” እያለ ባለበት ሰዓት ለምንና እንዴት ለተኩስ አቁም አስቀምጦት የነበረውን ቅድመ ሁኔታ ለማንሳት እንደወሰነ የታወቀ ነገር የለም።

” ገና ከአማራ ጋር የምናወራርደው ሂሳብ አለ” በሚልና የማዕከላዊ መንግስቱን ለመጣል በኦሮሞ ጽንፈኞች አማካይነት የተለያየ ሙከራ ሲያደርግ የነበረው ትህነግ አቋሙን ቀይሮ መደራደር እንደሚፈልግ ሁለት የአሜሪካ መልዕከተኞች አዲስ አበባ መግባታቸውን የአዲስ አበባ ተባባሪያችን አመልክቷል።

ወልቃይትና ጎንደር እጅቻእው መግባቱን፣ አዲስ አበባ ለመግባት በሩ ክፍት መሆኑን ባስታወቁ 24 ሰዓት ሳይሞላ፣ ከአዲሱ የድርድር ሃሳብ ጋር በተያያዘ ይሁን በሌላ ጌታቸው ረዳ ዛሬ ” … have been consistent in our principled position on the need for dialogue to end the crisis peacefully. ትህነግ ቀውሱን በሰላማዊ መንገድ በንግግር ለመፍታት አቋማችንና መርሃችን እንደተጠበቀ ነው” ሲል በቲውተር ገጹ ላይ አስፍሯል። በዚህ የቲውተር መልዕክቱ ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ ለንግግር ዝግጁ እንዳልሆኑም አመልክቷል።

ኢትዮጵያ ውስጥ ሕዝብ በራሱ አነሳሽነት ለቁጥር በሚገርም ደረጃ ወደ ወታደር ማሰለጠኛ ጣቢያዎች መትመሙ፣ የደጀኑ ድጋፍና ወላጆች ልጆቻቸውን መርቀው መላካቸው በሚዲያ ይፋ ከሆነ በሁዋላ፣ አቶ ጌታቸው የሰላምና የንግግር ሃሳብና መርህን ደጋግመው መናገራቸው፣ ከዚሁ ጎን ለጎን ከተቱን የትግራይ ሕዝብን ለማጥፋት የሚደረግ ዝግጅት አድርገው መሳላቸው የዛሬ ጠዋት መነጋገሪያ ሆኗል።

መንግስት በተደጋጋሚ እንዳስታወቀውና የክልል መንግስታት በይፋ እንደተናገሩት ” ጉዳያችን ትህነግ ከሚባል አሸባሪ ጋር ነው” በማለት እየገለጹ ባለበት ሁኔታ ጌታቸው ጉዳዩን የትግራይን ሕዝብ ከማጥፋት ጋር ማገናኘቱ ” እንደተለመደው የትግራይን ህዝብ ፍርሃት ውስጥ በመጣል በሁለት አማራጭ ውስጥ ሆኖ ውጊያ እንዲመርጥ ለማድረግ ነው” የሚል አስተያየት ተሰጥቶበታል።

አዲስ አበባ የገቡት የአሜሪካ መልዕተኞች ምን ላይ እንደደረሱ በይፋ ተባባሪያችን ባያረጋግጥም፣ ወልቃይትን ጨምሮ የድንበርና የማንነት ጥያቄ ያለባቸው ቦታዎች መፍትሄ እስኪገኝ በፌደራል ስር እንዲሆኑ፣ የፌደራል አገልግሎት ሰጪ ተቋማት ወደ ትግራይ እንዲገቡ፣ የመብራት፣ የባንክ፣ የስልክ ወዘተ አገልግሎቶች እንዲጀመሩ፣ የትግራይ መልሶ ማቋቋም ልዩ ፕሮግራም እንዲነደፍ… የመሳሰሉት ጉዳዮች ተነስተዋል።

በመንግስት በኩል የተሰጠውን ዝርዝር ምላሽ መረዳት ባይቻልም፤ የተጀመረው ኢትዮጵያን በመከላከያ ሃይል ማግዘፍና ካለችበት ከበባ ባስቸኳይ እንድትወጣ የተጀመረው ንቅናቄ ለአፍታም እንደማይቆም፣ ዝግጅቱ የኢትዮጵያን ሕዝብ ከማንኛውም ስጋት በጥቂት ወራቶች ነጻ ማድረግ፣ በአገሪቱ ውስጥ የሚነቀሳቀሱ ማናቸውንም ታጣቂዎች ለመጨረሻ ጊዜ ለማስወገድ ያለመ ስለመሆኑ ዘጋቢያችን መረጃ አግኝቷል።

መንግስት በይፋ ለሰላማዊ ንግግር ክፍት መሆኑ፣ ህግ የሚገልጋቸው በህግ እንደሚጠየቁ ደጋግሞ ከመናገሩ ውጭ አሁን ትህነግ ጠየቀ ስለተባለው የሰላም ነግግር በይፋ ያለው ነገር የለም።

የሰሞኑ የሕዝብ ንቅናቄና ወዶ ዘማችነት በመላው አገሪቱ እንደ ማዕበል መነሳቱ አሜሪካንን ጨምሮ በርካታ አገሮችን ማስደንገጡ እየተዘገበ ነው። የሽግግር መንግስት በሚል እነ አቶ ልደቱና ሻለቃ ዳዊት ባዘጋጁት ዕቅድ ውስጥ ስማቸው የሚነሳ ሳይቀር ራሳቸውን እያገለሉ መሆኑ ምን አልባትም ከህዝቡ ቁጣ የተነሳ ሊሆን እንደሚችል ግምት አለ።


Exit mobile version