Site icon ETHIO12.COM

ከ2 ቢሊየን ብር በላይ ገንዘብ በሃሰተኛ ሰነድ ከባንክ ሊያወጡ የሞከሩ 3 ግለሰቦች በቁጥጥር ስር ዋሉ

ከ2 ቢሊየን ብር በላይ ገንዘብ በሃሰተኛ ሰነድ ከባንክ ሊያወጡ ሲሞክሩ የነበሩ 3 ግለሰቦች በቁጥጥር ስር መዋላቸውን የፌዴራል ፖሊስ ኮሚሽን አስታወቀ፡፡

ኮሚሽኑ ከፋይናንስ ደህንነት መረጃ ማእከል ጋር በመቀናጀት ባደረገው የቀናት ክትትል መነሻ በማድረግ ነው ተጠርጣሪዎቹ በቁጥጥር ስር ሊውሉ የቻሉት።

በፌዴራል ፖሊስ ኮሚሽን ወንጀል ምርመራ ቢሮ የፋይናንስና ንግድ ወንጀሎች ምርመራ ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር ረዳት ኮሚሽነር ብርሃኑ አበበ በሃሰተኛ ሰነድ ሊመዘበር የነበረው ገንዘብ በኢትዮጵያ ንግድ ባንክ የተቀመጠ የሳሊኒ ኮንስትራክሽን ሂሳብ መሆኑን ለኢቲቪ በሰጡት መግለጫ አንስተዋል።

በታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ግንባታ ስራ ላይ ተሰማርቶ ውጤታማ የሆነው የዚህ ኩባንያ ሂሳብ በሃሰተኛ ሲፒኦ ሊያጭበረብሩ ጉዞ ላይ እያሉ በቁጥጥር ስር የዋሉት 3ቱ ተጠርጣሪዎች ተስፋሚካኤል ታመነ ፣ተክለ ብርሃን በርሄ እና መክብብ በላይ የተሰኙ ግለሰቦች ናቸው።

ተጠርጣሪዎቸ ዛሬ እኩለ ቀን አካባቢ በለሚ ኩራ ክፍለ ከተማ የተባበሩት ማደያ አካባቢ ለዚሁ ተግባር ከሚጠቀሙባቸው ተሽከርካሪዎች ጋር በቁጥጥር ስር መዋላቸውንም ነው ረዳት ኮሚሽነር ብርሃኑ የተናገሩት።

ተጠርጣሪዎቹ ከአሸባሪው ህወሓት ቡድን ጋር ግንኙነት ሳይኖራቸው እንደማይቀርም ረዳት ኮሚሽነሩ ተናግረዋል።

በአሁኑ ሰአት የተጠርጣሪዎች መኖሪያ ቤት ከፌዴራል የመጀመሪያ ደረጃ ፍርድ ቤት ከአራዳ ምድብ ችሎት በተገኘ የብርበራ ትዕዛዝ እየተፈተሸ መሆኑንም አብራርተዋል።

ENA

Exit mobile version