በድሬዳዋ የሽብር ተግባር ሊፈጽሙ የነበሩ የሸኔ አባላትና የተለያዩ የጦር መሳሪያዎች በቁጥጥር ስር ዋሉ

በድሬዳዋ ከተማና አካባቢው የሽብር ተግባር ለመፈጸም ሲንቀሳቀሱ ነበር የተባሉ የአሸባሪው የሸኔ አባላትና የተለያዩ የጦር መሳሪያዎች በቁጥጥር ስር ማዋሉን የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ መምሪያ ዕዝ አስታወቀ። የድሬዳዋ አስተዳደር ፖሊስ ኮሚሽን ኮሚሽነር አለሙ መግራ እንደገለጹት አሸባሪው የኦነግ ሸኔ ቡድን በምስራቅ ኢትዮጵያ በተለይም በድሬዳዋና አካባቢው ታህሳስ 11 ቀን 2014 ዓ.ም ልዩ ስሙ ገንደገበሬ በተሰኘው አካባቢ ግጭት ፈጥሯል፡፡ 

ይህን ተከትሎም የብሄራዊ መረጃና ደህንነት፣ የድሬዳዋ ፖሊስ፣ የፌዴራል ፖሊስ፣ የሀገር መከላከያ ሰራዊት፣ ከሚሊሻና ከህብረተሰቡ ጋር በመቀናጀት በተደረገው ዘመቻ 4 የሽብር ቡድኑን አባላት የጦር መሳሪያዎቻቸውን በተለያዩ ስፍራዎች በመደበቅ እራሳቸውን ከህብረተሰቡ ጋር በማመሳሰል ለመንቀሳቀስ ሲሞክሩ በቁጥጥር ስር መዋላቸውን አብራርተዋል፡፡ በቅርቡ የምስራቅ አካባቢ የኦነግ ሸኔ አዛዥና ጃል ኦዳ ኢብሳ በሚል ስያሜ የሚጠራው ፉአድ ሀሰን ከቢራ የተሰኘው የቡድኑ መሪ ሀረር ላይ በቁጥጥር ስር መዋሉን አስታውሰዋል፡፡ 

በእነዚህ የሸኔ በአባላት ላይ በተደረገው ምርመራ ለሽብር ተግባር ሲጠቀሙባቸው እና ሊጠቀሙባቸው የነበሩ የተለያዩ የጦር መሳሪዎች እንዲሁም 24 ተጠርጣሪ ግለሰቦች በቁጥጥር ስር መዋላቸውን ከድሬዳዋ መገናኛ ብዙሃን ኤጀንሲ ያገኘነው መረጃ ያመላክታል። በፌዴራል ፖሊስ ኮሚሽን የወንጀል ምርመራ ዘርፍ የምስራቅ ቀጠና ዲቪዥን ሃላፊ ም/ኢንስፔክተር ለሜሳ መኮንን በበኩላቸው÷ የሽብርተኛው ሸኔ ቡድን አባላት ራሳቸውን ከህብረተሰቡ ጋር በማመሳሰል ለመሰወር ሲሞክሩ ነው በቁጥጥር ስር የዋሉት፡፡ 

በተጨማሪም 20 የክላሽንኮቭ መሳሪያዎች ከ2 ሺህ 648 ጥይቶች ጋር፣ 798 የብሬል ጥይቶች ፣ 38 የክላሽንኮቭ ካዝና፣ 2 ቦንቦች ፣ 1 ጂም ስሪ መሳሪያ ከ38 ጥይቶች ጋር፣ ወታደራዊ ትጥቆች፣ የመገናኛ ሬዲዮን ጨምሮ ሌሎች ወታደራዊ ቁሳቁስ በተጠርጣሪዎቹ ላይ በተካሄደው ምርመራ ከቀበሩባቸው ስፍራዎች በፍተሻ መገኘታቸውንም ፋና ኮሚሽነሩን ጠቅሶ አስታውቋል።

Leave a Reply