ETHIO12.COM

ለሜቻ “እችላለሁ” ሲል ለፌዴሬሽኑ ማላሹን በገሃድ ሰጠ፤ ብር አገኘ፣ 5000 በሴቶች ነሃስ

በ5000 ሜትር ጉዳፍ ፀጋዬ የነሀስ ሜዳሊያ እንዲሁም ለሜቻ ግርማ በ3ሺ ሜትር መሰናክል የብር ሜዳልያ አስገኝተዋል። ድሉ ያስደስታል። ለሜቻ ላይ አሳፋሪ ቃላትና ግምገማ ያካሄዱ በአደባባይ ማፈራቸው ደግሞ ሌላው ሃሴት ነው።

ለሜቻ ” አትችልም፤ ሜዳላ ፌንት ታደርጋለህ፤ ለሩጫ ዋጋ የለህም” የተባለ አትሌት ነው። ሩጫው ስለተጠናቀቀ በገሃድ መናገሩ አስፈላጊ ነውና መባል አለበት። በኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌዴሬሽን ደንብ መሰረት ኮቪድ ስለነበረበት ኢትዮጵያ ሽምፒዮና አለመወዳደሩ እየታወቀ፣ ሃጢያት ተደርጎ ተወሰደበት። ሄንግሎ ላይ እግሩን ታሞ መወዳደር እንዳልቻለ የራሱ የፌዴሬሽኑ ሃኪም አረጋገጠው ሳለ ጥፋተኛ ተደርጎ መግለጫ ተሰጠበት። አሰልጣኙ ” ከእሱ የተሻለ ሯጭ የለም። እባካችሁን ጊዜ ይሰጠው ኦሊምፒክ ገና ግዜ አለ” ሲሉ ” እሱ ዋጋ የለውም” ተብሎ ተባረረ። በሳምንቱ ሞናኮ ሄዶ አዲስ ሪኮርድ በማስመዝገብ በዳይመንድ ሊግ አሸነፈ።

የኢትዮጵያ ኦሊምፒክ የቴክኒክ ኮሚቴ በወሰነው መሰረት ለሜቻ በግድ ወደ ቶክዮ ሲሄድ ደስተኛ የነበሩት አስልጣኙ፣ ኦሊምፒክ ኮሚቴና ችሎታውን የሚያውቁ አገር ወዳዶችና እሱ ብቻ ነበሩ። ፌዴሬሽኑ ግን ” መርህ ተጣሰ” በሚል አዲስ አበባ ላይ ቁጭ ብሎ ” ሕዝባችን፣ መንግስታችን” እያለ የዶክተር አያሌው ቶኪዮ አለመሄድ ጨንቆት መግለጫ ይሰጥ ነበር። ከለሜቻ ይልቅ ለሜቻን ” ዋጋ የለውም፣ ፌንት ያደርጋል” ላለ ጡረተኛ ሃኪም ይሟገት ነበር። ዶክተር አያሌው በዚህ ኦሊምፒክ ብቻ ሳይሆን በበርካታ ጉዳዮች ሙያዊ ስህተትና ውስልትና የፈጸሙ መሆናቸው እየታወቀ አመራሩ ከገርና ባንዲራ ይልቅ ለሳቸው ደረት ሲመታ ሰንብቷል። ለሜቻ ግን ያመኑበትን ሳያሳፍር ብዙም በማንታወቅበት 3000 መሰናክል አሸንፎ የአገሩን ባንዲራ ከፍ አድርጓል። ክብር ይገባዋል።

ዶክተር አያሌው አትሌት ወርቅውሃ ጌታቸው በ800 ሜትር እጅግ የምትጠበቅ ተወዳዳሪ ብትሆንም ለዓለም ዓቀፉ ኦሊምፒክ በላኩት ኢሜል ምክንያት አልተወዳደርችም። አትሌቷ የሆርሞን መጨመር ችግር ቢያገጥማት እንኳን 1500 ሜትር መወዳደር እየቻለች በሚስጢር ይህ መደረጉ አስደንጋጭ፣ አሳዛኝ፣ ከዚያም በላይ ዓለም ዓቀፉ ፌዴሬሽን ሳይከለክላት ዶክተር አያሌው ይህን ማድረጋቸው ልጅቱና አንገት አስደፍቷታል።

ይድነቃቸው ከስፍራው እንደዘገበው ከሆነ አዲስ አበባ እንደደረሰች በዶክተር አያሌው ላይ ክስ ትመሰርታለች። የማትወዳደር ከሆነች ለረጅም ወራት በዝግጅት፣ ከዛም ለምን ቶኪዮ እንድትሄድ ተደረገ ለሚለው ጥያቄ ደራርቱም ሆነ ዶክተር አያሌው ከማጭበርበር ውጭ ምላሽ ሊኖራቸው አይችልም።

ስማቸው እንዳይጠቀስ የጠየቁ አሰልጣን ” ወርቅውሃ ፕሮቶኮሏ አልተጠበቀም። አዋርደዋታል። ቢያንስ ቢያንስ 1500 ሜትር መሮጥ የምትችል ውጤታማ አሰለጣን ነበረች። የለሜቻ ሲገርመን እሷንም…” ብለዋል። ሙክታር እድሪስም አሁን ላይ ብቃት ያለው መሆኑ እየታወቀ “ለምን ከለሜቻ አስለጣኝ ጋር ሰራህ” በሚል እንዳይወዳደር መደረጉ ታውቋል።

ከለሜቻ ጋር አብሮ የሮጠውና አራተኛ የወጣው ጌትነት በመሰናክል ከለመድነው ውጢት አንጻር ድሉ እጅግ የሚበረታታና ክብር ሊሰጠው የሚገባ ሆኖ ተገኝቷል። በደንብ ከተሰራበት ውጤት ሊገኝበት የሚችል ሌላው ምድብ እንደሆነ አመላካች ነው።

5000 ሴቶች ፍጻሜ ውጤት

5000 ሜትር ጉዳፍ ፀጋዬ የነሀስ ሜዳሊያ ወስዳለች። አትሌቷ ብዙም ልምድ የሌላትና እንደ ሲፋን ካሉ መብረቅ ተወዳዳሪዎች ጋር መወዳደሯን ከግንዛቤ ውስጥ ለሚያስገቡ ውጤቷ ተስፋ ያላት ተወዳዳሪ መሆኗን ነው።

ሲፋን ሃሰን እየተንሳፈፈች ብቃቷን ባሳየችበት በዚህ ውድድር ከአሸነፈች በሁዋላ የኒዘርላንድን መለያ ለብሳ አንብታለች። ተገፍታ ዜግነቱና የቀየረችው ሲፋን ገና ሌላ ሜዳሊያ ከዚ በበለጠ ብቃት እንደምታገኝ ለኖርዌይ ሚዲያ አስታውቃለች።

በዚህ ውድድር ኪንያዊቷ ትሪዮፕ 2ኛ ስትወጣ፣ እጅጋየሁና ሰንበሬ አምስትና ስድስተኛ ሆነው ጨርሰዋል። ውጤቱ ከዓለም አንጻር ትልቅ ቢሆንም፣ ከለመድነው ጋር ሲወዳደር የሩጫ ውጤት ከቀን ወደ ቀን እየወረደ መምጣቱን አማለካች ነው። ተተኪ ማፍራት አለመቻሉን የሚያሳይ ነው። አንድ ኦሊምፒክ ዓመት ሲያልቅ ለአንድ ሌላ አራት ዓመት አቅዶ መስራት የሚባል ጥበብ መንጠፉን አመላካች ነው።

በውስን አትሌቶች ችሎታና፣ አትሌቶቹ ለረዥም ጊዜ ውጤታቸውን አስጠብቀው በመኖራቸው ሳቢያ ሲሾምና ሲሸለም የኖረው ፌዴሬሽን ዛሬ ላይ ሊፈተሽ፣ በዕውቀት ሊመራ እንደሚገባና እጅግ በርካታ ጠቋሚ ጉዳዮች አሉ። በርካታ ችግሮች ወጥረው የያዙት ፌዴሬሽኑ የተወሰኑ ሴረኞች ታዋቂ ሯጮችን ከፊት በማቆም እየበተበጡ እንደሆነ አሰልጣኞችና ለቤቱ ቅርብ የሆኑ ጠቁመውናል።

ማሳሰቢያ

በውጤቱ ላይ ጫና ላለማሳደር በርካታ ጉዳዮችን ለማንሳት እንቸገራለን። እጅግ አሳፋሪና ለማመን የሚከብድ ደባ እየተሰራ ነው። ከውድድሩ በሁዋላ በስፋት እንመጣበታለን። ለዛሬ ግን ከማራቶን አትሌቶች መካከል እንዳይወዳደሩ ቅስቀሳ እየተደረገ መሆኑን ጥቆማ ደርሶናል። ይህ የሚሆነው ሆን ተብሎ ነው። ” አሞኛል ብለህ ውጣ” በሚል ከፌዴሬሽኑ አመራሮች ምክር ሲሰጥ መስማቱን የገለጸልን አትሌት ” ምን እንደሚፈለግ አይገባኝም” ሲል ውጤቱ ቢበለሽ ሊጠየቁ የሚገባቸው ወገኖች መኖራቸውን አመልክተዋል።

Exit mobile version