Site icon ETHIO12.COM

ጠርጥር! ጥርጣሬህንም ቢሆን ጠርጥር!

አስተሳሰብህን ጠርጥር! ፖለቲካህን ጠርጥር! ራሱ ጥርጣሬህንም ቢሆን ጠርጥር!
(Be skeptical even of your skepticism)
(እ.ብ.ይ.)

አባቶቻችን ‹‹ጠርጥር ገንፎም አለው ስንጥር››፣ ‹‹ያልጠረጠረ ተመነጠረ›› እያሉ ጥርጣሬ እውነትን ማግኛ፤ ከክፉ ወጥመድ ማምለጫ መንገድ አድርገው በምሳሌውም በተረቱም ያስተምሩናል፡፡ መጠርጠር በቅን ልቦና ከሆነ መድረሻው እውነትና እውቀት ነው፡፡ ስሜትን መጠርጠር ከደመነፍስ ውሳኔ ያድናል፡፡ አቋምን መጠርጠር ከመውደቅና ከመደናቀፍ ይጠብቃል፡፡ ሃሳብን መጠርጠር ከግራመጋባት ይመልሳል፡፡ አዙሮ ማየት፣ መለስ ብሎ መመልከት፣ አራት ዓይና መሆን ጥርጣሬን ማስወገጃ፣ ግራ መጋባትን ማጥሪያዎች ናቸው፡፡ መጠርጠር የምርምር መስመር ነው፡፡ ዓለሙን የጠረጠሩ የዓለሙን አስከፊ ሁኔታ ለውጠዋል፡፡ የኖርንበትን አስተሳሰብ የጠረጠሩና ዙሪያ ገባውን አመለካከት የመዘኑ የተሻለ እውቀትና ማንነት ላይ ደርሰዋል፡፡ ዓለም እዚህ ዝማኔ ላይ የደረሰችው እውነት ባይሆንስ፣ ልክ ባይሆንስ፣ የምንከተለው መንገድ የተሳሳተ ቢሆንስ ብለው ሁኔታውን፣ መንገዱን፣ ውስጡን ባጠኑ ጥልቅ አሳቢያን ነው፡፡

የምዕራቡ ዓለም ፍልሰፍና ከተወለደ ሁለተኛ ሚሊንየሙን አሳልፏል፡፡ ነገር ግን ዘመናዊው ፍልስፍና ከጥንታዊው ፍልስፍና ዕድሜ ጠገብነት አንጻር በንፅፅር ሲታይ ዕድሜው ገና ለጋ ነው፡፡ የመጀመሪያዎቹ የጥንታዊው ፈላስፎች ምድብ መገኛ ሐገር ግሪክ ስትሆን በጊዜው ከነበሩት ፈላስፎች መካከል በዋነኝነት የሚጠቀሱት እነሶቅራጦስ፣ ፕሌቶ፣ አርስጣጢሊስ እና ሌሎችም ናቸው፡፡ የሁለተኛው የፈላስፎች ምድብ መነሻውን ሰሜን አውሮፓ ያደረገ ሲሆን ተጠቃሽ ተዋናዮቹም የነበሩት ዴስካርቴ፣ ሆብስ፣ ሰፒኖዛ፣ ሎክ፣ ሊቤንዝ፣ ሂዩም፣ ሩሶ፣ ቮልቴርና ሌሎችም ናቸው፡፡ እነዚህ የዘመናዊውን ፍልስፍና ለዓለሙ ያስተዋወቁ፣ የስነክዋክብቱን፣ የጨረቃውን፣ የትዕይንተ ዓለሙን ፍልስፍና ከሰማይ አውርደው የሰውነትን ፍልስፍና ወደሰው ልጅ ልቦና የዶሉ፤ የተኛውን አዕምሮ የቀሰቀሱና ጨለማውን ዘመን በዕውቀት ብርሃን የገፈፉ፤ የሃሳብ አብዮት ያስነሱ፣ ለምን፣ አንዴት ብለው የጠየቁ የሃሳብ አብዮቶኞች ናቸው፡፡ በሁለቱም ምድብ የነበሩት ፈላስፎች ፍልስፍናን ለገንዘብ ጥቅም ሳይሆን ለእውነት፣ ለመንፈስ ደስታ የተፈላሰፉባት፣ ለዕውቀት የረቀቁባት፣ ቁሳዊ ችግርን ለመፍታት ሳይንስን ፀንሰው የወለዱባት፤ እውነትን ፈላጊዎች፣ ጥበብን አሳዳጆች፣ ዕውቀትን አጥማጆች ነበሩ፡፡ ያለምንም ቁሳዊ ክፍያ ሕሊናቸውን በዕውቀት አጥግበው፤ ለጥበብ ሲሉ ነፍሳቸውን እስከመስጠት የደረሱ አስቦ አዳሪዎች፣ ሰርቶ አሳዪዎች ናቸው፡፡ 18ኛው ክ/ዘመን ያበቀለው የዕውቀት ብርሃን (Enlightnment) እነዴስካርቴ በ17ኛው ክ/ዘ የዘሩትን ነው፡፡ ዓለም የዛሬዋ ስልጣኔ ላይ እንድትደርስ ዋጋ የከፈሉ ጥልቅ አሳቢያን ክብር ይገባቸዋል፡፡

ከዘመናዊው ፈላስፎች መካከል አንደኛው ሰው ዴስካርቴ ነው፡፡ ይህ ሰው እውነትን የሚፈልግበት መንገድ የተለየ ነበር፡፡ የፍራንሲስ ቤከን አባባል የእሱ የፍልስፍናው መመሪያ ሆኗል፡፡ ፍራንሲስ ቤከን፡-

‹‹በእርግጠኝነት የጀመረ ሰው በጥርጣሬ ይጨርሳል፡፡ ነገር ግን በጥርጣሬ የጀመረ በእርግጠኝነት ይጨርሳል፡፡ (If man will begin with certainties, he shall end in doubts, If he will be content to begin with doubts, he shall end in certainties)›› ይላል፡፡

የዴስካርቴ ፍልስፍና የፍራንስስ ቤከን ግልባጭ ነው፡፡ ጠርጣራነቱ እውነትን የሚፈልግበት አዋጭ መንገዱ ነው፡፡ ስሜቱን አያምንም፡፡ ስሜታችን አሳሳች ነው ብሎ ነው የሚያስበው፡፡ በማሕበረሰቡ እምነትና አመለካከት ላይ አመኔታ የለውም፡፡ ባህሉንም፣ ሃይማኖቱንም ወግ ልማዱንም ይጠረጥራል፡፡ የራሱን ሃሳብ እንኳን እንደወረደ አያምነውም፡፡ ከእኛ አስተሳሰብ ውጪ በእኛ ላይ ሃይል ያለው ማንም የለም ይላል፡፡ ያልተጠረጠረና ያልተመነጠረ አስተሳሰባችን ነው አሁን ላለንበት የክፋት ጥግ፣ የማንነት ቀውስ፣ የውርደት ደረጃ ያደረሰን ሲል ይናገራል፡፡

እውነት ነው! ባህላችን፣ አኗኗራችንና ወግ ልማዳችን እንድናስብ ሳይሆን ዝም ብለን እንድንቀበል ነው የሚገፋፋን፡፡ ልናራግፋቸው የሚገቡን የተጫኑብን የመንፈስ ሸክሞች ብዙ ናቸው፡፡ ስነልቦናችን ልክ አይደለም፡፡ አስተሳሰባችን የጠራ አይደለም፡፡ ማሕበረሰባችን ምን፣ ለምን፣ እንዴት ብሎ መጠየቅ አላስለመደንም፡፡ ወይ መቀበል አልያም መቃወም ነው የተማርነው፡፡ ስንቀበል እንዴት፤ ስንቃወም ለምን ብለን አንጠይቅም፣ ምክንያታችንን አናስቀምጥም፣ ማስረጃችንን አናቀርብም፡፡ ዓለሙ የጋተን በግድ ማመንን ወይም በሃይል ማሳመንን ነው፡፡ በታሪካችን ጀግና የሚባለው ጉልበተኛው ነው፡፡ ዘመደ ብዙን እንፈራለን፤ ብቸኛውን እናስፈራራለን፡፡ ደሃ አደጉን እንበድላለን፤ ለባለ ገንዘቡ እናደላለን፡፡ ሰውን በነፃና በእኩል ደረጃ መውደድ አልተለማመድንም፡፡ አሁንም ባለጡንቻው ይሾማል፣ ይሸለማል፣ ይፈራል፣ ይታፈራል፣ ይገበርለታል፡፡ ዛሬም ጦርነት የሃሳብ ልዩነቶቻችን መፍትሄ እንደሆነ ነው፡፡ ያለነፍጥ በሃሳብ ለመሸናነፍ የተዘጋጀን አይደለንም፡፡ በዘመናዊው ዓለም ውስጥ የምንኖር ኋላ ቀር ህዝቦች ሆነናል ብል ማጋነን አይሆንብኝም፡፡ ባለስልጣኑን አንጠረጥርም፤ ፖለቲካችንን አንጠረጥርም፤ ካድሬውን አንጠረጥርም፣ ሴራውን አንፈትሽም፡፡ ርዕዮታችን ሰልባጅ ነው፡፡ በልካችን የተሰፋ ፖሊሲም ሆነ ስትራቴጂ የለንም፡፡ እቅዳችን የሚሳካው በሪፖርት እንጂ በተግባር አይደለም፡፡ የምናምነውን መዝነንና መርምረን አናምንም፡፡ ወገንተኝነት ያጠቃናል፡፡ አድሏዊነት አጥፍቶናል፡፡ የምንቃወመው፣ የምንጠላው፣ የምንወደውም በጅምላ ነው፡፡ በግል የምንወስንበት ደረጃ ላይ አልደረስንም፡፡ ተማርን የምንል ብንኖርም መማራችን በተግባር አልታየም፡፡ ሃሳባችን መሬት ላይ መውረድ አልቻለም፡፡

ወዳጄ ሆይ…. ዴስካርቴ፡- ‹‹ጥርጣሬ የጥበብ መገኛ ነች! (Doubt is the origin of wisdom)›› እንዲል መጠርጠር የሚገባህን ሁሉ ጠርጥር፡፡ አዎ ፍቅርህንም ቢሆን ጠርጥር፡፡ ጠብህንም ጠርጥር፡፡ ፖለቲካህንም ጠርጥር፤ ፍልስፍናህን ጠርጥር፤ ስሜትህንም ጠርጥር፡፡ ከሁሉ ይልቅ ሃሳብህን ጠርጥር፡፡ ዕውቀትህንም ጠርጥር፡፡ አሁን የያዝኩት እውቀት፣ እውነትና እምነት ልክ ነውን ብለህ መዝን፡፡ አጉል ጥርጣሬ እንዳይሆን ራሱ ጥርጣሬህንም ቢሆን ጠርጥር! ጠርጥር ስልህ መርምር እያልኩህ እንደሆነ አትዘንጋ፡፡ አንተነትህን ፈትሽ! ሕይወትህን ፈትሽ! ስሜትህን ፈትሽ፣ መንፈስህን ፈትሽ! የአስተሳሰብ ማዕከልህን፣ የአመለካከት ድንበርህን ፈትሽ!

‹‹ጠርጠር እንዳታጥር፤
ጥርጣሬህንም ጠርጥር፣
ወደኋላ እንዳትነጥር፡፡
ፈትሽ እንዳትቆሽሽ!
ሞራልህ እንዳይሟሽሽ፤
ሩጥ መርሽ…
ከሐሰቱ ሽሽ፡፡››

ቸር ጥርጣሬ!


እሸቱ ብሩ ይትባረክ (እ.ብ.ይ.)
ዕለተ እሁድ ነሐሴ ፪ ቀን ፳፻፲፫ ዓ.ም.

Exit mobile version