Site icon ETHIO12.COM

ዓለም ትህንግን ዝም አለው “ለምን? ለምን? ለምን?” ቢለኔ ስዩም

ቢለኔ ስዩም ” ለምን፣ ለምን፣ ለምን…?” በማለት የጠየቁትና ” አስደንጋጭ” ሲሉ የገለጹት የዓለም ዓቀፍ ማህበረሰብ፣ አገራት፣ ተቋማትና ሚዲያዎች ትህነግ በግፍና ዓለም በሚጠየፈው ህገወጥ ተግባር ተሰማርቶ ሳለ ዝም ማለታቸውን ነው። እሳቸው ብቻ ሳይሆኑ ድፍን ኢትዮጵያንና ፍትህወዳድ የሆኑትን በሙሉ በተመሳሳይ ” ግን ለምን?” የሚለው ጥያቄ በውሰጠ ታዋቂ ግልጽ ቢሆንም በገሃድ ምላሽ አላገኘም።

የሰብአዊ እርድታ ለተራቡ ዜጎች እንዳይደርስ መደረጉ፣ ስደተኞች መገደላቸው፣ መዘረፋቸው፣ መደፈራቸውና መወረራቸው እየታወቀ፣ ሕጻናት በአደባባይ ዕጽ እየወሰዱ እንደሚዋጉ በመረጃ እየቀረበ፣ ድንበር ታልፎ ንጹሃንን እዲፈናቀሉ እየተደረገ … የዚህ ሁሉ ድርጊት ባለቤትና መሪ ትህነግ ሆኖ ሳለ ዓለም ዓቀፉ ማህበረሰብም ሆነ ሚዲያዎች ጸጥ ማለታቸው ቢለኔ ባይናገሩትም ኢትዮጵያ ላይ የተቀነባበረ ዘመቻ ስለመኖሩ አመላካችና ማረጋገጫ ነው።

በረባው ባልረባው ኢትዮጵያ ላይ ዱላዋን የምትመዘው አሜሪካ በሌላት ተፈጥሮ ለሰው ልጆች ተቆርቋሪ መስላ መንግስትን ስታስጨንቅ ከርማ ዛሬ ላይ ጆሮ ዳባ ልበስ ማለቷ ለኢትዮጵያዊያን ግልጽ መልዕክት ስለላለው ” እኔ ለአገሬ እዘምታለሁ” በሚል ምላሽ ተደምድሟል።

“ሕዝብ በትህነግ ሳቢያ እድሜ ልካችንን ሰላም የማናጣበት ምክንያት የለም” ሲል ክተት መግባቱ ለአሜሪካና ለሌሎች የተሰጠ ምላሽ እንደሆነ ዜጎች ያምናሉ። ቢለኔ ስዩም እጅግ በተደራጀና መረጃ ላይ በተመረኮዘው መግለጫቸው የተጠቀሱኡትን ክፍሎች በሙሉ ደባ ላይ መሆናቸውን አሳይተዋል። ኢትዮጵያን ሊበሏት እንዴት እንደተነሱ በጨዋ መንገድ አሳይተዋል። መግለጫውን ከታች ኢዜአ አጠር አድርጎ አቅርቦታል።

የኢፌዴሪ መንግሥት የወሰደውን የተናጠል የተኩስ አቁም ውሳኔን ወደጎን በማለት አሻባሪው ሕወሃት በአጎራባች ክልሎች ላይ የጠብ አጫሪነት ትንኮሳ እየፈጸመ መሆኑን የጠቅላይ ሚኒስትር ጽህፈት ቤት አስታወቀ።

አሻባሪ ቡድኑ በያዘው የጠብ አጫሪነት ባህሪ የትግራይን ሕዝብ ለተጨማሪ ችግር እንያጋለጠው መሆኑንም ጽህፈት ቤቱ ገልጿል። የጠቅላይ ጠቅላይ ሚኒስትር ጽሕፈት ቤት ፕሬስ ሴክሬተሪያት የውጭ ቋንቋዎችና ዲጂታል ሚዲያ ዘርፍ ሃላፊ ቢለኔ ስዩም ዛሬ በሰጡት መግለጫ፤ ሕወሃት በያዘው የጠብ አጫሪነት ባህሪ በአጎራባች ክልሎች ላይ ትንኮሳውን እንደቀጠለ አስታውቀዋል።

ቡድኑ መንግሥት የወሰደውን የተናጠል የተኩሰ አቁም ውሳኔ እንደ እድል ተጠቅሞ ለትግራይ አርሶ አደር ለሰብዓዊ ድጋፍና ለእርሻ ሥራ እንዲያውለው ማድረግ ሲገባው ተጨማሪ አፍራሽ ሥራ ውስጥ መግባቱን ገልጸዋል። በዚህም የትግራይን ሕዝብን ለተጫማሪ ችግር እንደዳረገው ነው የገለጹት።

ያም ብቻ ሳይሆን ንጹሀን ዜጎችን ለጦርነት በማሰለፍና እንደ ሰብዓዊ ጋሻ በመጠቀም በአፋርና በአማራ ክልሎች በሚኖሩ ሕዝቦች ላይ ጥቃት እየሰነዘረ መሆኑን ተናግረዋል። በአሸባሪ ቡድኑ ምክንያት በተለይም በሁለቱ ክልሎች ያሉ አርሶ አደሮችና አርብቶ አደሮች የዕለት ተዕለት ሥራቸው መስተጓጎሉን አመልክተዋል።

ቡድኑ የዚህ ዓይነቱን እኩይ ተግባር ይበልጥ አጠናክሮ እንደቀጠለ ጠቁመው፤ በትግራይ ክልል ያለው ችግር እንዲቃለል ከማድረግ በተቃራኒ ማባባሱን አስረድተዋል። አሸባሪው ሕወሃት ህጻናት አደንዛዥ እጽ እንዲጠቀሙ በማደረግ ለጦርነት እየማገደ እንደሆነ ጠቁመው፤ ይህንንም በተመለከተ ኢትዮጵያ ድርጊቱን ማውገዟንና ለዓለም አቀፉ ተቋማት ማስታወቋን ገልጸዋል።

ለሚመለከተው ዓለም አቀፍ ተቋም ህጻናቱ አፍራሽ ለሆነው ለሕወሃት ፕሮፓጋንዳ ሰላባ መሆን እንደሌለባቸው ኢትዮጵያ ማስረዳቷን ጠቅሰዋል። በሌላ በኩል ለሰብዓዊ ድጋፍ ተብሎ በእህል ማከማቻ መጋዘን የተቀመጠው 400 ሺ ኩንታል የምግብ ክምችትም ሕወሃት ለራሱ እያዋለው መሆኑን አብራርተዋል።

የሰብዓዊ እርዳታ ማመላለሻ ኮሪደሮችም በቡድኑ መዘጋቱንና የመንግሥት ደጋፊ ያላቸውን የትግራይ ተወላጆችንም እየገደለ እንደሆነ ተናግረዋል። በተጓዳኝም የኤርትራ ስደተኞች በሚገኙባቸው ጣቢያ የዓለም ምግብ ፕሮግራም ግምጃ ቤትን ጨምሮ የተለያዩ የጣቢያውን ንብረቶችን መዝረፋቸውን ገልጸዋል። በስደተኞቹ ጣቢያዎች ላይ ባደረሱትም ጥቃት እስከሁን ስድስት ኤርትራዊ ስደተኞች መገደላቸውን ነው ያስታወቁት።

ኤርትራዊያን ስደተኞች በገንዘብና በዓይነት ለሽብርተኛው አስተዋጽዖ እንዲያደርጉ ከመገደዳቸው በተጨማሪ ከተጠለሉበት ጣቢያ በሃይል እንዲዘዋወሩ መደረጉንም አስረድተዋል።

ይህ ሆኖ ሳለ ዓለም አቀፉ ማኅበረሰብና ዓለም አቀፍ የመገናኛ ብዙሃን ተቋማት ይህንን ከማጋለጥ ይልቅ “ዝምታ መምረጣቸው ያስደነግጣል”በማለት፤ ከፍ ሲልም በዓለም አቀፉ ማኅበረሰበ ላይ ጥያቄ የሚያስነሳ ክስተት መሆኑንም ተናግረዋል።

መንግሥትም ምንም እንኳን እንዲህ ያሉ ችግሮች ቢኖሩም በክልሉ እየተካሄደ ያለውን የሰብዓዊ እርዳታ ለማሳለጥ ከሚመለከታቸው አካላት ጋር እየሰራ እንደሚገኝ ገልጸዋል።

ሕዝቡም በውጭ ከሚገኘው ዲያስፖራ ማኅበረሰብ ጋር በመቀናጀት የአሸባሪውን ሕወሃት እኩይ ተግባር በማጤን ለመመከት እያደረገ ያለው ሥራ የሚበረታታ መሆኑን ገልጸቅ፤ይህም ተጠናክሮ ሊቀጥል እንደሚገባ ተናግረዋል።


Exit mobile version